የ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን መ/ቤት ድርጅታችን ማገዱን ተከትሎ ከመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) የተሰጠ መግለጫ

የ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን መ/ቤት ድርጅታችን ማገዱን ተከትሎ ከመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል

 (ካርድ) የተሰጠ መግለጫ

ሕዳር 14፣ 2017 

ውድ አጋሮቻችን፣ ደጋፊዎቻችን እና ብዙኃን የካርድ ሥራዎች ተከታታዮች፣

የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) ሕዳር 3 ቀን 2017፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለሥልጣን (ACSO) በተላከ ደብዳቤ ድርጅታችን ካርድ ከሥራው እንደታገደ ለመረዳት ችለናል። ደብዳቤው የእግዱን መንስዔ ሲያስረዳ "ከፖለቲካ ገለልተኛ መሆን ሲገባው፣ ከዓላማው ውጭ በመንቀሳቀስ የአገርን ጥቅም የሚጎዱ ተግባራት ላይ ተሠማርቷል” የሚል ይዘት አለው። 

ይሁንና ድርጅታችን ካርድ ለእግድ የተሰጠው ምክንያት ከእውነታው የራቀ መሆኑን አበክሮ ለመግለጽ ይወዳል። ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ እግዱን ለመጣል እንደ ምክንያት የገለጸው የምርመራ ሒደት ስለመከናወኑ ድርጅታችን ምንም ዓይነት መረጃ ያልነበረው ከመሆኑም ባሻገር፣ ውሳኔው አስፈላጊ የሆኑትን ሕጋዊ አካሄዶች እንዳልተከተለ ለመግለጽ እንወዳለን። እንደማሳያም፣ የምርመራ ሒደቱን ካርድ እንዲያውቅ ተደርጎ፣ በግልጽ ሒደት ድርጅቱ መሳተፍ ይጠበቅበት የነበረ ቢሆንም በተግባር ግን ይህ አልተደረገም። ካርድ ከዓላማው ውጪ ምንም ዓይነት ተግባራት ላይ እንደማይሳተፍ እና በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ፍጹም ገለልተኛ ተቋም መሆኑን በድጋሜ በአጽንዖት ለመግለጽ ይወዳል። 

ግልጽነት፣ ገለልተኝት እና ዴሞክራሲያዊነት የካርድ የማያወላውል መርሖዎች መሆናቸውን እያስታወስን፣ ድርጅታችን ሕጋዊ ሰውነት ካገኘበት፣ ከሐምሌ 17 ቀን 2011 ጀምሮ ካርድ ሰብዓዊ መብቶችን የሚከበሩባት እና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ያበበባት ኢትዮጵያን ለማየት የሚያስችሉ በርካታ አዎንታዊ ሥራዎችን በመሥራት አገራዊ ፋይዳ ያላቸው አስተዋፅዖዎችን ሲያበረክት ቆይቷል። በዚህም፣ ከ40 በላይ አገር ዐቀፍ እና ዓለም ዐቀፍ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እና በመቶ ሺሕዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ጋር የሚደርሱ ሥራዎችን፣ የሰብዓዊ መብቶችን እሴቶች እና ዲሞክራሲያዊ ሕዝባዊ ባሕልን ለማጎልበት የሚያስችሉ ፕሮግራሞችን እና ስትራቴጂካዊ ሥራዎች በዋነኛነት የሚጠቀሱ ናቸው። 

ድርጅታችን ካርድ እንደ ውርድወት ፌሎውሺፕ እና አዲስ የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ትውልድ በመሳሰሉት ፕሮጅክቶቹ፣ ወጣቶችን እና የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥም ቢሆን ለሰላምና ለእኩልነት እንዲሁም ለሰብዓዊ መብቶች ጥብቅና እንዲቆሙ የሚያስችሉ ምርምሮችን እንዲሠሩ እና ሥልጠናዎችን እንዲያገኙ እየሠራ ይገኛል። ጋዜጠኞች እና ዜጎች መረጃ እንዲያገኙ፣ ሐሳባቸውን በነጻነት እንዲገልጹ እንዲሁም ደኅንነቱ በተጠበቀ የዲጂታል ምኅዳር ተሳትፎ ማድረግ እንዲችሉ የሚዲያ ነፃነት እና ዲጂታል መብቶችን የሚያበረታቱ ሥራዎችን ሠርተናል። በተጨማሪም የኢትዮጵያን ክልላዊ መስተዳድሮች ዴሞክራሲያዊ ሒደቶች ለመከታትል እና ለመሰነድ የሚያስችሉ ሥነ ዘዴዎችን ቀርፀን ሪፖርቶችን ይፋ ማድረግ ጀምረናል። 

"ዴሞክራሲን ብቸኛው የጨዋታው ሕግ ማድረግ" በሚለው መሪ ቃላችን በመመራት ካርድ በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ማዕቀፍ ውስጥ ለኢትዮጵያ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ተግዳሮቶች መፍትሔ እንዲገኝ መሟገቱን ቀጥሏል። በአሁኑ ወቅት ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጋር በመነጋገር የእግድ ውሳኔው እንዲነሳ እና የተፈጠረው አለመግባባት መፍትሔ እንዲያገኝ በትብብር መንፈስ እና ሕጉን መሠረት ባደረገ መልኩ ጥረት እያደረግን እንገኛለን። ለዚህ ችግር መፍትሔ በምናፈላልግበት በዚህ ጊዜ፣ አጋሮቻችን እና የሥራዎቻችን ተከታታዮች እገዛ፣ ክትትል እና ትዕግስት እንዳይለየን ጥሪያችንን እናቀርባለን። 

ከባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ጋር የምናደርጋቸውን ቀጣይነት ያላቸው ውይይቶችን ከሕጋዊ እና ይፋዊ የመፍትሔ አማራጮች የምናስቀድም ቢሆንም፣ ሁሉንም የመፍትሔ አማራጮች እግዱ እስከሚነሳ ድረስ ህጉን ተከትለን ሁሉንም አስፈላጊ ጥረቶች ማድረጋችንን እንደምንቀጥል ልናሳውቃችሁ እንወዳለን። በሒደቱም እያንዳንዱን ሁኔታ በይፋ በማሳወቅ፣ በግልጽነት መረጃዎችን የምናደርሳችሁ ይሆናል። 

ድርጅታችን ካርድ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር እና ዲሞክራሲያዊ ባሕል ግንባታ ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ንቁ የሲቪክ፣ የሚዲያ እና ዲጂታል ምኅዳር ዕድገት እንዲመጣ ለማድረግ የተቋቋመለትን ተልዕኮ በድጋሚ እያረጋገጠ ለእግዱ መነሳት በምንሠራበት ጊዜ የእናንተ ድጋፍ እና ማበረታቻ እንደማይለየን በማመን ከልብ እናመሰግናለን።

የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)

For English version click here

 

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.