በእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ ለመከላከያ መስክርነት የተጠሩ ባለስልጣናት ሳይቀርቡ ቀሩ፡፡ (ጥቅምት 27፣ 2010)

“ለምስክርነት የተዘረዘሩት ባለ ስልጣናት መጥሪያ አልተላከላቸውም፡፡” ፍርድ ቤቱ

“ከተከበሩ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ጋር አንድ ላይ የምክር ቤት አባል ነበርን፡፡ እሳቸው ኢህአዴግ ስለሆኑ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆኑ እኔ ተቃዋሚ ስለሆንኩ እስር ቤት ገባሁ፡፡” ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ደጀኔ ጣፋ

 “እኔ በተሰጠው ቀጥሮ (ህዳር 6) ልቀርብ ፈቃደኛ አይደለሁም፡፡ ከህግ በላይ የሆኑ ሰዎች አሉ ማለት ነው? በፍርድ ቤቱ አካሄድ   አላመንኩበትም፡፡” አራተኛ ተከሳሽ አቶ በቀለ ገርባ

የእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ  ለጥቅምት 27፣2010 የተቀጠረው የተከሳሾቹን መከላከያ ምስክሮችን ለመስማት ነበር፡፡ በዚህም መሰረት መዝገቡን የሚያየው የከፍተኛው ፍርድ ቤት 4ኛ ችሎት የተመደቡ አዲስ ዳኞች መዝገቡን ካገላበጡ በኃላ መዝገቡ በምስክርነት ለተጠሩ አምስት የመንግስት ባለስልጣናት መጥሪያ አለመውጣቱንና ለሌሎች ምስክሮች ግን መጥሪያ መውጣቱን አረጋግጠዋል፡፡ በተጨማሪም የተከሳሾቹ የስም ዝርዝር በሚጠራበት ወቅት 11ኛ ተከሳሽ አቶ በየነ ሩዶ አለመቅረባቸው ታውቋል። በተመሳሳይ መዝገብ የሚገኝ አንድ ተከሳሽ ከአቶ በየነ ሩዶ ጋር በቂሊንጦ በአንድ ዞን እንደሚኖሩ ገልፆ “ጠዋት ፍርድ ቤት ቀጠሮ አለኝ ብሎ ሲወጣ፤ አንተ ቀጠሮ የለህም ብለው ፖሊሶች መለሱት” በማለት የተፈጠረውን ነገር ያስረዳ ሲሆን ዳኞች ከተከሳሹ መቅረት ጋር ተያይዞ የሰጡት ትእዛዝም ሆነ አስተያየት የለም።

አምስቱን የመንግስት ባለስልጣናትን በጋራ የመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡ የጠየቁት ከአንደኛ እስከ አራተኛ የሚገኙት ተከሳሾች ጠበቆች መጥሪያ አለመውጣቱን ተቃውመው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ የአራቱ ተከሳሾችን የጋራ መከላከያ ምስክሮችን (ባለስልጣናቱን) ዝርዝር ባስገቡበት ወቅት ፍርድቤቱ ተቀብሎ እንደሌሎቹ መከላከያ ምስክሮች መጥሪያ እንዲያወጣላቸው ያዘዘ መሆኑን እና አቃቤ ህግም ተቃውሞ አለማንሳቱን ጠበቆች አቶ አመሃ መኮንን እና አቶ አብዱልመጅድ ሁሴን ለፍርድ ቤት አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ከቃሊቲ ማረሚያ ቤት እንዲቀርብላቸው መጥሪያ የተላከለት የአራተኛ ተከሳሽ (አቶ በቀለ ገርባ) መከላከያ ምስክር የሆነው አቶ አንዷለም አራጌ በዛሬው እለት መቅረብ ሲኖርበት እንዳልቀረበ እና በቀጣይ ቀጠሮ እንዲቀርብ ጠይቀዋል፡፡ ለምስክርነት ተጠርተው መጥሪያ ያልተላከላቸውን ባለስልጣናት በተመለከተ ፤ መጥሪያውን እንዲያደርስ የሚጠበቅበት የፍርድ ቤቱ አካል ለምን እንዳልደረሳቸው ቀርቦ እንዲያስረዳ እና በተያዙት ተከታታይ ቀጠሮዎች ቀርበው እንዲመሰክሩ መጥሪያው እንዲወጣ እንዲታዘዝ ሲሉ ጠበቆቹ አሳስበዋል፡፡ በዛሬው እለት በግራ ዳኝነት የተሰየሙት አቶ ዮሐንስ ምስክሮቹ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት መሆናቸውን ገልፀው በምን ጭብጥ እንደሚመሰክሩላቸው ጠይቀዋል፡፡ የሚመስክሩባቸውን ጭብጦች በስነስረአት ህጉ መሰረት ምስክሮቹ ሲቀርቡ የሚያሳውቁ መሆኑን የገለፁት ጠበቆቹ ፤ ተከሳሾቹ የተከሰሱት በኦሮሚያ በ2008 ከነበረው ተቃውሞ ጋር በተያያዘ ስለሆነ የተጠሩት ባለስልጣናት ደግሞ በጉዳዩ ላይ እውቀት ያላቸው እና በተለያየ ጊዜ ለሚዲያ መግለጫ ሲሰጡ የነበሩ መሆናቸውን ጠቅሰው ከክሱ ጋር ቀጥታ የሚገናኝ ምስክርነት እንደሚሰጡላቸው ተናግረዋል፡፡ ጠበቆቹ በተጨማሪም ባለስልጣናቱ በተለያየ ጊዜ የተናገሯቸውን ንግግሮች እና የሰጧቸውን መግለጫዎች ከኢብኮ (የኢትዮጵያ ብሮድካስቲን ኮርፖሬሽን) እና ሌሎች የመንግስት ተቋማት እንዲቀርቡላቸው ዝርዝር ማስገባታቸውን ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡ ዳኛ ዮሐንስ ጠበቆቹ የጠቀሷቸው የሰነድ ማስረጃዎች ባለስልጣናቱ በአካል መጥተው ለሚመሰክሩት ምስክርነት አይበቃም ወይ? በማለት ለጠበቆች ጥያቄ እቀርበው ነበር፡፡ ጠበቆቹም ባለስልጣናቱ በአካል ቀርበዉ የሚመሰክሩበት ጭብት በመግለጫ በሰጡት እና ባደረጉት ንግግር ሊመለስ እንደማይችል እና እንደማይመሳሰል ምላሻቸውን ሰጥተዋል፡፡ ዳኞችም መጥሪያው ለምን እንዳልወጣ እና በጉዳዩ ላይ የሚሰጡትን ውሳኔ ለመስጠት ለከሰአት ቀጥረው የቀሪ ተከሳሾችን መከላከያ ምስክሮች ወደ መስማት ሂደት አልፈዋል፡፡

በቅድሚያ መከላከያ ምስክሮቹን እንዲያሰማ የቀረበው በመዝገቡ ስምንተኛ ተከሳሽ የሆነው ጌቱ ግርማ ነው፡፡ ጌቱ ግርማ ምስክሮቹን ከማሰማቱ በፊት የሚከተለውን የመከላከያ ምስክርነት ቃሉን ሰጥቷል፡፡

“ክሱ በኦሮሚያ ፋይናንስ እና ኦዲት ቢሮ እየሰራሁ እያለ የኦነግ ሴል ማደራጀቴን ነው የሚገልፀው፡፡ ማን እንዳደራጀኝ እኔ ደግሞ ማንን እንዳደራጀሁ የሚያስረዳው ነገር የለም፡፡ በአቃቤ ህግ ምስክርነት የቀረበብኝ አቶ ተክሌ ገ/ህይወት ሲመሰክር በፌስ ቡክ ላይ ፕሪንት ሆነው የወጡ ወረቀቶች ላይ መንግስትን የሚቃወም ነገር ፅፏል ብሏል፡፡ ፅሁፎቹም በኦሮምኛ የተፃፉ መሆናቸውን እና ኦሮምኛ ቋንቋ የማይችል መሆኑን ተናግሯል፡፡ ኦሮምኛ የማይችል ከሆነ መንግስትን የሚቃወም ይሆን አይሁን በምን አወቀ? በተጨማሪም ምስክሩ ከኛ መዝገብ በተጨማሪ በተለያዩ መዝገቦች ከ2008 ጀምሮ የአቃቤ ህግ ምስክር ሆኖ ቀርቧል፡፡ በነ ደስታ ዲንቃ መዝገብ፣ በነ ደረጄ አለሙ መዝገብ እና በነ ተሾመ ረጋሳ በሚባሉ መዝገቦች የአቃቤ ህግ ምስክር ሆኖ ቀርቧል፡፡ በዛ ላይ የእውነት ምስክር እና እኔንም ያየኝ ቢሆን ለይቶ ያሳየኝ ነበር፡፡ እሱ ግን በሚመሰክርበት ወቅት ሊለየኝ አልቻለም፡፡ ስለዚህ የሰጠው ምስክርነት የተሳሳተ እና በወቅቱም ያልነበረ በመሆኑ ውድቅ ይሁንልኝ፡፡ በተጨማሪም በፀረ ሽብር ህጉ አንቀፅ 14 እና አንቀፅ 23 መሰረት ስልክ በመጥለፍ የተሰበሰቡ የተባሉ ማስረጃዎች አንደኛ ስልኩ ተጠልፎ ሲከታተሉ የነበረው በፍርድ ቤት ትእዛዝ እንደነበረ የሚያሳይ ማስረጃ የለም ሰበሰብን የሚሉት ነገር ህጋዊ መሰረት የለውም፤ ሁለተኛ እኔ የማላቀውን ተጠቅሜ የማላቀውን ቁጥር ነው የፃፉት ማእከላዊ በኤግዚቤትነት የተያዘብኝ ስልክም እነሱ በሪፖርታቸው የገለፁት አይደለም፤ ሶስተኛ እኔ የተወለድኩትም ያደኩትም ኦሮሚያ ነው፡፡ ከስራዬም ፀባይ አንፃር ብዙ ጌዜ የማወራው በኦሮምኛ ነው፡፡ ከኢንሳ መጣ የተባለው ሪፖርት በአማርኛ ነው፡፡ ኢንሳ ደግሞ የመተርጎም ስልጣን የለውም፡፡ አስተርጉሞም ከሆነ ከህጋዊ ተርጓሚዎች ያስተረጎመበትን መረጃ ማቅረብ አለበት፡፡ እነሱ ያቀረቡት የራሳቸውን ቃላት እና አረፍተነገር ሰብስበው ነው፡፡ ኮንትሮባንድ የመሰለ መረጃ ነው፡፡ እኔን አይገልፅም፡፡ ሌላ በስነስረአት ህጉ አንቀፅ 27(2) መሰረት ለፖሊስ ሰጠ ተብሎ የቀረበው እኔ በፈቃዴ የሰጠሁት ቃል አይደለም፡፡ ለምርመራ በማእከላዊ አራት ወር ቆይቻለው፡፡  እኔ የሰጠሁት ቃል ከተወለድኩ ጀምሮ እጄ እስከሚያዝበት ሰአት ድረስ ያለውን ታሪኬን ነው፡፡ከፌስቡክ ወጣ ብለው ያስፈረሙኝም ደብድበው ነው ያስፈረሙኝ፡፡ በዛ ወቅት በደረሰብኝ ድብደባ ግራ ጆሮዬ ከጥቅም ውጪ ሆኗል፡፡ በግራ ጆሮዬ መስማት አልችልም፡፡ ቂሊንጦ ከመጣሁ ራሱ ሃኪም ቤት አይወስዱኝም፡፡ ለመከላከያ ልትጠቀምበት ነው የምትፈልገው ይሉኛል፡፡ ሃገሬ ሰላሌ ነው፡፡ አደራጅተሃል የተባልኩት ደግሞ በዛው መስመር ያሉ ከተሞች ነው፡፡ ኮታ የተሰጠኝ ነው የሚመስለኝ፡፡ እስከ አባይ በረሃ ድረስ ያሉ ከተሞች ተጠቅሰዋል፡፡ እንደዚህ አይነት ወንጀልም አይሰራም፡፡” በማለት መከላከያ ቃሉን ሰጥቷል፡፡

የስምንተኛ ተከሳሽ ጌቱ ግርማ የመጀመሪያ መከላከያ ምስክሩ በተመሳሳይ መዝገብ ተከሳሽ ሲሆን ተስፋዬ ሊበን ይባላል፡፡ ተስፋዬ ሊበን ስምንተኛ ተከሳሽ ጌቱን በማእከላዊ እንደሚያቀው፣ በጨለማ ቤት አንድ ክፍል ውስጥ እንደነበሩ፣ ለምርመራ እየተባለ ቀንም ማታም ለሊትም እየተወሰዱ ያልሰሩትን ነገር እመኑ እየተባሉ ድብደባ እንደሚፈፀምባቸው፣ ጌቱ እስከ ሌሊት 8ት ሰአት ድረሰ ቆይቶ አንዳንድ ፅሁፎች ያንተ ናቸው ከኦነግ ጋር ግንኙነት አለህ እየተባለ ተደብድቦ ወደ ክፍላቸው ይመለስ እንደነበረ፣ ጥር 25/2008 ቀን ማታ ላይ አብረው ምርመራ ክፍል አብረው ተጠርተው 31 ቁጥር ምርመራ ክፍል አገብተው እሱንም ጌቱንም እጃቸው ላይ ካቴና እንደታሰረላቸው ደብድበው እንዳስፈረሟቸው፣ ጌቱ አልፈርምም ሲል አንድ መርማሪ በሁለቱም እጆቹ በአንዴ በጥፊ እንደመታው እግሩ ላይም በከስክስ እንደመታው ከዛም ጌቱ በግራ ጆሮው ደም ሲወጣ እንዳየ እግሩም እንዳበጠ፣ እሱ ራሱ (መስካሪው) በደረሰበት ድብደባ ደም እየፈሰሰው እንደነበር፣ ጌቱም በድብደባው ምክንያት መሬት እንደወደቀ እና መርማሪዎች አንስተው እንዳስፈረሙት፣ ቀድሞ ጨርሶ ወደክፍሉ ከሄደ ከተወሰነ ደቂቃዎች በኋላ ጌቱ እንደመጣ እና በክፍሉ የነበሩ ሌሎች እስረኞች እርዳታ እንዳረጉላቸው ገልፇል፡፡ እንዲሁም ህክምና ማግኘት እንዳልቻሉም አስረድቷል ምስክሩ፡፡

በተመሳሳይ ጭብጥ የሚያስረዳለት ሌላው ምስክር የሆነው አብደታ ነጋሳ ፤ ተከሳሹ ምስክርነቱን አልፈልገውም በማለቱ ሳይመሰክር በችሎት እንዲሰናበት ተደርጓል፡፡

ችሎቱ የምሳ ሰአት በማለፉ ቀሪ ምስክሮችን ለመስማት እና ትእዛዙን ለመስጠት ለከሰአት ቀጥሯል፡፡ እንደተለመደው የተከሳሾቹ ጠበቆች ተከሳሾቹ ቤተሰብ የሚያቀርብላቸውን ምግብ እንዲመገብ ትእዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡ የማረሚያ ቤት ኋላፊዎችም ከማረሚያ ቤት የመያላቸውን ምሳ እንደሚያበሏቸው እና የቤተሰብ ምግብ ተቀብሎ ለማስተናገድ በማረሚያ ቤቱ እንደሚያደርጉት ከደህንነት አንፃር መፈተሻ እንደሌላቸው ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል፡፡ ጠበቆቹ ከዚህ ቀደመም በመዝገቡ ተከሳሾቹ በሚውሉበት ጊዜ ምሳ ከቤተሰብ እንዲቀርብላቸው የሚታዘዝ ሲሆን የቀረቡት ኃላፊም የፍርድ ቤት ትዝዛዝ ባለማክበራቸው የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ግለሰብ መሆናቸውን አስታውሰው ፤ የማረሚያ ቤቱ ደምብ  የተመጣጠነ ምግብ ለታራሚዎች ያቀርባል የሚል መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የማረሚያ ቤቱ ኃላፊ ይዘው የመጡትን ምሳ ይዘት ተጠይቀው የሚያቀርቡላቸው ዳቦ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሁለተኛ ተከሳሽ ደጀኔ ፤ ከዳኞቹ ለመዝገቡ አዲስ መሆናቸውን ገልፆ ከዚህ በፊት ምሳ ከቤተሰብ ሲቀርብላቸው ይሰራበት የነበረውን አሰራር ገልፆላቸዋል፡፡ “እዚህ ውስጥ የስኳር ህመምተኛ አለ፡፡ እስካሁንም ኮካ እየጠጡ ነው የቆዩት፡፡ ለኔ ለምሳሌ ባለቤቴ አለች፡፡ እሷ ናት የምታመጣልኝ፡፡ ሌሎቹም ልጆቻቸው እህቶቻቸው ናቸው የሚያመጡት፡፡ ሚስቴ ምታመጣልኝን ምግብ እንዴት እጠራጠራለው? እንዳትገለኝ ነው?” በማለት ደጀኔ ጣፋ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ዳኞቹም ተከሳሾቹን ዳቦ በልታችሁ የከሰአቱን ችሎት ተከታተሉ ማለት እንደሚከብዳቸው ገልፀው ቤተሰብ የሚያመጣላቸውን ምግብ ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ እንዲያበሏቸው ለኃላፊው ያዘዙ ሲሆን ተከሳሾቹም በታዘዘው መሰረት ተስተናግደዋል፡፡

ዳኞቹ በከሰአቱ ችሎት ስራቸውን የጀመሩት ከአንደኛ እስከ አራተኛ ያሉ ተከሳሾች የጠሯቸውን የጋራ ምስክሮች በተመለከተ ውሳኔያቸውን በማሳወቅ ነው፡፡ ዳኞቹ ለመከላከያ ምስክርነት የተጠሩት ባለስልጣኖች መጥሪያ ይሰጣቸው ወይንስ አይሰጣቸው በሚለው ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት ለህዳር 6 መቅጠራቸውን ተናግረዋል፡፡ ጠበቆችም መጥሪያ እንዲወጣ ከዚህ በፊት የታዘዘ መሆኑን አስታውሰው ፤ በዛሬው ውሳኔ ፍርድ ቤቱ የራሱን ውሳኔ እየሻረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አራተኛ ተከሳሽ አቶ በቀለም ይህንን አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

“እነዚህ ምስክሮች ከሌሎቹ ምስክሮች የሚለዩበት ምክንያት አልገባኝም፡፡ ፍርድ ቤቱም ለሌሎቹ ምስክሮቹ መጥሪያ ሲያደርግ ለነዚህ መጥሪያ ወጪ አለማድረጉ ያልተለመደ ነገር ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ትልልቅ እና ትንንሽ አድርጎ የሚያያቸው ሰዎች አሉ ማለት ነው? ህግ አለ ብለን ነው እዚህ የምንመጣው፡፡ ምስክሮቹ ለምን እንዳልቀረቡ ማብራሪያ መስጠት አለበት፡፡ እንጂ እንደ አሻንጉሊት እየመጣን የምንገተርበት ምክንያት የለም፡፡ የጠራናቸው ምስክሮች እዚሁ ከተማ ወይም ሃገር ያሉ ናቸው፡፡ ዛሬ ይቀርባሉ ብለን ነበር የገመትነው፡፡ ለምን አልቀረቡም? ይቀርባሉ አይቀርቡም የሚለው ነገር ራሱ ከጥያቄ ውስጥ አይገባም፡፡ እኔ በተሰጠው ቀጥሮ (ህዳር 6) ልቀርብ ፈቃደኛ አይደለሁም፡፡ ከህግ በላይ የሆኑ ሰዎች አሉ ማለት ነው? በፍርድ ቤቱ አካሄድ አላመንኩበትም፡፡ ከዚህ ቀደም ለኔ አራት ወር የፈጀውን የዋስትና መብት ሲሰጠኝ፤ ለአቃቤህግ  በ2ሰአት ውስጥ የዋስትና መብቴን ለማሳገድ ችሏል፡፡ በፍትህ ስርዓቱ አላመንኩበትም፡፡ እዚህ ከምመላለስ እዛው የሰጣቹኝ ማጎሪያ ቤት ብቀመጥ እመርጣለው፡፡

ዳኛ ዮሐንስ በተደጋጋሚ ውሳኔውን ማስተላለፋቸውን በመግለፅ ሊያቋርጧቸው እየሞከሩ የነበረ ሲሆን በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሳይሰጡ የሌሎች ተከሳሾችን መከላከያ ምስክሮች መስማት ቀጥለዋል፡፡

በመቀጠል የተሰሙት የመከላከያ ምስክሮች የስድስተኛ ተከሳሽ የገላና ነገራ ናቸው፡፡ ተከሳሹ ገላና በቅድሚያ የመከላከያ ቃሉን የሰጠ ሲሆን ፤ ሰላማዊ ሰው መሆኑን፣ በማእከላዊ የሰጠው ቃል የሰብአዊ መብቱ ተጥሶ ያለፈቃዱ የሰጠው መሆኑን፣ በደረሰበት ድብደባም ከባድ ጉዳት የደረሰበት መሆኑን፣ ከኢንሳ ቀረቡት ሪፖርቶች ውስጥ የተጠቀሱት ስልኮች የሱ አለመሆናቸውን ጠቅሶ ፍርድ ቤቱ ስልኮቹ የማን መሆናቸውን እንዲያጣራ ለቴሌ እንዲያዝለት ጠይቋል፡፡

በቅድሚያ ለስድስተኛ ተከሳሽ ገላና ነገራ ለመመስከር የቀረበው ቶኩማ ለማ ይባላል፡፡ ቶኩማ ከተከሳሹ ገላና ጋር በ2001 በጅማ ዩንቨርስቲ ተመድበው ከተገናኙበት ጊዜ ጀምሮ እንደሚተዋወቁ እን ጓደኛሞች መሆናቸውን፣ በዩንቨርስቲ ውስጥ ምንም አይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ እንዳልነበራቸው፣ ከተመረቁ በኋላም ቡራዩ አካባቢ መኖር እንደጀመሩ  በጥቃቅን  እና አነስተኛ ተደራጅተው በኮንስትራክሽን ስራ እንደተሰማሩ እንዲሁም በሚያውቀው ጊዜ ሁሉ የሚጠቀመው ሲም አንድ መሆኑን (የሚያቀውን ስልክ ቁጥር ተናግሯል) ፡፡ ምስክሩ ቶኩማ አክሎም ፤ ቡራዩ እየሰሩ ባሉበት ወቅት በ2008 ማስተር ፕላኑ ትግበራ ላይ በቡራዩ ከተማ ውይይት ተጠርተው እንደነበረ እና በወቅቱ እሱ፣ ገላና እና ሌሎች ጓደኞቻቸው ፤ ማስተር ፕላኑን ጥናት ሳይደረግበት ህዝብ ሳይወያይበት እንዴት ትግበራ ላይ ትጠሩናላችሁ፤ ገበሬውም ተገቢውን ካሳ ሳያገኝ በየቦታው ወድቆ ዘበኛ እየሆነ ነው ይሄ እንዴት ልማት ይባላል? በማለት ተቃውሞ በማቅረባቸው ማእከላዊ ታስረው እንደነበረ ገልፇል፡፡ስብሰባው ከተካሄደ አምስት ወይም ስድስት ቀን በኋላ መታሰራቸውን የገለፀው ቶኩማ በማእከላዊ እያሉም ገላና የማያቃቸው ስልኮች ያንተ ነው እየተባለ እንዲፈርም እንደሚያስገድዱት እንደነገረው መስክሯል፡፡ ቶኩማ ለእስር የተዳረጉት በስብሰባው ወቅት ባቀረቡት የተቃውሞ ሃሳብ መሆኑን ገልፇ ጊዜያዊ ቀጠሮ ግን ሲያቀርቧቸው የሚያቀርቡባቸው ክስ ከኦነግ ጋር በመስራት በመደዋወል የሚል መሆኑን ተናግሯል፡፡ ከሶስት ወር ሶስት ሳምንት በኋላ ከማእከላዊ እንደተፈታ ተናግሯል ምስክሩ ቶኩማ ለማ፡፡ አቃቤ ህግ ለቶኩማ ፤ ተከሳሹ ከሱ ጋር በማይገናኝበት ወቅት ምን ይሰራ እንደነበር እንደሚያውቅ ጥያቄ አቅርቦለት “ህግ ባለበት ሃገር ምን ሊሰራ ይችላል? ፖለቲካ ፓርቲ በድብቅ አቋቁሞ ይሰራል ብለህ ነው?” በማለት በችሎት የነበረውን ሰው ፈገግ አስብሏል፡፡

ስድስተኛ ተከሳሽ ገላና ነገራ ሁለተኛ ምስክሩ አብዶ ወልዴ ይባላል፡፡ ምስክሩ አብዶ ገላና ነገራ ጋር ዝምድና እንዳላቸው፣ በልጅነታቸው አብረው እንዳደጉ እና አብረው እንደተማሩ፣ ገላና ዩንቨርስቲ ከገባ ኋላም ክረምት ክረምት ሲሆን እንደሚገናኙ፣ ስራ ከያዘ በኋላ ደግሞ ቢያንስ በየሳምንቱ እንደሚደዋወሉ እና እንደሚገናኙ፣ ገላና ስልክ ካወጣ ጊዜ ጀምሮ የሚተቀመው አንድ ሲም መሆኑ ሌላ ሲም ቢኖረው ያውቁ እንደነበረ እና ሚስጥረኞች መሆናቸውን በማስረዳት ምስክርነቱን ጨርሷል፡፡

የስራ ሰአት በማለቁ ለቀጣይ ቀን በተያዘው ቀጠሮ እንደሚቀጥል ዳኞች ተናግረዋል፡፡ አቶ በቀለ በችሎቱ ውሎ ላይ አስተያታቸውን እንደሚከተለው ሰጥተዋል፡፡

“በዛሬ ውሎ ላይ ነው አስተያየት መስጠት የምፈልገው፡፡ ችሎቱ ክፍት ነው ይመስለኛል፡፡ ለቤተሰብም፣ ለታዳሚም፣ ለጋዜጠኛም፣ ለማንም፡፡ ነገር ግን ሁለት ሰዎች ላይ ችሎቱ ጥያቄ ጠይቋቸዋል፡፡ አንድ ወንድሜ ከችሎት መሃል ምስክር እየተሰማ ተነስቶ ሞባይሉን እንዲያሳይ ተጠይቆ ሞባይሉ ታይቶ ተመልሷል፡፡ ሰብአዊ መብቱ ተገፏል፡፡ አንዷ ታዳሚ ከችሎት ስትወጣ እንድትቆም ተደርጎ ጋዜጠኛ ነሽ ወይ ተብላ ተጠይቃለች፡፡ ችሎቱን የሚከታተሉ ላይ ወከባ ለመፍጠር እና እንዳይመጡ ለማድረግ ችሎቱ አቋም የያዘ ነው የሚመስለኝ፡፡ ይሄ ነገር እንዳይደገም ነው አመሰግናለው፡፡”

ሁለተኛ ተከሳሽ ደጀኔ ጣፋም  ይህን አስተያየት ሰጥቷል፡፡

“በህግ ነው የምንመራው፡፡ በህግ አካል ደግሞ ትልቁ ቦታ የሚሰጠው ፍርድ ቤት ነው፡፡ በየትኛውም አለም ላይ፡፡ እንደናንተ ባላውቅም ኢትዮጵያ ውስጥ ነው ህግ ነው የተማርኩት፡፡ የአንድን ማስረጃ ተቀባይነት እና ጉዳዩ ይገናኛል አይገናኝም የሚል ቅድመ ምርመራ አይቼ አላውቅም፡፡ አቃቤ ህግ ባልተቃወመበት ሁኔታ፡፡ ከተከበሩ አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ጋር አንድ ላይ የምክር ቤት አባል ነበርን፡፡ እሳቸው ኢህአዴግ ስለሆኑ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆኑ እኔ ተቃዋሚ ስለሆንኩ እስር ቤት ገባሁ፡፡ ለምንድነው ፍርድ ቤት የማይቀርቡት? ባለፈው የወሰናችሁትንስ በየትኛው የስነስረአት ህግ ነው የሻራችሁት? በውሳኔያችሁ አስከፍታችሁናል፡፡ እኔ በአብዛኛው እዚህ የምመጣው ለራሴ ብዬ አይደለም፡፡ ፍትህ በኛ ይገኛል በኛ ይመጣል ብለን ነው ልጆቻችንን እና ህይወታችንን ትተን እዚህ የገባነው፡፡ የፍርድ ቤትን ኢንዲፔንደንሲ የናንተ የዳኞችን ኢንዲፔንደንሲ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት የተትርመሰመሰ ዲሞክራሲ አይገባትም፡፡ አንዱ የሚጎዳባት አንዱ የሚንደላቀቅባት ሃገር አይሁን፡፡ “

ዳኛ ዮሐንስ፤ ችሎቱ ዝግ እንዳልሆነ፣ ማንም ችሎቱን ተከታትሎ ታዝቦ የሚገምተውን ገምቶ መሄድ እና የተከታተለውን ነገር ሚዛናዊ አድርጎ መዘገብ እንደሚችል ነገር ግን አዛብቶ ማቅረብ በህግ እንደሚያስቀጣ ፣ በሞባይል ፎቶዎች እየተቀረፁ ከግል ጥቅም በዘለለ በሶሻል ሚዲያ ላይ እየተለቀቁ እንደሆነ፣ ችሎት ሲታደም የነበረውን ልጅ ሞባይሉን እንዲያሳይ የተጠየቀው ከዚህ አንፃር መሆኑን [ዳናው ልጁን ሞባይሉን ተቀብለው ፎቶዎች ካዩ በኋላ የተነሳ ፎቶ እንደሌለ አረጋግጠው የመለሱለት ሲሆን ፤ ፎቶእንዳነሳ ነገር ግን ማግኘት እንዳልቻሉ ለችሎት ተናግረው ነበር]፣ የችሎቱን ድባብ የማስጠበቅ ሃላፊነት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡ ከችሎት ስትወጣ ጋዜጠኛ ነሽ ወይ ተብላ የተጠየቀችውን በተመለከተ ፤ ጥያቄውን ያቀረቡላት ችሎቱ ሳያልቅ አቋርጣ እየወጣች ስለሆነ ጋዜጠኛ ከሆነች ችሎቱ ስላላለቀ የተጓደለ ነገር እንዳትዘግብ በሚል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ዳኛው በክርክር ሂደት ውሳኔ እስካልተሰጠበት ድረስ ወደ ኋላም ወደፊትም እየሄዱ እንዳይሰሩ የሚከለክል ህግ እንደሌለ ገልፀው ከጠበቆችም ከአቶ በቀለም የተሰጠውን ሃሳብ ሳይቀበሉ በውሳኔያቸው በመፅናት ለአዳር የተያዘው ቀጠሮ እንደተተበቀ መሆን በመግለፅ የእለቱን ችሎት አጠናቀዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *