በኢትዮጵያ የበይነመረብ ተጠቃሚዎች በኢንተርኔት ደህንነት ዙሪያ ያላቸውን አመለካከት የተመለከተ ጥናት ተደረገ፡፡

98 ከመቶ የበይነመረብ ተጠቃሚዎች የኢንተርኔት ደህንነት እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የበይነመረብ (ኢንተርኔት) አገልግሎት መስጠት ከተጀመረ አስር ዓመት በላይ አልፎታል፡፡ ይሁን እንጂ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የተጠቃሚዎቹ አሃዝ አናሳ ነበር፡፡ በ2000 ዓም የበይነመረብ ተደራሽነቱ 0.4 በመቶ ብቻ የነበር ሲሆን በ2009 ዓም ግን ተደራሽነቱ ወደ 15.4 በመቶ ማደጉን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ነገር ግን ወደ 100 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ እንዳላት በሚነገርላት ኢትዮጵያ ከጎረቤት ኬኒያ አንፃር ሲመዘን እንኳ የበይነመረብ ተደራሽነቱ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ በቅርቡ ፍሪደም ሃውስ የተባ ለመንግስታዊ ያልሆነ የሰብአዊ መብት ተቋም ይፋ ባረገው ሪፓርት የኢትዮጵያ መንግስት በከፍተኛ ደረጃ የበይነመረብን ተጠቃሚዎች ለመቆጣጠር ክትትል እና ቁጥጥር ከሚያደርጉ በዓለም አገራት የሁለተኛነትን ደረጃ ከሶሪያ እኩል ተቀምጧል፡፡ በርግጥ የኢትዮጵያ  መንግስት በይነመረብ ተዘግቶ እንደማያውቅ፣ የበይነመረብ ገደብ አለመኖሩን በተደጋጋሚ ማስተባበሉ ይታወቃል፡፡

በአለም አቀፍ ደረጃ የተባበሩት መንግስታት በበይነመረብ (ኢንተርኔት) ሐሳብን መግለፅ፣ ለመብት መከራከር፣ የሰብዓዊ መብት ተቀጥላ ተደርጎ የሚወሰድ በመሆኑ መንግስታት ሆነ ማናቸውም ተቋማት ይህንን ሰው በመሆን ብቻ የሚገኝ መብትን እንዲያከብሩ ማሳሰቡ ይታወቃል:: ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ የሚገኙ በርካታ ዜጎች በበይነመረብ  ሐሳብ የመሰንዘር መብታቸው እንደወንጀል ተቆጥሮ ለእስር እና ለከፋ እንግልት የተዳረጉ በርካታ ሰዎች መኖራቸው በተለያዩ ሪፖርቶች ይፋ ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው መንግስት ከሃገር ውጪም የሚገኙ አራማጆችን ኮምፒዩተር ሳይቀር በተደጋጋሚ ለመሰለል ጥረት ማድረጉን ክስ ቀርቦበት ይህንኑ ክስ አለማስተባበሉ እንዳለ ሆኖ ከተለያዩ የበይነ መረብ ነፃነት ተሟጋች ተቋማት መንግስት በይነመረብን ባሻው ሰኣት እንደሚዘጋ፣ ከፍተኛ ውጪን በማውጣት የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን እንደሚሰልል የተለያዩ ሪፖርቶች ይፋ መደረጋቸው ይታወቃል፡፡ በተለይ ፕራይቨሲ ኢንተርናሽናል እና የጀርመኑ የበይነመረብ ላይ ነፃነት አራማጅ ድረዓምባ ያገኙት ሚስጢራዊ ሰነድ መሰረት በማድረግ ባቀረቡት ሰፊ ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግስት በከፍተኛ ወጪ ዜጎቹን ለመሰልል በርካታ ቴክኖሎጂዎቹን ስለመግዛቱ አጋልጠዋል፡፡

የበይነመረብ ተጠቃሚዎች በኢንተርኔት ደህንነት ዙሪያ ያላቸውን አመለካከት የተመለከተ ያለውን የመረጃ ክፍተት ለመሙላት በሀርቫርድ ዩንቨርስቲ የበርክማን ክላየን ማዕከል ፌሎው የሆነው አስማማው ሃ/ጊዮርጊስ በተለይ ለኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ፕሮጀክት (ኢሰመፕ) ጥናት በማዘጋጀት ያቀረበ ሲሆን የዚህ ጥናት ዋነኛ መነሻም የጥናቱ አቅራቢው በተመሳሳይ ሐሳብ በእግሊዘኛ ያዘጋጀው ጥናት ነው ፡፡

ከመስከረም 10፣ 2010 እስከ ህዳር 12፣ 2010 ድረስ በበይነመረብ አማካኝነት በተሰራጨ መጠይቅ በዋንኛነት በማህበራዊ ሚዲያ፣ በኢሜል ምላሹ የተሰበሰበ ሲሆን የተሳታፊዎቹን ትክክለኛ ወካይነት ለማረጋገጥም የአይፒ መለያ ቁጥር በጥቅም ላይ ውሏል፡፡ መጠየቁ በሁለት ቋንቋዎች (በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ)  ተዘጋጅቶ የቀረበ ሲሆን በአጠቃላይ የጥናቱን ካልአይ የመረጃ ምንጮችን ለማሰባስብ፣ በጥናቱ ዐብይ ርእስ ላይ መሰረት ያደረጉ ጥያቄዎችን ማዘጋጀትና ማረም፣ ከተሳታፊዎቹ መረጃ ለመሰብሰብ የሚያስችሉ ተገቢ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎችን ለመምረጥና ማዘጋጀት፣ የተዘጋጁትን የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎች በሚገባ ለመተንተን ብቁ የሆኑን የሶፍትዌር ፍርግሞች መለየትና መሰል ተያያዥ ከጥናቱ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን ለማከናወን ከ6 ወራት ያላነሰ ጊዜን ወስዷል፡፡

ከጥናቱ የተገኙ ዋና ዋና ውጤቶች

በዚሁ ጥናት መሰረትም ስለ ኢንተርኔት ደህንነት እና ግለሰባዊ መብቶች መጠበቅ (Privacy) የሚያሳስቦት ምን ያሕል ነው የሚለው ጥያቄ ከቀረበላቸው በጥናቱ ተሳታፊ ከሆኑ በኢትዮጵያ የሚገኙ የበይነመረብ ተጠቃሚዎች መካከል 98 ከመቶ የግል ሚስጥራቸው መጠበቅ እንደሚያሳስባቸው ይፋ አድርገዋል፡፡

 በዚህ ጥናት ተሳታፊ ከነበሩት ውስጥ 70 በመቶ የሚደርሱት የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ከትምህርት ቤት ውጪ ወይም ተመርቀው በስራ ላይ የሚገኙ ሲሆን 25 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ በትምህርት ላይ የሚገኙ ናቸው፡፡ 5 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ከትምህርት ቤት ውጪ ነገር ግን ስራ ያልነበራቸው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

 ኢንተርኔት ሲጠቀሙ ምን ያህል ጊዜ ያጠፋሉ የሚለውን በተመለከተም 46 ከመቶ የሚሆኑት  የጥናቱ ተሳታፊዎች ከ2 ሰዓት በላይ ኢንተርኔትን መጠቀም እንደሚያዘወትሩ ሲገልፁ ከ91-120 ደቂቃን (ከአንድ ሰዓት ተኩል እስከ ሁለት ሰዓት) እንዲሁም ከ61-90 ደቂቃን (ከአንድ ሰዓት እስከ አንድ ሰዓት ተኩል) ኢንተርኔት በመጠቀም ጊዜያቸውን የሚያጠፉት  በተመሳሳይ 12 ከመቶ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ከግማሽ ሰዓት እስከ አንድ ሰዓት ኢንተርኔትን የሚጠቀሙ ደግሞ 25 ከመቶ ሲሆን ከ20-30 ደቂቃ ብቻ ኢንተርኔትን እጠቀማለሁ ያሉ የጥናቱ ተሳታፊዎች ድርሻ 5 በመቶ  ነው፡፡ በተሳታፊዎቹ ምላሽ መሰረት 95 ከመቶ የሚሆኑት ከ30 ደቂቃ በላይ ኢንተርኔትን እንደሚጠቀሙ ማወቅ ይቻላል፡፡

የኢንተርኔት ተደራሽ መሆን ሰብዓዊ መብት ነው ብለው ያምናሉ? የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ 91 በመቶ የሚሆኑት አዎንታዊ ምላሽን ሲሰጡ የተቀሩት ግን ማለትም 9 በመቶ የሚሆኑት አይ የሚል ምላሽን ሰጥተዋል፡፡

ስለ ኢንተርኔት ደህንነት እና ግለሰባዊ መብቶች መጠበቅ (Privacy) የሚያስቦት ምን ያሕል ነው የሚለውን ጥያቄ በተመለከተም ስለ ኢንተርኔት ደህንነት እና ግለሰባዊ መብቶች (ግለ ሚስጥር) ስለመጠበቁ ጉዳይ በጣም እጨነቃለሁ ያሉት 64 በመቶ ሲሆኑ 24 በመቶ የሚሆኑት ግን ስለ ኢንተርኔት ደህንነት እና ግለሰባዊ መብቶች መጠበቅ በመጠኑ እጨነቃለሁ ብለዋል፡፡ 10 በመቶ የሚሆኑ መላሾች በበኩላቸው በጣም በተወሰነ ደረጃ ብቻ እንደሚያስጨንቃቸው ሲገልፁ 2 በመቶዎቹ ደግሞ ስለ ራሴ ደህንነት የግል ጉዳይ ፈጽሞ አልጨነቅም ሲሉ ሐሳባቸውን ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም የጭንቀታቸው ደረጃ ይለያይ እንጂ 98 ከመቶ የሚሆኑት የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች የግል ሚስጥራቸው መጠበቅ እንደሚያሳስባቸው ይፋ አድርገዋል፡፡

ማህበራዊ ሚዲያን ለአካባቢያዊ ጥበቃ ለፆታ እኩልነት እና መሰል ጉዳዮች በስፋት በጥቅም ላይ በመዋሉ ረገድ የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች የሚገጥማቸው ሶስት ተግዳሮቶችን በተመለከተ 90 በመቶ የሚሆኑት የሚመለከታቸውን አካል ክትትል በመፍራት፣ 74 በመቶዎቹ ደግሞ የኢንተርኔት ተደራሽነት በበቂ ሁኔታ አለመኖርን እንደ ዋንኛ ተግዳሮት እንደሚቆጥሩት ገልፀዋል፡፡

 ኢንተርኔትን በመጠቀም ከሚያከናውኗቸው ተግባራት በመነሳት የእኔን ተግባር በዋነኝነት ይገልፀዋል የሚሉትን በተመለከተም 81 በመቶ የሚሆኑት በሐገሩ ጉዳይ የሚያገባው (መረጃ ያለው ዜጋ) በሚል ራሳቸውን ሲገልፁ 14 በመቶዎች ደግሞ አራማጅ (አክቲቪስት) ስለመሆናቸው የተቀሩት 5 በመቶ ደግሞ ራሳቸውን እንደ ዜጋ ጋዜጠኛ (Citizen journalist) እንደ ሚቆጥሩ ተናግረዋል፡፡

የኢንተርኔት ተጠቃሚነት ጋር በተያያዘ የአካዳሚክ ሰው የፆታ እኩልነት ተሟጋች የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ወይም የተቃውሞ ድምፅን የሚያሰማ የታሰረ ወይም ዛቻ የደረሰበትን ያውቃሉ ለሚለው 95 በመቶዎቹ አውቃለሁ የሚልን ምላሽ ሲሰጡ 5 በመቶዎች ግን የለም ሲሉ መልሰዋል፡፡

 

በዲጂታል አራማጅነት (ኢንተርኔት ላይ የሚደረጉ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ያመጣል የሚለውን ጥያቄ በተመለከተም 87 በመቶ የሚሆኑት አዎ ለውጥ ያመጣል በማለት እምነታቸውን ሲገልፁ 13 በመቶ የሚሆኑት ግን የለም ማለትም ለውጥ ያመጣል ብለው እንደማያስቡ መልሰዋል፡፡

 

ኢንተርኔት ሲጠቀሙ የግል ሚስጥርዎን ከመጠበቅ አንፃር ያደረጉት ዝግጅት በቂ ነው ብለው ያምናሉ? ወይስ ከዚህ የበለጠ ማድረግ ይገባኛል ብለው ያምናሉ? ለሚለው 75 በመቶ የሚሆኑት በጭራሽ የግል ሚስጥራቸውን ለመጠበቅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ አለማድረጋቸውን የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ እሻለሁ፡፡ ነገር ግን ይህንን እንዴት ማድረግ እንዳለብኝ አላውቅም:: ሲያወሱ 25 በመቶዎቹ ግን አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረጋቸውን ገልፀዋል፡፡

 

የጥናቱን ሙሉ ይዘት ይህንን   ማስፈንጠሪያ  በመጫን ያገኙታል፡፡

ኢሰመፕ- ለጥናት ባሞያው ለአቶ አስማማው ሃይለጊርጊስ ከፍተኛ ምስጋናና ያቀርባል ፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *