Photo Credit - Addis Standard

በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገብ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ እንዲታዩ የቀረበው ይግባኝ ተከሳሾች በሌሉበት ተደመጠ

  • ተከሳሾች በአካል ካልሆነ በቀር በፕላዝማ አንቀርብም ብለዋል።
  • ዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸው የመወሰን ሥልጣን የፍርድ ቤት ሳይሆን የዐቃቤ ሕግ ነው ብሎ ተከራክሯል።

ሚያዝያ 20፤ 2013 – የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ ሕገ መንግሥታዊ እና የፀረ ሽብር ጉዳዮች ችሎት፣ ምስክሮች ሥማቸው ሳይገለጽ በግልጽ ችሎት እንዲመሰክሩ የሰጠውን ብይን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ የምስክር ደኅንነት ጥበቃ ዐዋጁን መሠረት በማድረግ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁለተኛ መዝገብ ችሎት ይግባኝ ማለቱ ይታወሳል።

በተከላካይ ጠበቆች በኩል ተከሳሾች በአካል ቀርበው መሳተፍ እና ማስረዳት ስለሚፈልጉ ችሎቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው እንዲሁም ከ17ኛ እስከ 23ኛ ያሉ ተከሳሾችን ሥማቸው ሲጻፍ በወታደራዊ ማዕረግ መሆን እንደነበረበት ለችሎቱ  አቤቱታዎች አሰምተዋል።

ችሎቱ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ተከሳሾች በአካል መቅረብ ስለማይችሉ፣ በፕላዝማ ቀርበው እንዲከታተሉ በቀደመው ችሎት ብይን በተመሳሳይ መልኩ እንደተሰጠ እና በማዕረጋቸው ያልተጠሩ ተከሳሾችን በሚመለከት ዐቃቤ ሕግ ክሱ ላይ ሥማቸውን ከማዕረጋቸው ጋር አስተካክሎ እንዲያቀርብ ውሳኔ ሰጥተዋል።

ይሁንና ተከሳሾች በፕላዝማ አንቀርብም በማለታቸው በጠበቆቻቸው በኩል ተወክለው ቀርበዋል።

ዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸው የመወሰን መብት የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እንጂ የከፍተኛ ፍርድ ቤት እንዳልሆነ በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ሥልጣን አለኝ ብሎ ቢያስብ እንኳን ዐቃቤ ሕግን ምክንያት ባላመዛዘነ መልኩ አቤቱታውን ውድቅ ማድረጉ ትክክል አለመሆኑን፣ በማከልም ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ መሆኑ የተከሳሾችን የመጠየቅ መብት እንደማይጋፋ እና ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን እንደማይጣረስ ዐቃቤ ሕግ አስረድተዋል።

ጠበቆች የምስክር ማንነት ባልታወቀበት ወይንም በማይታይበት ሁኔታ የምስክር ቃሉ ተዓማኒነት ከጥያቄ ውስጥ የሚገባ ነው፤ ምክንያቱም በግል ጥላቻ ይመስክር ወይንም በሐቅ የሚታወቀው ምስክሮች በግልጽ ችሎት ሲመሰክሩ  ብቻ ነው ብለው ተከራክረዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ተከሳሾች የፖለቲካ አመራር እንደመሆናቸው እና ብዙ ተከታዮች ስላላቸው አደጋ ማድረስ የሚያግዳቸው ነገር እንደማይኖር፣ እንደ ምሳሌነትም ጃዋር መሐመድ በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ጥበቃዎቼ ተነስተዋል ብለው በለጠፉት መልዕክት የብዙ ንፁኃን ሞት መንስዔ መሆኑ የሚታወስ ነው በማለት፣ ምሰክሮቹ በኦሮሚያ ክልል እንደ መገኘታቸው መጠን ለነርሱም ለቤተሰቦቻቸው ደኅንነት እንሰጋለን ብሏል።

ተከላካይ ጠበቆች በበኩላቸው ከ23 ተከሳሾች ሦስቱ ብቻ የፖለቲካ አመራር እንደሆኑ የተቀሩት ደሞ ተማሪዎችና መንግሥት ለጃዋር መሐመድ የቀጠራቸው ጥበቃዎች እንደሆኑ ዐቃቤ ሕግ እንዳሉት ለደኅንነት አስጊ አይደሉም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

በተከላካይ ጠበቆች እንደመፍትሔ በቀረበው ሐሳብ ላይ ዐቃቤ ሕግ የ146 ምስክሮችን ከነቤተሰቦቻቸው የቦታ ለውጥ ማድረግ ቦታ መቀየር ሳይሆን እንደማፈናቀል ነው የሚሆነው፤ ትጥቅ ማስታጠቁም ሆነ ማንነት መቀየር ምስክሮች ካላቸው የቁጥር ብዛት አንፃር ለሦስተኛ ወገን ደኅንነት አስጊ ስለሚሆን እንደ መፍትሔ ምስክሮች ከማጋረጃ ጀርባ እና በዝግ ችሎት እንዲመስክሩ ለችሎቱ አቤቱታ አሰምተዋል።

ጠበቆች በቅድመ ምርመራ ወቅት ምስክሮች ከመጋረጃ ጀርባ እንደተመሰከረ ሁሉ በግልጽ ችሎትም የመሰከሩ እንደነበሩ ለችሎቱ በማስታወስ ነገር ግን በነዛ ምስክሮች ላይ አንዳችም ጉዳት ያልደረሰባቸው መሆኑ እና ከመጋረጃ ጀርባ መሆኑ የተከሳሾችን ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የሚጣረስ ስለሆነ ችሎቱ የዐቃቤ ሕግ የይግባኝ ጥያቄ ውድቅ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል። ፍርድ ቤቱ የግራ ቀኙን ክርክር ሰምቶ መዝገቡን መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ለግንቦት 4፣ 2013 ቀጣይ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ሚያዚያ 15 በዋለው ችሎት በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ ለተከሰሱትም ተመሳሳይ ክርክር ማስተናገዱ ይታወሳል።

Center for Advancement of Rights and Democracy (CARD)

Making Democracy the Only Rule of Game!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *