ማንደፍሮ አካልነው፤ “ሚዲያ ስላወቀ እንጂ ሕይወትህ አትተርፍም ነበር ብለውኛል”

ጸሐፊ፡- በላይ ማናዬ

በዓለም ዐቀፍ የቱሪስት መስህቧ ላሊበላ ከተማ ተወልዶ ያደገው ማንደፍሮ አካልነው፣ ከላሊበላ ተነስቶ ማዕከላዊ፣ ቃሊቲ፣ ቂሊንጦ እና ዝዋይ እስር ቤቶችን አዳርሷል፡፡ የ31 ዓመቱ ማንደፍሮ አካልነው ከስድስት ዓመታት በላይ እስር ቤት አሳልፏል፡፡ ‹ውጭ ሀገር ሆነው ነፍጥ አንስተው ኢትዮጵያን ከሚያተራምሱ ኃይሎች ጋር ግንኙነት አለህ› በሚል ግንቦት 17 ቀን 2003 ከሚኖርበት ላሊበላ ከተማ በፌደራል ፀረ-ሽብርተኝነት ግብረ ኃይል አባላት ተይዞ ታስሮ በ2010 ነው ከእስር ግዜው ላይ አመክሮ ተቀንሶለት የተፈታው፡፡ አንድ ቀን ላሊበላ የሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ እንዲያድር ከተደረገ በኋላ፣ በማግስቱ ወደ አዲስ አበባ ተጓጉዟል፡፡

 

ማንደፍሮ አካልነው ከላሊበላ ተነስቶ ማዕከላዊ፣ ቃሊቲ፣ ቂሊንጦ እና ዝዋይ እስር ቤቶችን አዳርሷል፡፡

ማዕከላዊ

አካላዊ እና ሥነ ልቦናዬ ማሰቃየት

– እንቅልፍ መንፈግ

– ቤተሰብ ጉብኝት ክልከላ

የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) የነበረው ምርመራ በዋናነት ከኤርትራ መንግሥት ጋር ግንኙነት በማድረግ አገር አሸብረሃል በሚል ማሰቃየት እንደነበር ማንደፍሮ ይናገራል፡፡ “ማን እንደመለመለህና ማንን መልምለህ ኤርትራ እንደላክህ ተናገር በሚል ብዙ በደል አድርሰውብኛል፡፡ ድብደባ፣ ስድብና ዛቻ በየዕለቱ ይፈጽሙብኝ ነበር፡፡ አንድ ጥርሴን በድብደባ አውልቀውብኛል፡፡ ሚዲያ ስላወቀ እንጂ ሕይወትህ አትተርፍም ነበር እያሉ ዝተውብኛል፡፡ የወጣሁበትን ማኅበረሰብ እየጠሩ ማንነቴን መሠረት አድርገው ይሰድቡኝ፣ ያንቋሽሹኝ ነበር፡፡ አካላቸው ሲታይ ትልልቅ ሰዎች ናቸው፤ ስድባቸው ግን ከእነሱ የሚወጣ አይመስልም፡፡”

ማንደፍሮ የማዕከላዊ መርማሪዎች ከወንበር ጋር አስረው ፊቱ ላይ ምራቃቸውን ይተፉበት እንደነበር ይናገራል፡፡ ምርመራ የሚደረግበት ሌሊት ሌሊት ነበር፡፡ “በኤሌክትሪክ ገመድ ገርፈውኛል፡፡ በከስክስ ጫማ በተደጋጋሚ ረግጠውኛል፡፡ በጥፊ፣ በቦክስ መትተውኛል፡፡ ጨለማ ክፍል አቆይተውኛል፤ ውኃ በሚያንጠባጥብ ስፍራ አስረው እንቅልፍ እንዳልተኛ አድርገውኛል፡፡ ከመሬት በታች በሚገኝ ክፍልም ብቻዬን አስረውኝ ነበር፡፡”

ማንደፍሮ በማዕከላዊ ቆይታው ቤተሰቦቹ እንዳይጠይቁት ተከልክሎ ነበር፡፡ በማዕከላዊ ለ33 ቀናት ሲሰቃይ ቆይቶበት ነበር፡፡ “ድበደባው የቆመው ራሳቸው ጽፈው ባመጡት ወረቀት ላይ አስገድደው ካስፈረሙኝ በኋላ ነበር” ይላል፡፡

 

“አሸበሪ ነው፣ እንዳትጠጉት”

ማንደፍሮ የሽብርተኝነት ክስ ከተመሰረተበት በኋላ ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተዛውሯል፡፡ ቃሊቲ ለአንድ ዓመት ቆይቷል፡፡ በዚህ ጊዜ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች በሽብርተኝነት የተጠረጠረ መሆኑን በመጥቀስ በሌላ ክስ የታሰሩ ሰዎች እንዳይቀርቡት እያስጠነቀቁ መገለል ያደርሱበት እንደነበር ይናገራል፡፡ ሌሎቹን እስረኞች “ይህ አረመኔ አሸባሪ ስለሆነ እንዳትጠጉት” ይሏቸው ይላል፡፡ “ክብረ ነክ ስድብ ይሰድቡኝ ነበር፡፡ በተለይ ፍ/ቤት አንድ ነገር በአቤቱታ መልክ ከተናገርሁ ወደ እስር ቤት ስመለስ ስድባቸው ከባድ ነበር፡፡ ዛቻም አድርሰውብኛል፡፡ ሕክምና ከልክለውኛል” በሚል ነው የቃሊቲ ቆይታውን የሚያስታውሰው፡፡

 

ቂሊንጦ እስር ቤት

ቂሊንጦ የሚገኘው እስር ቤት ከተሠራ በኋላ ማንደፍሮ ከቃሊቲ ወደ ቂሊንጦ ተዛውሯል፡፡ ማንደፍሮ በቂሊንጦም “ሕክምና እንዳላገኝ ተደርጌያለሁ” ይላል፡፡ “ከፍተኛ የሕመም ስቃይ ላይ ሆኜ እያለ ‹ለአሸባሪ ሕክምና አንሰጥም› በሚል ከልክለውኝ ነበር፡፡ ሕመሙ ሲበረታብኝ የተመለከቱ እስረኞች የርሃብ አድማ እናደርጋለን በሚል ታግለው ነው ሕክምና በመጨረሻ ያገኘሁት፡፡ ቂሊንጦ እስር ቤት መጽሐፍ እንዳላነብ፣ ለእስረኞች በተዘጋጀ ካፌ እንዳልጠቀም ከልክለውኛል፡፡” ማንደፍሮ በቂሊንጦ እስር ቤት አንድ ዓመት ከቆየ በኋላ ወደ ዝዋይ እስር ቤት ተዛውሯል፡፡

ዝዋይ – ራኢሮ

ላሊበላ ከተማ ላይ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋለው ማንደፍሮ ቃሊቲ እና ቂሊንጦ ቆይቶ በመጨረሻ ወደ ዝዋይ ከፍተኛ ጥበቃ የፌደራል ማረሚያ ቤት ተዛውሯል፡፡ እዚያ ብዙ የመብቶች ጥሰቶች እንደተፈፀሙበት ይናገራል፡፡

ማንደፍሮ ራኢሮ የሚባል ጨለማ ቤት ታስሮ ቆይቷል፡፡ “ራኢሮ ለአንድ ሰው ብቻ የተዘጋጀች ክፍል ውስጥ አስረውኛል፤ እዚች ክፍል ውስጥ እግሬን ዘርግቼ ማረፍ አልችልም ነበር፡፡ በጣም ጠባብ፣ ሙቀት የበረታባትና ጨለማ ክፍል ናት – ራኢሮ፡፡ ከዚህ ክፍል ስወጣም ጨለማ ቤት ተብሎ የሚጠራ ሌላ ክፍል ውስጥ አሰሩኝ፡፡ ይህኛው ክፍል ሌላ ሰውም ስለነበረበት ይሻላል፡፡ የተከሰስኩበትን የክስ ዓይነት እያዩ፣ ‹አንተኮ ወንጀልህ ሽብር ነው፣ ዛሬም የተከልኸው እሾህ እንዳለ ነው› እያሉ ህዝብ ተቃውሞ ባነሳ ቁጥር ያሰቃዩኝ ነበር፡፡

“ዝዋይ በዚህ አስቸጋሪ አያያዝ ምክንያት በጠና ታምሜያለሁ፡፡ ኩላሊቴን፣ ልቤን አመመኝ፡፡ በቂ ሕክምና ሳላገኝ ቆየሁ፡፡

ማንደፍሮ ዝዋይ እስር ቤት ሳለ ጊዜው ያለፈበት መድኃኒት ስለተሰጠው ቆዳው ተቆጥቶ መላላጡን ይናገራል፡፡

ከብዙ ስቃይ በኋላ ሕክምና ወስደውኝ ነበር፤ ጊዜው ያለፈበት መድኃኒት ሰጥተውኝ ተጨማሪ ስቃይ ደረሰብኝ፡፡ መድኃኒቱን በመውሰዴ ምክንያት ሙሉ የሰውነቴ ቆዳ ተላላጠ፡፡ እስረኞች ሁሉ እስኪደነግጡ ቆዳዬ ተላልጦ አለቀ፡፡ አሁን ያለው ሰውነቴ አዲስ ቆዳ ነው፡፡” በዚህ ሁኔታ ዝዋይ አምስት ዓመት ቆይቶ የእስር ጊዜዬን በአመክሮ ጨርሶ ጥር 2010 በፍቺ ተሰናብቷል፡፡

ማንደፍሮ በእስር ቤቶች በደረሰበት ስቃይ ዛሬም ድረስ ልቡ እና ኩላሊቱን እንደሚያመው ይናገራል፡፡ ትንሽ መንገድ በመኪና ሲሔድና፣ ረጂም ሰዓት ሲቀመጥ እግሮቹ ያብጣሉ፡፡ በአቅም ማነስ ምክንያት በቂ ሕክምና ሊያገኝ አልቻለም፡፡ ከእስር ከወጣ በኋላ ለወራት ያህል ጥሩ እቅልፍ መተኛት አይችልም ነበር፡፡ በእስር ቤት ያሳለፈው ስቃይ በአእምሮው እየተመላለሰ እንደሚረብሸው ደጋግሞ ይናገራል፡፡

“እስር ቤት ሳለሁ ለተፈጸመብኝ በደል ምንም ዓይነት ካሣ አልተደረገልኝም” ይላል፡፡ ምንም እንኳን የፖለቲካው ሁኔታ ቢለወጥም በዚህ ጉዳይ ማንደፍሮን ያነጋገረው የመንግሥት አካልም የለም፡፡ ይሁን እንጂ “አጠያይቄ እንደተረዳሁት፣ በደል ያደረሱብኝ ሰዎች አሁንም በሥራቸው ላይ ናቸው” ይላል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *