ሁለት እግሮቹን በእስር ወቅት ያጣው ከፍያለው ተፈራ

ጸሐፊ፡- በላይ ማናዬ

ከፍያለው ተፈራ ደረሰ ይባላል፡፡ 33 ዓመቱ ነው፡፡ ወለጋ፣ ሆሮ ጉድሩ ነው የተወለደው፡፡ አሁን የሚኖረው ኦሮሚያ ክልል፣ ፊንፊኔ ዙርያ ሰበታ ወረዳ ወለቴ 03 ነው፡፡ ከ1999 ጀምሮ ለ12 ዓመታት እስር ቤት ቆይቶ ሰኔ 16/2010 ነው የተፈታው፡፡ ማዕከላዊ፣ ቃሊቲ እና ቂሊንጦ እስር ቤቶች በእስር ቆይቷል፡፡

 

ማዕከላዊ

– አካላዊ ማሰቃየት

– ያለፍርድ እስር

– የጤና አገልግሎት ክልከላ

ከፍያለው መስከረም 03/1999 ከሦስት ጓደኞቹ ጋር ከወለቴ ወደ አዲስ አበባ እየሔደ ባለበት ካራ ቆሬ ላይ ተኩስ ተከፍቶባቸው መያዛቸውን ይናገራል፡፡ በወቅቱ ሦስት ሰዎች ሲገደሉ፣ እሱ ጉልበቱ እና ቁርጭምጭሚቱ ላይ በጥይት ቆስሎ በቀጥታ ፖሊስ ሆስፒታል ነበር የተወሰደው፡፡ ፖሊስ ሆስፒታል ከማንም ጋር ሳይገናኝ አንድ ወር ቆይቷል፡፡ ቁርጭምጭሚቱ ላይ የቆሰለውን እግሩን ጉልበቱ ላይ፣ እንዲሁም ጉልበቱ ላይ የቆሰለውን ጭኑ ላይ ያለ ፍቃዱ እና ሳያውቅ አደንዝዘው ቆርጠውታል፡፡ ጉዳቱ እግሮቹን ለመቆረጥ የሚያበቃ እንዳልነበረ ከፍያለው ይናገራል፡፡

የ33 ዓመቱ ከፍያለው ተፈራ የሐዋሳ ዩንቨርስቲ የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ሳለ ነበር የታሰረው፡፡ በ2010 ሲፈታ ትምህርቱ ተቋርጧል፡፡ እግሮቹን አጥቷል፡፡ ጤንነቱ ተቃውሷል፡፡

ከፍያለው ቁስሉ ሳይድን ነበር ወደ ማዕከላዊ (የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል) የተወሰደው፡፡ ማዕከላዊ ሲገባ ልብሱ እና አካሉ ሁሉ በደም የጨቀየ እንደነበር ያስታውሳል፡፡ “ማዕከላዊ መጀመሪያ የመረመረኝ ግርማ ካሳ (ኮሚሽነር) ነበር፡፡ ትንሽ ካነጋገረኝ በኋላ ጓዶቹን ‹በደንብ ሻወር አስወስዱት!› ብሏቸው ትቶኝ ወጣ፡፡ ለካ በእነሱ ቋንቋ ‹ሻወር አስወስዱት!› ማለት ግረፉት ማለት ኖሯል፡፡ የግርማን ትዕዛዝ የተቀበሉት ተከታይ መርማሪዎች እጅግ የከፋ ድብደባ ፈፅመውብኛል፡፡ እጆቼን አስረው ግድግዳ ላይ በመስቀል የተቆረጡ እግሮቼን ቁስል በብረት እየነኩ አሰቃይተውኛል፡፡ ኦ.ነ.ግ. መጥቶ ያድንህ እያሉ ይደበድቡኝ ነበር፡፡ ጆሮዎቼን በሁለት የእጅ መዳፎቻቸው በአንዴ ግጥም አድርገው እየመቱ ጉዳት አድርሰውብኛል፡፡ ከወንበር ጋር አስረው በዱላ፣ በቦክስ፣ በገመድ፣ ባገኙት ነገር ሁሉ ደብድበውኛል፡፡”

“መርማሪዎቹ ሌሊት ሰክረው እየገቡ ይደበድቡኝ ነበር” ይላል ከፍያለው፡፡ “ድብደባው ለ7 ወራት ሳያቋርጥ ተፈፅሞብኛል፡፡ ጨለማ ቤት ውስጥ ብቻየን ነበር ያሰሩኝ፡፡ ብዙ ጊዜ በቀላሉ ለመንቀሳቀስ ስለመልችል ባለሁበት ክፍል እየመጡ ነበር የሚያሰቃዩኝ፡፡ አንዳንዴ በጨለማ፣ በሽፍን መኪና ወደ ማላውቀው ቦታ ወስደው ሊገድሉኝ እንደሚችሉ ይዝቱብኛል፣ ያስፈራሩኛል፡፡ ገደል አፋፍ እያስጠጉ፣ ገደል ውስጥ ሊወረውሩኝ እንደሆነ እየዛቱ አስፈራርተውኛል፡፡”

ከፍያለው በምርመራ ወቅት ራሱን ደጋግሞ ይስት እንደነበር ይናገራል፡፡ በምርመራ ማሰቃየቱ የሞቱ ሰዎችን ያውቃል፡፡ ከፍያለው ራሱን ሲስት እንዳይሞትባቸው ፋታ ይሰጡት እንደ ነበር ያስታውሳል፡፡ ታዲያ “እንደዛ ተጎድቼ ህክምና ማግኘት አይፈቀድልኝም” ይላል፡፡

ፍ/ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበው ከታሰረ 7 ወር በኋላ ነበር፡፡ ቤተሰብም ሆነ የሕግ ባለሙያ ማየት አልተፈቀደለትም ነበር፡፡ ልብስ የቀየረው ከወራት በኋላ ነበር፡፡ “በደም የጨቀየ ልብስ ነበር እላየ ላይ ለወራት የቆየው” ይላል፡፡ “የፀሐይ ብርሃን አላገኝም ነበር፤ በዚህ ምክንያት ሰውነቴ ቢጫ ሆኖ ነበር፡፡ ሽንት ቤት አይወስዱኝም ነበር፣ በታሰርከበት ክፍል እንድፀዳዳ እገደድ ነበር፡፡ ሲወስዱኝም እንደ እቃ ነበር ሽንት ቤቱ ውስጥ እጅ እና እጄን ይዘው ነበር የሚወረውሩኝ፡፡ ስምንት ወር ሙሉ ሰውነቴን አልታጠብሁም ነበር፡፡ ፀያፍ ስድብ፣ ዛቻ እና ማስፈራሪያ የየዕለት ተግባራቸው ነበር፡፡”

 

ቃሊቲ እስር ቤት

– ከቤተሰብ ጋር መገናኘት መከልከል

– ከጠበቃ ጋር መገናኘት መከልከል

– ሕክምና መከልከል

ከፍያለው መደበኛ ክስ ተመሥርቶበት ከማዕከላዊ ከወጣ በኋላ ወደ ቃሊቲ እስር ቤት ነበር የተዛወረው፡፡ ከቤተሰቡ ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተያየው ቃሊቲ ሲገባ ነበር፡፡ ወደ አንድ ዓመት አካባቢ ቤተሰቦቹን አላገኘም ነበር፡፡ ቃሊቲ እስር ቤት ከገባ በኋላም ቢሆን ስቃዩ ቀጥሏል፡፡ 2 ዓመት ከ6 ወር ጨለማ ቤት አስረውታል፡፡ መጀመሪያ አካባቢ ቤተሰብ ይጠይቁት የነበረ ቢሆንም መልሰው ለረጂም ጊዜ እንዳይጠየቅ ተከለከለ፡፡ ፍ/ቤት አቤቱታ ቢያቀርብም ሰሚ አልነበረም፡፡ እንዲያውም ጉዳዩን የሚከታተልለትን ጠበቃ እያስፈራሩ ሥራውን እንዳይሠራ አድርገውት እንደ ነበር ከፍያለው ይናገራል፡፡ “በዚህ ጨለማ ቤት በታሰርኩበት ጊዜ ሁሉ ሕክምናም ተከልክዬ ነበር፡፡ አካል ጉዳተኛ ስለሆንሁ መፀዳጃ ቤት ለመጠቀም የሚያንቀሳቅሰኝ ሰው አልነበረም፤ ስለዚህም ወለል ላይ እንድፀዳዳ እገደዳለሁ፡፡ በዚህ ስቃይ ላይ ሆኜ ፍ/ቤት አመላልሰው ያለማስረጃ ዕድሜ ልክ ነበር የፈረዱብኝ፡፡”

 

ቂሊንጦ እስር ቤት

ከፍያለው የቂሊንጦ ቆይታውን እንዲህ ያስታውሰዋል፡- “ቂሊንጦ አዛውረው ሁለት ዓመት አስረውኛል፡፡ ቂሊንጦ በነበርሁበት ጊዜ በቂ ምግብ አልነበረም፡፡ በመጠን ትንሽ ዳቦ ነበር የሚሰጡኝ፡፡ አካሌን ስላጎደሉት ለእኔ ሁሉም እስር ቤት ስቃይ ነበር፡፡ ህክምና ቂሊንጦም አላገኘሁም፡፡ የቤተሰብ ጥየቃ ገደብም ነበረብኝ፡፡”

 

ሕይወት ከእስር በኋላ

ከፍያለው “ሕዝብ ታግሎ ከእስር አስፈትቶኛል” ይላል፡፡ “ሙሉ አካል የነበረኝ ሰው ነበርኩ፤ በተፈፀመብኝ ግፍ ሁለት እግሮቼን አጥቻለሁ፡፡ አሁን በአርቲፊሻል እግር ነው የምታገዘው፡፡ ሆኖም አርቲፊሻል ማቴሪያሉ ችግር አለበት፡፡ ምቾት ስለሌለው ያመኛል፡፡ አርቲፊሻል እግር በግሌ የገዛሁት ነው፡፡ ጆሮዬ ይደማል፤ ሕክምና ያስፈልገኛል፡፡ ጭንቅላቴን ያመኛል፡፡ ብዙ ጉዳት ነው ያለብኝ” በማለት ሕይወት ከእስር በኋላ እንደከበደበት ይገልጻል፡፡

ከፍያለው ለተፈፀመበት ግፍ ምንም ዓይነት የገንዘብም ሆነ የሞራል ካሣ አላገኘም፡፡ “ሕዝብ ታግሎ አስፈትቶኛል፣ አይዞህም ይለኛል፡፡ በመንግስት በኩል ግን ምንም ካሳ አልተደረገልኝም” ብሏል፡፡ “ይህን ግፍ የፈፀሙብኝ አካላት አሁንም ሥልጣን ላይ ናቸው፡፡ በፈፃሚዎቹ ላይ የተወሰደ የሕግ ተጠያቂነት የለም፡፡”

ከፍያለው በታሰረበት ወቅት በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ ዓመት የእፅዋት ሳይንስ ተማሪ ነበር፡፡ ትምህርቱ በእስሩ ተቋርጦ ቀርቷል፡፡ “አባቴ ሁለት እግሮቼ ተቆርጠው ሲያየኝ ደንግጦ ነው የሞተው፡፡ ወንድሜን አስረው አሰቃይተው ጎድተውታል፡፡ እህቴን ለምን ለመጠየቅ እስር ቤት ድረስ ትመጫለሽ በሚል በተደጋጋሚ አስፈራርተዋታል” በማለት ችግሩ ከራሱ አልፎ ቤተሰቡን ማዳረሱን ተናግሯል፡፡ “ለዚህ ሁሉ ለተመሰቃቀለው ሕይወቴ ምንም የጉዳት ካሳ የለም፤ ተጠያቂ የሆነ ባለሥልጣንም የለም፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *