ለብሄረሰብ ተኮር ጥቃቶችና ግጭቶች መፍትሄ ይሰጥ – የሰመጉ 143ኛ መግለጫ

የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ሰመጉ) በኢትዮጵያ ለብሄረሰብ ተኮር ጥቃቶችና ግችቶች የማያዳግም የፖሊሲና የአፈጻጸም እርምጃ እንዲወሰድ የሚያሳስብ ልዩ መግለጫ ጥቅምት 24/2010 ዓ.ም አውጥቷል፡፡ ሰመጉ በዚሁ በ143ኛ ልዩ መግለጫው በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ጌዲኦ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች እና በሐረር ከተማ ውስጥ እየተፈጸሙ ያሉ የተለያዩ የመብቶች ጥሰት በአስቸኳይ እንዲቆም አሳስቧል፡፡

ሰመጉ ከአሁን ቀደምም ብሄር ተኮር ግችቶችና ጥቃቶች እንዲቆሙ በተለያዩ መግለጫዎቹ ተመሳሳይ ማሳሰቢያዎችን ሲያሰማ ቢቆይም በቂ ትኩረት ባለማግኘቱ እና ተግባራዊ ምላሽ ባለመሰጠቱ ጥቃቱና ግጭቱ ስለመቀጠሉ በዚሁ በ143ኛ ልዩ መግለጫው አመልክቷል፡፡

በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ጌዲኦ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች ብሄር ተኮር የሆነ የከፋ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ከመስከረም 27-28/2009 ዓ.ም እንደተፈጸመ ሰመጉ በ143ኛ ልዩ መግለጫው በዝርዝር አስፍሯል፡፡ በዞኑ ይርጋጨፌ፣ ኮቸሬ፣ ዲላ፣ ወናጎ፣ ፍስሃገነት፣ ጨለለቅቱና ዙሪያው የመብት ጥሰቱ መፈጸሙን ሰመጉ አረጋግጧል፡፡

በዚህም መንግስት ለዜጎች በቂ ጥበቃ ባለማድረጉ ብሄር ተኮር በሆነ ጥቃት በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ጌዲኦ ዞን 31 ሰዎች ተገድለዋል፤ 101 ሰዎች ቆስለዋል፤ ብዙዎች ተፈናቅለዋል፤ የበርካታ ንጹሃን ዜጎች ንብረትም ወድሟል፡፡

ከጥቃቱ ጋር በተገናኘ እጃቸው አለበት የተባሉ በርካታ ሰዎች በጌዲኦ ዞን በእስር ላይ እንደሚገኙም ሰመጉ በሪፖርቱ አመልክቷል፡፡

ሰመጉ በዚሁ በ143ኛው ልዩ መግለጫው እንዳመለከተው በሐረሪ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሐረር ከተማ የተለያየ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ተፈጽሟል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሰኔ 30/2009 ዓ.ም በሐረር ከተማ የአፈረንቀሎ የኦሮሞ ባህል እና ታሪክ ማዕከል ለመገንባት በኦሮሚያ ክልል እና ሀረሪ ክልል ፕሬዚደንቶች እና ሌሎች ባለስልጣናትና ነዋሪዎች በተገኙበት የመሰረት ድንጋይ ሲጣል የኦሮሞ ባህል አልባሳትን ለብሰው ተቃውሞ ባሰሙ ዜጎች ላይ በሀረሪ ክልል ፖሊስ አባላት ህገ ወጥ እስራትና ድብደባን ጨምሮ ሌሎች የመብቶች ጥሰት መፈጸሙን ሰመጉ ገልጹዋል፡፡

ሰመጉ በሁሉም ቦታዎች ለተፈጸሙት የመብት ጥሰቶች ተገቢው ማጣራት ተደርጎ ጥሰት ፈጻሚዎች ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው በመጠየቅ፣ ተመሳሳይ ብሄር ተኮር ጥቃቶች እና ግጭቶችን ለማስቆም የአፈጻጸም እና የፖሊሲ እርምጃ እንዲወሰድ አሳስቧል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *