ስለ ካርድ

የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ሴንተር ፎር አድቫንስመንት ኦፍ ራይትስ ኤንድ ዴሞክራሲ /ካርድ/) ቦርድ-መር፣ ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ 113/2011 መሠረት፣ በመዝገብ ቁጥር 4307፣ ሐምሌ 17፣ 2011 ሕጋዊ ሰውነት ያገኘ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ነው።

​ካርድ በሰብዓዊ መብቶች እሴቶች ላይ የቆመ ዴሞክራሲያዊ ባሕል ያበበባት ኢትዮጵያን ማየት ራዕይ አድርጎ ሰንቆ፥ የኢትዮጵያ ዜጎች እና የዜጎች ማኅበራት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር በመሟገት ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲያሰፍኑ የሚያስችላቸውን የአቅም ግንባታ ማድረግ ተልዕኮ በማንገብ እየሠራ የሚገኝ ድርጅት ነው።

ዴሞክራሲን በኢትዮጵያ
ብቸኛው የጫወታ ሕግ ማድረግ!

ካርድ ሰብዓዊ መብቶች እና ዴሞክራሲያዊ ባሕል ያላቸውና በሰብዓዊ መብቶች እሴቶች የሚመሩ ሕዝባዊ ንቅናቄዎችን ለመገንባት የግንዛቤ ማስጨበጥ፣ ሲቪል ተቋማትን ማደራጀት፣ እና የፖሊሲ መሻሽሎችን ማግባባት ሥራዎችን ይሠራል።  

የካርድ ራዕይ

​በሰብዓዊ መብቶች እሴቶች ላይ የቆመ ዴሞክራሲያዊ ባሕል ያበበባት ኢትዮጵያን ማየት።

የካርድ ተልዕኮ

የኢትዮጵያ ዜጎች እና የዜጎች ማኅበራት ለሰብዓዊ መብቶች መከበር በመሟገት ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እንዲያሰፍኑ የሚያስችላቸውን የአቅም ግንባታ ማድረግ

የካርድ አንኳር ዓላማዎች

ካርድ፣ በሕግ በተመዘገበለት አግባብ መሠረት የሚከተሉትን ዓላማዎች አንግቧል፦

 • በኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ባሕል እንዲያብብ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት
 • የሰብዓዊ መብቶች እና የዴሞክራሲ ዕድገት ደረጃን በመከታተል እና በመገምገም መንግሥታዊ የሆኑ እና መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ተጠያቂነት እንዲያዳብሩ ማድረግ
 • የዴሞክራሲ ግንባታን ለማገዝ የሚያስችሉ ተፅዕኖዎችን ለማድረግ የምርምር ሥራዎችን መሥራት፣ የምክክር መድረኮችን ማዘጋጀት፣ እና የማግባባት ሥራዎችን መሥራት
 • ለዴሞክራሲ ተቋማት ቴክኒካዊ እና ሙያዊ ድጋፍ መስጠት
 • ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበራቸውን ለማረጋገጥ የፖሊስ ማቆያዎችን፣ የማረሚያ ቤቶችን አያያዝ እና የፍርድ ቤቶችን ሒደት መከታተል እና መገምገም
 • ምርጫዎችን መታዘብ፣ የዜግነት እና የመራጮች ትምህርት መስጠት

መርሓ ግብሮች

ካርድ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲ ለመገንባት መብት-ተኮር የሆነ አካሔድ ይከተላል። በዚህም መሠረት የተቀረፁ አምስት መርሓ ግብሮች አሉት።

 1. የዜግነት ተሳትፎ

ይህ መርሓ ግብር ብዝኃነት የተላበሱ የሰብዓዊ መብቶች እና ዴሞክራሲያዊ ጉዳዮች ላይ ዜጎች ተሳትፎ የሚያደርጉባቸው ተቋማት እና መድረኮች እንዲፈጠሩ ለማስቻል ያለመ ነው። በዚህ መርሓ ግብር ውስጥ ያሉት ፕሮግራሞች እና ተግባራት የሚከተሉት ናቸው።  

 • መደበኛ፣ ኢ-መደበኛ፣ እንዲሁም ልማዳዊ የሆኑ ቡድኖች ንቅናቄዎቻቸውን ተቋማዊ እንዲያደርጉ የማብቃት ሥራ መሥራት
 • አዳዲስ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን ሰብዓዊና ቁሳዊ አቅም ግንባታ በማድረግ የተፅዕኖ አቅማቸውን ማጎልበት
 • ተከታታይ በይነ-ቡድናዊ ወይም የእርስ በርስ የውይይት መድረኮችን በተለያዩ አነጋጋሪ ማኅበረፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በማመቻቸት መግባባት መፍጠር
 • የግጭት መንስዔዎችን በመመርመር ለሁሉን አካታች መፍትሔ ማመቻቸት

2. የሚዲያ አረዳድ ክኅሎት

ይህ መርሓ ግብር የዴሞክራሲ ባሕልን ለመገንባት የብዙኃን መገናኛዎች አቅም እና ምኅዳር እንዲጎለብት ለማስቻል ያለመ ነው። በዚህ መርሓ ግብር ሥር ያሉ ፕሮጀክቶች እና ተግባራት የሚከተሉት ናቸው።

 • ሐሳብን የመግለጽ ነጻነትና የብዙኃን መገናኛዎች ምኅዳር እንዲሻሻል ግፊት ማድረግ
 • ለሙያዊ ጋዜጠኝነት መጎልበት የጋዜጠኞችን ደኅንነት እና ነጻነት መጠበቅ እና መከላከል
 • በመደበኛ እና ኢመደበኛ መድረኮች የሚስተዋሉ ትርክቶችን፣ የተዛቡ መረጃዎችን፣ የጥላቻ ንግግሮችን መከታተል እና የተዋስዖ መድረኩ በሥነ ምግባር እንዲታገዝ የሚያስችሉ ሥራዎችን መሥራት
 • በመንግሥት በጀት የሚተዳደሩ ብዙኃን መገናኛዎች የተረጋገጠ እና ብዝኃነት ያለው የሐሳብ እና መረጃ ይዘት እንዲኖራቸው ማግባባት

3. የወጣቶች እና ሴቶች ማብቃት

ይህ መርሓ ግብር የብቃት ማሳደጊያ ዕድሎችን በማመቻቸት ወጣቶች እና ሴቶች በዜግነት ጉዳዮች ላይ ተሳትፏቸውን እንዲያሳድጉ ለማስቻል ያለመ ነው። በዚህ መርሓ ግብር ሥር ያሉ ፕሮጀክቶች እና ተግባራት የሚከተሉት ናቸው።

 • የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን እና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የሰብዓዊ መብቶች እሴቶች እና የዴሞክራሲ መርሖዎችን የሚያስተዋውቁ ሥልጠናዎች እንዲያገኙ በማድረግ ግንዛቤያቸውን ማሳደግ
 • የወጣቶች እና ሴቶችን አቅም በማጎልበት ዕውቀት መር ማኅበራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ የምርምር መድረኮችን መፍጠር
 • አካታችነት እና ብዝኃነትን የሚያበረታቱ የሰብዓዊ መብቶች ክብረ በዓላት እና ሴሚናሮችን፣ እንዲሁም የተለያዩ መደብ አቋራጭ የንግግር መድረኮችን ማዘጋጀት
 • የስርዓተ ፆታ መብቶችን እና የተገለሉ እና ተጋላጭ የማኅበረሰብ ክፍሎችን መብቶች ማሳደግ

4. የዲጂታል መብቶች

ይህ መርሓ ግብር የዲጂታል መብቶች እንዲከበሩ እና የበይነመረብ ተጠቃሚ ዜጎች ደኅንነት እንዲጠበቅ ያለመ ነው። በዚህ መርሓ ግብር ሥር ያሉ ፕሮጀክቶች እና ተግባራት የሚከተሉት ናቸው።

 • በማኅበረሰብ ክፍሎች ዘንድ ያለውን የዲጂታል ክፍፍል ለመቀነስ ነጻ እና ሁሉን አካታች የበይነመረብ ተዳራሽነት እንዲኖር ማግባባት
 • ሐሳብን የመግለጽ ነጻነት እና የመረጃ የማግኘት መብቶች በይነመረብ ላይ እንዲከበሩ መቆም
 • የግለሰቦች የበይነመረብ ዳታ፣ የግል ምሥጢር፣ እና ደኅንነት እንዲጠበቅ ማበረታታት
 • የበይነመረብ ኩባንያዎች አገራዊ እና ነባራዊ ዐውዶችን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓቶችን እንዲዘረጉ ድጋፍ መስጠት

5. የዴሞክራሲ ኢንዴክስ

ይህ መርሓ ግብር በኢትዮጵያ ያሉ ክልላዊ እና ፌዴራላዊ መስተዳድሮችን አሠራር በዴሞክራሲ መርሖዎች በመለካት ተከታታይ የሆነ መግለጫ በማውጣት የዴሞክራሲ ሒደት እንዲሻሻል ለማገዝ ያለመ ነው። ይህ መርሓ ግብር ያሉት ፕሮጀክቶች እና ተግባራት የሚከተሉት ናቸው።

 • ክልሎች እና ፌዴራላዊ አስተዳደሮችን በየዓመቱ በሚደረግ የዴሞክራሲያዊ መርሖዎች መመዘኛ እና ደረጃ አሰጣጥ ስርዓት የዴሞክራሲያዊነት ሒደትን መገምገምና አስተዳደሮች እርስ በርሳቸው እንዲሁም ከራሳቸው ያለፉ ዓመታት ተሞክሮ ጋር ጤናማ ፉክክር እንዲያደርጉ ማስቻል
 • በምርምር የታገዘ መረጃ የመስተዳድሮችን ጥንካሬ እና ደካማ ጎን በማደራጀት ባለድርሻ አካላት ሊሠሩባቸው የሚገቧቸውን የትኩረት አቅጣጫዎች በቀላሉ እንዲለዩ ማገዝ
 • በዴሞክራሲ ዕድገቱ ተመሥርቶ ሒደቶችን በመመልከትና የፖሊሲ ሐሳቦችን በመቅረፅ  አዎንታዊ መሻሽሎች እንዲደረጉ መወትወት

አካሔድ እና ተደራሲዎች

ካርድ መርሓ ግብሮቹን እና ተግባራቱን የሚያከናውንባቸው አካሔዶች ዕውቀት ከመፍጠር ተነስተው፣ በተገኘው ዕውቀት መሠረት ዜጎችን የሚያሳትፉ ተግባራትን በመቅረፅ ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። ተግባራቱ ግንዛቤ ከማስጨበጥ የፖሊሲ ለውጦች እንዲደረጉ እስከማግባባት የሚዘልቁ ናቸው። ግንዛቤ የማስጨበጡም ይሁን ለፖሊሲ ለውጥ ማግባባቱ በባለሙያዎች የተጋዘ ከመሆኑም ባሻገር ባለድርሻ አካላቱን እና ተደራሲያኑን ያሳትፋል። ተግባራቶቻችን ዕውቀት መር ብቻ ሳይሆኑ መብቶች ተኮርም በመሆናቸው የተለያዩ መብቶችን በማሳደግ ሰላማዊ እና በንግግር የሚያምን ማኅበረሰብ በመፍጠር ዴሞክራሲን ማሳደግ ይቻላል የሚል ፍልስፍና አላቸው። በሥራዎቻችን ተደራሲ የምናደርጋቸው የማኅብረሰብ ክፍሎች በተለይ የሚከተሉት ናቸው።

 1. መደበኛ እና መደበኛ ያልሆኑ የወጣቶች ቡድኖች
 2. ወጣት አመራሮች፣ የማኅበራዊ ንቅናቄ አስተባባሪዎች፣ እና የመብት ተሟጋቾች
 3. ትውፊታዊ እና ልማዳዊ ተቋማት
 4. ብዙኃን መገናኛዎች፣ ጋዜጠኞች እና ጦማሪዎች
 5. የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶች
 6. ሕዝባዊ የዴሞክራሲ ተቋማት
 7. የበይነመረብ አውታሮች እና የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች