ስለ ካርድ

የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) ቦርድ-መር የሆነ፣ ለትርፍ ያልተቋቋመ እና በተሻሻለው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ 1113/2011፣ በመዝገብ ቁጥር 4307፣ ሐምሌ 17፣ 2011 የተመዘገበ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ነው። ካርድ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ተፈጥራ ማየትን ራዕይ አድርጎ፣ ዴሞክራሲ ብቸኛው የጫወታ ሕግ እንዲሆን የዴሞክራሲ መርሖዎችን የማስተጋባት ተልዕኮ ይዞ እየሠራ ይገኛል።

ካርድ የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ፕሮጀክት (ኢሰመፕ) በሚል መጠሪያ ከኢትዮጵያ ውጭ ተቀማጭ የነበረው የሰብኣዊ መብቶች ላይ የሚሠራ ተቋም ዳግም ሥሪት ነው። ኢሰመፕ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶችን መመርመርና የፍርድ ቤት ጉዳዮችን መከታተል ሥራዎችን ይሠራ በነበረበት ጊዜ ከ50 በላይ የኅሊና እስረኞችን የፍርድ ቤት ጉዳዮች እና የእስር ቤት አያያዝ ክትትል እና ዘገባ ሲያደርግ ነበር። በ2011 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን አዋጅ መሻሻል ተከትሎ፣ ካርድ እንደ አዲስ ተቋቁሟል።

መርሐ ግብሮች እና ዒላማዎች

ካርድ መብቶች-ተኮር የሆነ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ዘዴ ይከተላል። በአሁኑ ወቅት ካርድ የሚሠራባቸው አራት መርሓ ግብሮች ናቸው። እነዚህም፦

 1. የዜግነት ተሳትፎ
 2. ወጣቶችና ሴቶችን ማብቃት
 3. የሚዲያ አረዳድ ግንዛቤ ማሳደግ፣ እና
 4. የዲጂታል መብቶች ናቸው።

ካርድ እነዚህን መርሓ ግብሮች በተለያዩ ፕሮጀክቶች እያከናወነ ሲሆን፣ ዒላማ አድርጎ እየሠራባቸው ያሉት ተደራስያኑ የሚከተሉት ናቸው፦

 1. ወጣት መሪዎች እና የመብቶች አራማጆች፣
 2. የሚዲያ ባለሙያዎች እና የበይነመረብ ላይ ይዘት አዘጋጆች፣
 3. ወጣቶች እና ሴቶች፣
 4. የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣
 5. መንግሥታዊ የዴሞክራሲ ተቋማት።

የካርድ ራዕይ

ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ማየት።

የካርድ ተልዕኮ

የዴሞክራሲ መርሖዎችን በማስተጋባት ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ብቸኛው የጫወታ ሕግ እንዲሆን መሥራት።

የካርድ ዓላማዎች

ካርድ ሊያሳካቸው የሚያልማቸውና በሕግ የተመዘገበባቸው ዓላማዎቹ የሚከተሉት ናቸው፦

 • ዴሞክራሲያዊ ባሕል በኢትዮጵያ እንዲጎለበት በዴሞክራሲያዊ መርሖች ዙሪያ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት፣
 • መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ተጠያቂ እንዲሆኑ ወቅታዊ የመከታተል እና ግምገማ ሥራዎችን መሥራት፣
 • አስፈላጊ የሆኑ ለውጦችን ለማምጣት የፖሊሲ ጥናትና ምርምር እንዲሁም ምክክር እና ግፊት ማድረግ፣
 • ለዴሞክራሲ ተቋማት ሙያዊ እና ቴክኒካዊ ድጋፍ ማድረግ፣
 • የሰብኣዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ የፖሊስ ማቆያዎችን፣ ማረሚያ ቤቶችን እና ፍርድ ቤቶችን መከታተልና መገምገም፣
 • ምርጫዎችን መታዘብ፣ የሥነ ዜጋ እና የመራጮች ትምህርት መስጠት።