“በሥም ማጥፋት” ሰበብ የሚፈፀም እስር

ይህ ዓመት በነጻው ፕሬስ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስትያን (ኢ.ኦ.ቤ.ክ) መካከል የተደረጉ ሁለት ታዋቂ የፍርድ ቤት ሙግቶች የተቋጩበት ዓመት ነው፡፡ የመጀመሪያው ፕሬስን በተመለከተ ከኢትዮጵያ የፍትሕ ስርዓት ያልተለመደ ፍትሕ የተገኘበት ነበር፤ ሁለተኛው ፍትሕ አላግባብ ከፕሬሱ ተነፍጎ፣ ለኢ.ኦ.ቤ.ክ. የተሸለመት ነበር፡፡

የመጀመሪያው፣ በዳንኤል ክብረት የተጻፈ እና ሙሉ ለሙሉ ሊባል በሚችል መልኩ የኢ.ኦ.ቤ.ክ. ፓትርያርክ ቤተ ክርስትያኗ ውስጥ እየተፈፀመ ያለውን ሙስና እያዩ በዝምታ አልፈዋል በሚል የሚወቅስ ሒሳዊ አስተያየት ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ በኢ.ኦ.ቤ.ክ. መንበረ ፓትርያርክ፣ ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስትያን ውስጥ እየተፈፀመ ነው በሚል በቤተ ክርስትያኗ ምዕመን እና ካሕናት የቀረበ አቤቱታ ላይ ተመሥርቶ የተጻፈ ዜና ነው፡፡ (የጋዜጣው ዜና ከዚህ ጽሑፍ ስር ይገኛል፡፡)

ሒሳዊ አስተያየቱ በታዋቂው ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ተጽፎ ሳምንታዊው ሰንደቅ ጋዜጣ ላይ ነበር የታተመው፤ ሌላኛው ዜና ደግሞ ለተቃዋሚ ድምፆች ሰፊ ገጽ የምትሰጠው ኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣ ነበር የወጣው፡፡ የሰንደቅ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ፣ ፍሬው አበበ፣ ጥር 9/2009 የኢ.ኦ.ቤ.ክ ከመሠረተችበት “የሥም ማጥፋት” ክስ በነጻ ተሰናብቷል፡፡ የኢትዮ-ምኅዳር ዋና አዘጋጁ ጌታቸው ወርቁ ግን ኅዳር 15፣ 2009 በተመሳሳይ በኢ.ኦ.ቤ.ክ. ሥር የሚገኘው የቅድስት ማርያም ቤተ ክርስትያን አስተዳደር በመሠረተበት “የሥም ማጥፋት” ክስ “ጥፋተኛ” ተብሎ የአንድ ዓመት ቀላል እስራት እና የ1,500 ብር ቅጣት ተጥሎበታል፡፡ በተጨማሪም፣ ኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣ የ10,000 ብር ቅጣት ተበይኖባታል፡፡ ለግንቦት 25 ሰበር ችሎት ቀጠሮውን እየተጠባበቀም ይገኛል ፡፡ ሰንደቅ ጋዜጣን በተመለከተ፣ የተከሰሰው ዋና አዘጋጁ ብቻ ነበር፡፡ ኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣን በተመለከተ ግን ጋዜጣው እና ዋና አዘጋጁ – ሁለቱም – ተከሳሾች ሆነው በጥፋተኝነት ቅጣት ተላልፎባቸዋል፡፡

ፍሬው አበበ – በመከላከያ ሰነድነት ያቀረበው ከመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና ከጋዜጠኞች ኅብረት የተገኙ ደብዳቤዎችን ነው፡፡ አቶ ጌታቸው ረዳ (በወቅቱ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩ) እና ዶ/ር ነገሬ ሌንጮ (በወቅቱ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን ትምህርት ቤት ኃላፊ የነበሩ) ለቂርቆስ ክፍለ ከተማ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፍሬው አበበን የሚከላከሉ የተቋማቸው ማሕተም ያረፈባቸው ደብዳቤዎች ጽፈዋል፡፡ ሁለቱም ደብዳቤዎች ሰንደቅ ጋዜጣ ላይ የታተመው ሒሳዊ አስተያየት “ትችት ሊባል ከሚችል በስተቀር ሥም ማጥፋት እንዳልሆነ” አስረድተዋል፡፡ በተመሳሳይም፣ ለመንግሥት ወገንተኛ ነው ከሚባለው የኢትዮጵያ ብሔራዊ የጋዜጠኞች ኅብረት (ኢብጋኅ) ፕሬዚደንት አንተነህ አብርሃምም የመከላከያ ደብዳቤ ለጋዜጠኛ ፍሬው አበበ ተጽፎለታል፡፡ እነዚህ ደብዳቤዎች፣ ፍሬውን ከተመሠረተበት “የሥም ማጥፋት” ክሶች ነጻ እንዲወጣ ረድተውታል፡፡ መንግሥት ላይ ጠንካራ ትችት የሚያትመው ኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጌታቸው ወርቁ ግን እነዚህን የመሰሉ መከላከያ ደብዳቤዎች የሚጽፍለት ባለመኖሩ በአራዳ ክፍለ ከተማ የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት “ጥፋተኛ” ነህ ተብሏል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ጌታቸው ክሱን ለመከላከል የሚያስችሉ ሌሎች ማስረጃዎች አላቀረበም ማለት አይደለም፡፡ ጌታቸው ለዜና ምንጭ የሆነውን ደብዳቤ፣ እንዲሁም ቤተ ክርስትያኗ ውስጥ ሙስና እየተፈፀመ እንደሆነ ያስረዳልኛል ያለውን የሒሳብ ጉድለት የሚያሳይ የኦዲት ሪፖርት አቅርቦ ፍትሕ አላስገኘለትም፡፡ (የኦዲት ሪፖርቱ ኮፒ ከስር ተያይዟል፡፡)

ጌታቸው አራዳ የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ያሳለፈበትን ፍርድ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ይግባኝ ሰሚ አቅርቦት ነበር፡፡ ይግባኝ ሰሚው የሥር ፍ/ቤቱን ውሳኔ አፅድቆበታል፡፡ አሁን፣ ጠበቃው ይግባኙን መሠረታዊ የሕግ ጥሰቶችን ወደሚመረምረው የፌዴራል ሰበር ሰሚ ችሎት ወስደውታል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ እስካሁን ቀጠሮ አልቆረጠም፤ ጋዜጠኛ ጌታቸው ግን ከኅዳር 6 ጀመሮ የአንድ ዓመት ቅጣቱን እስር እያወራረደ ነው፡፡ ጌታቸው የታሰረው ቤተሰቦቹ ከሚኖሩበት አዲስ አበባ 200 ኪሜ ርቃ በምትገኘው ሸዋ ሮቢት ከተማ ነው፡፡ ጌታቸው ባለትዳር እና የአንድ ዓመት ሴት ልጅ አባት ሲሆን፣ ለቤተሰቡ የገንዘብ ገቢ ምንጭ ብቸኛ አምጭ ነበር፡፡

ሁለቱን ክሶች ማነፃፀር አስፈላጊ የሆነው በብዙ ምክንያቶች ነው – የክሶቹ መመሳሰል እና ሁለቱ ጋዜጦች የገጠማቸው የተለያዩ የፍርድ ውሳኔዎች ዋነኞቹ ምክንያቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለት ምክንያቶች የኢትዮጵያ ፕሬስ እና የፍትህ ስርአቱም  እንዴት እንደሚሠራ ጥሩ ተጨማሪ ማሳያ ይሆናሉ፡፡ በተጨማሪም፣ በንፅፅሩ “የሥም ማጥፋት” ክሶች እንዴት በቀላሉ ሊጠመዘዙ እንደሚችሉ ማሳያ ይሆነናል፡፡

ሰንደቅ ላለፉት ዐሥር ዓመታት የጎላ ችግር ሳይገጥመው አገልግሎት የሰጠ ሳምንታዊ ጋዜጣ ነው፡፡ ለገዢው ፓርቲ አመራሮች የቅርብ ወዳጅ በሆኑት፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊው የሳኡዲ ዜጋ ሼክ መሐመድ አላሙዲ የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚደረግለት ይገመታል፡፡ ኢትዮ-ምኅዳር፣ በሌላ በኩል፣ አምስት ዓመታት ለስርጭት ስትበቃ የዋና አዘጋጁን መታሰር እንኳን ተቋቁሞ መዝለቅ የሚያስችል የፋይናንስ አቅም አልገነባም ነበር፡፡ ኅዳር 6/2009፣ ጌታቸው ወርቁ በፍርድ ቤት “ጥፋተኛ” በተባለበት ወቅት፣ “የተፈረደብኝ ጋዜጣዋ እንድትቆም ስለተፈለገ ነው” በማለት ተናግሮ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ከደርዘን በላይ ጋዜጠኞችን እና ጦማሪዎችን ያሰረ ከመሆኑ አንፃር የጌታቸው ንግግር ለመቀበል የሚከብድ አይደለም፡፡ አሁን ኢትዮ-ምኅዳር ጋዜጣ ከስርጭት ወጥታለች፡፡ ለዚህ ደግሞ የፊት ለፊት ተወቃሽ እንዲሆን የተደረገው መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ነው፡፡ ጌታቸው፣ ለችሎቱ በተደጋጋሚ ‹የታሰረው ዜናውን የሰጠውን ሰው (ምንጩን) ተጠይቆ በሕግ አግባብ አልሰጥም ባይል ኖሮ እንደማይታሰር› ተናግሯል፤ “የሆኑ ሰዎች ቢሮዬ ድረስ መጥተው ዜናውን ማን እንደሰጠህ ንገረን አሉኝ፡፡ ማን እንደሆነ እንደማልነግራቸው፣ ነገር ግን መልስ ካላቸው ጋዜጣው ላይ እንደማትምላቸው አስረዳኋቸው፡፡ እነሱ ግን ‹ለዚህ ዋጋህን ታገኛለህ› ብለው ዝተውብኝ ሔዱ” ብሏል፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ ጋዜጣው ላይ ባተመው ነገር ችግር ውስጥ ሲገባ ይህ የመጀመሪያው አይደለም፡፡ ከአራት ዓመታት በፊት – በ2006 – ከባልደረባው ኤፍሬም በየነ ጋር ሐዋሳ ዩንቨርስቲ ውስጥ አለ ስለተባለ ሙስና ጋዜጣቸው ላይ ባተሙት ዜና “የሥም ማጥፋት” ክስ ተመሥርቶባቸው ነበር፡፡ ክሱን ለመከታተል ሐዋሳ ከተማ በሚመላለሱበት ጊዜ ጋዜጠኛ ኤፍሬም በደረሰበት ድንገተኛ በባጃጅ የመገጨት አደጋ ከፊል ሰውነቱ መንቀሳቅስ እንዳይችል ሆኗል፡፡ ጌታቸው እና ባልደረቦቹ፣ አደጋው በሙስና ፈፃሚዎቹ የተቀነባበረ ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡

የዚህ የቤተክርስትያኗ ክስ ሌላኛው አስቸጋሪ ገጽታ፣ የከሳሽ ምስክር ተብለው የቀረቡት ሰዎች ገለልተኝነት ነው፡፡ ከአንዱ ምስክር በስተቀር ሌሎቹ በሙሉ በሙስና የሚጠረጠረው የቤተ ክርስትያኑ አስተዳደር አባላት ናቸው፡፡ ምስክሮቹ ዝርዝር ውስጥ ገንዘብ ያዡ እና የግምጃ ቤት ኃላፊው ይገኛሉ፤ እነዚህ ደግሞ የተጠረጠረውን ሙስና መርተዋል የሚባሉት ሰዎች ናቸው፡፡

“የሥም ማጥፋት” ክስ አደገኝነት

የሥም ማጥፋት ክሶች ችግር ፈጣሪዎች እና ጸሐፊዎች ላይ ተዘዋዋሪ ሳንሱር የሚጥሉ ማዕቀቦች ናቸው፡፡ በሁለቱ ክሶች ከላይ ለማሳየት እንደጣርነው፣ “የሥም ማጥፋት” ክሶች አደገኛነት የሚገለጠው በቀላሉ ሊጠመዘዙ የሚችሉ በመሆናቸው ነው፡፡ ባለሥልጣናት “የሥም ማጥፋትን” ክስ እንደ ኢትዮ-ምኅዳር የማይወዱትን ፕሬስ እና ጋዜጠኛ ለማስወገድ፣ እንዲሁም እንደሰንደቅ ጋዜጣ የማይጠሉትን ፕሬስ በማስጠንቀቂያ ለማለፍ ይጠሙበታል፡፡ በነዚህ ምክንያት ይመስላል፣ ብዙ ዴሞክራሲያዊ አገራት “የሥም ማጥፋት” ክስን ከወንጀል ድርጊቶች ዝርዝር ውስጥ እየፋቁ ያሉት፡፡

ጥር 17/2006 በአዲስ አበባው የኢትንተርኮንቲኔንታል ሆቴል፣ በአዲስ አበባ ጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን ት/ቤት በተዘጋጀ አንድ ሲምፖዚየም ላይ የቀድሞው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ምንስትር ዲኤታ፣ አቶ ሽመልስ ከማል ‹የሥም ማጥፋት ክስ በወንጀል ሕጉ ውስጥ መካተቱ ስህተት መሆኑን መንግሥታቸው እንደደረሰበት› የተናገሩት “በጭንቅላት ተቆሞ የወጣ ሕግ” በማለት ነበር፡፡ ሚኒስትር ዲኤታው ‹የሥም ማጥፋትን የሚመለከተው አንቀጽ ከወንጀል ሕጉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይፋቃል› ብለው ቃል ቢገቡም፣ ይህን ከተናገሩ ከሦስት ዓመታት በኋላ ጌታቸው ወርቁ ተከሶበት፣ ታስሯል፡፡

የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 612/ለ፣ የሕጉን ተፈፃሚነት ሲያመለክት “የተባሉት ነገሮች ከሥራው ጋር አግባብነት ያላቸውና በተግባሩ ውስጥ ሆነው የተነገሩትም ክብርን ለመንካት በማሰብ ሳይሆን ተግባሩን በሚያከናውኑበት ጊዜ በተለይም በምርመራ፣ ሪፖርት በማድረግ ወይም የምስክርነት ቃልን በመቀበል፣ በፍርድ ቤት ወይም በአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች ፊት በመከራከር፣ በተፈቀደ የመንግሥት የመረጃ ግልጋሎት ጊዜ በመንግሠት ሠራተኛ፣ በጠበቃ ወይም ነገረ ፈጅ፣ በልዩ ዐዋቂ ወይም ምስክር፣ በጋዜጠኝነት ወይም በማንኛውም ሌላ ሰው በቅን ልቦና የሚደረጉ ወይም ተደግመው የሚነገሩ ንግግሮች፣ መግለጫዎች ወይም አስተያየቶች” እንደ ሥም ማጥፋት ወይም ክብር መንካት ተቆጥረው አያስቀጡም ይላል፡፡ (መስመር የተጨመረ፡፡)

ከክሱ ጋር ተያያዥ ፋይሎች ከስር ይገኛሉ፡፡

Getachew’s Sentence

Verdict on Getachew

Getachew’s Appeal

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *