በእነ አስክንድር ነጋ ላይ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች የሚደመጡበት ቀን ተራዘመ፤ (ጥር 26፤ 2013 ዓ.ም)

በእነ አስክንድር ነጋ ላይ የዐቃቤ ህግ ምስክሮች የሚደመጡበት ቀን ተራዘመ፤

(ጥር 26፤ 2013 ዓ.ም)

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ-ሽብር እና ህገ-መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ጥር 26፣2013 ዓ.ም በእነ አስክንድር ነጋ ላይ የዐቃቤ ህግ ምስክሮችን ለመስማት ተሰይሞ የነበረ ቢሆንም ዐቃቤ ህግ ከጠቅላይ ፍርድ ቤት ባቀረበው የእገዳ ሰነድ ምክንያት ምስክሮች ሳይሰሙ ቀርተዋል፡፡ በችሎቱ የቀረበውን የእገዳ ትዕዛዝ በተመለከተ ሁለቱም ወገኖች የየራሳቸዉን መከራከሪያ ነጥብ ለፍርድ ቤቱ አቅርበዋል።

የተከሳሾች ጠበቆች በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በመዝገብ ቁጥር 26/0175 ላይ ምስክር ለመስማት የተጀመረዉ ሂደት በግልጽ የታገደ መሆኑን በመጥቀስ ከ1ኛ እስከ 4ተኛ ያሉ ተከሳሾች አቆያየትን በሚመለከት የእገዳ ትዕዛዙ ምንም ያለው ነገር ስለሌለ ተከሳሾቹ በችሎቱ ፊት እስረኛ የሚሆኑበት አግባብ ስለማይኖር መዝገቡን በማቋረጥ እንዲፈቱልን ሲል አቤቱታ አሰምተዋል፡፡ 5ተኛ ተከሳሽን በሚመለከት በወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 74 መሰረት ፍርድ ቤቱ ከዚህ ቀደም ዋስትና የፈቀደ መሆኑን፤ ነገር ግን አዲስ ነገር በተከሰተ ጊዜ የዋስትና ጥያቄን እንደገና ይመለከታል ስለሚል ተከሳሽ ያስያዙት ዋስትና እንዲወርድ ጠይቀዋል፡፡ አያይዞም የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 184 በጊዜያዊ ትዕዛዝ ላይ ይግባኝ እንደማይኖር በግልጽ የሚደነግግ መሆኑን በመጥቀስ በህጉ አንቀጽ 184/ሐ መሰረት ይግባኝ ማለት ሆነ ትዕዛዝ መስጠት የሚቻለዉ በማስረጃዉ ተቀባይነት እና ተቀባይ ያለመሆን ላይ ብቻ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ በመሆኑም ዐቃቤ ህግ ምስክር አቅርብ አታቅርብ በተባለዉ ላይ ይግባኝ ማለት እንደማይችል በመግለጽ ህገ-መንግስታዊ መሰረት በሌለው ጉዳይ ተከሳሾች ሰብዓዊ መብታቸዉን ማጣት ስለሌለባቸዉ ምስክር ማሰማት ብሎም ክሱን መቀጠል አልፈልግም የሚል ከሆነ ክሱን ያቋርጥ ሲሉ ተደምጠዋል።

ዐቃቤ ህግ በበኩሉ እገዳዉ ተከሳሾች ጉዳያቸዉን በማረሚያ ቤት ሆነዉ እንዲከታተሉ እንጂ ነጻ ይሁኑ እንደማይል እና ክሱን በሚመለከት ደግሞ ቀጣይነት ያለዉ እንደሆነ የሚያሳይ እንጂ ተቋርጧል የሚል ጭብጥ የሌለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በተጨማሪም አንቀጽ 184 በሚመለከት በጠቅላይ ፍርድ ቤት ክርክር የምናደርግበት ይሆናል በማለት ምላሽ ሰጥቷል።

በተያያዘ መልኩ ከተከሳሾች መካከል አቶ ስንታየሁ የቀረበባቸው ክስ የሀሰት ስለሆነ ዐቃቤ ህግ ምስክር ማቅረብ ብሎም በህጉ መሰረት ማስቀጣት እንዳልቻለ፤ ነገር ግን ተከሳሾችን እስር ቤት በማቆየት እንግልት እየፈጸመባቸው መሆኑን ችሎቱ በመገንዘብ ፍትህ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ወ/ሮ አስካል ደምሴ በበኩላቸው ተከሳሾች ፍትህ እናገኛለን፤ ምስክር እንሰማልን ብሎ በሚጠብቁበት ሰዓት የተፈጠረው ነገር ቅስም ሰባሪ መሆኑን ገልጸው ሂደቱ በአጠቃላይ የሃሰት ስለሆነ የሞራል ካሳ ተሰጥቶን መፈታት አለብን ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ በመጨረሻም ወ/ሮ ቀለብስዩም ችሎቱ በህጉ መሰረት እንዲዳኛቸው እና በተማሩት መሰረት ትክክለኛ ፍትህ ማግኘት እንደሚሹ ተናግረዋል ።

ችሎቱም የግራ ቀኙን ክርክር ካዳመጠ በኋላ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ዉሳኔ በመቀበል ቀጣይ ቀጠሮ ለየካቲት 16፤2013 ዓ.ም ሰጥቷል።

Center for Advancement of Rights and Democracy (CARD)

Making Democracy the Only Rule of Game!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *