‹‹ታዳጊ-ወጣት ጥፋተኞች››  ክፍል 1

በጌታቸው ወርቁ

አዲስ አበባ/ኢትዮጵያ፡-

ከኒው ዮርክ እና ከጄኔቫ ከተሞች በመቀጠል በዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ መናኸሪያነት የምትታወቀው አዲስ አበባ/ኢትዮጵያ፣ በእንግዳ ዓይን ለሚመለከታት የአገሩን የዲፕሎማሲ ሥራ ሊከውን የተመደበ የውጭ አገር ዲፕሎማትም ሆነ፣ በዓለም አቀፍ ሥራ የተሰማራ የሌላ አገር ሰው፣ አሊያም ደግሞ ለደርሶ ተመላሽ አገር ጎብኚ እንግዳ (ቱሪስት)፣ ሰብዓዊ ምልከታ የሚጎረብጥ የዘወትር የጎዳና ላይ ትዕይንት አላት- በጎዳና ላይ የተጣሉ የጎዳና ልጆች በማኅበረሰብ የተገፋ አሳዛኝና ሰቅጣጭ የአደባባይ የጎዳና ላይ ኑሮ፡፡  የከተማዋ አስተዳደር በተለያዩ ምክንያቶች ከወላጆቻቸው፣ ከቤተሰቦቻቸው፣ ከማኅበረሰባቸው ተለይተውና ርቀው በጎዳና ሰቅጣጭ ህይወት ላይ የተገፉ ታዳጊ-ወጣቶችን (junior youth) ህይወት የሚታደግበት አሰራር የለውም፡፡ የጎዳና ህይወት የቀን ተቀን ትርዒት፣ ከመዲናዋ አዲስ አበባ ከተማ ባሻገር ባሉ በየክልሎች ዋና ከተሞች ሀዋሳ፣ አዳማ፣ ሻሸመኔ፣ ባህር ዳር፣ ደብረ ብርሃን፣ ድሬዳዋ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ ከተሞች ሁሉ በየጎዳናው ዘወትር ይታያል፡፡

  ከፀባይ ማረሚያ ያመለጠው የዳዊት ታሪክ

ዳዊት አበራ (ሥሙ የተቀየረ) በአዲስ አበባ ስታዲየም ዙሪያ በሚገኙ ጎዳናዎች ላይ ህይወቱን የመሠረተ የ13 ዓመት ታዳጊ ወጣት ነው፡፡ በመዲናዋ ከሚገኘው ‹‹በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ በወንጀል ነክ ነገር ውስጥ ገብተው የተገኙ ህፃናት ማቆያና ተሀድሶ ተቋም›› በተለምዶ (ጸባይ ማረሚያ) ተብሎ የሚጠራውን ተቋም፣ ነሐሴ 28 ቀን 2010 ዓ.ም ከለሊቱ 5፡30 ሰዓት ላይ አምልጠው ከወጡ ሃያ አምስት (25) ‹‹ታራሚ›› ልጆች መካከል አንዱ ነው፡፡ እኔ ሳገኘው የውሃ ላስቲክ ውስጥ ይዞ የሚስበው ‹‹ማስቲሽ›› (አንዳንዶች ቤንዚን ያራሰውን ጨርቅም ይስባሉ/ያሸታሉ) ቃና፣ የአካባቢውን አየር የሚበክል ነበር፡፡

በአዲስ አበባ ልደታ አካባቢ የሚገኘው የታዳጊዎች ማረሚያ ቤት ምንም ዓይነት ተቋማዊ ገጽታ የለውም። ከውጭ ለሚያየው አንድ ተራ የመኖሪያ ግቢ ይመስላል። የተቋሙን ሥም መግለጫ ሥያሜም አልተለጠፈበትም።

ዳዊት ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ጎዳና ህይወት ሊወጣ የቻለው በወላጅ አባቱ እና ወላጅ እናቱ ትዳር መፍረስ ምክንያት በ11 ዓመቱ እንደሆነ ይናገራል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የላዳ ታክሲ ሾፌር የሆነው አባቱ እና የአዲስ አበባ ፖሊስ አባል የሆነችው እናቱ፣ እርሱ ባልተረዳውና በማያውቀው ሁኔታ ትዳራቸው ፈርሶ፣ የቤት ዕቃ ተከፋፈሉና አባት ጉለሌ ክፍለ ከተማ ከሚገኘው የመኖሪያ ቤታቸው ሲወጣ እናት ልጇዋን ይዛ አባቱ በወር ለልጁ በሚያደርግላት ተቆራጭ እና በወር ገቢዋ ታግዛ ለተወሰነ ጊዜ ኑሯቸውን እንደ ቀድሞው ቀጥለው ነበር፡፡ “ሆኖም በሂደት እናቴ ሌላ የወንድ ጓደኛ ያዘች” ይላል ዳዊት:: በመጨረሻም ይህ ሰው በተለምዶ (ባህላዊ መንገድ) ለእናቴ ሁለተኛ ቧሏ ሆኖ ወደ ቤታችን ሲቀላቀል፣ ከእኔ ጋር አልተመቻቸንምና እኔን ከአስኮ ራቅ ብሎ ኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከሚገኝ የገጠር መንደር አያቶቼ (የእናቱ አባትና እናት) ጋር ቀላቀለችኝ ይላል፡፡ አያቶቼ እና አክስት-አጎቶቼ ለጊዜው በፈገግታ ቢቀበሉኝም፣ እየቆየ ከትምህርቴ ይልቅ በቀን ተቀን የግብርና ህይወታቸው ላይ ዋና አጋዥ እንድሆን አደረጉኝ ይላል፡፡

“የእኔን ወደ ትምህርት ቤት መሄድ አይፈቅዱም፤ ብዙ ጊዜ እንድቀር ስለሚያደርጉኝ በትምህርቴም ተዳከምኩ፡፡ ሲብስብኝ ይህንን ሁኔታ ለአባቴ ደውዬ ባሳውቀውም፣ ምንም ሊያደርግልኝ አልቻለም፡፡ ነገሮች ሲከፉብኝ ሳላስበው በትምህርት ቤትም ሆነ በአካባቢዬ ተናዳጅ፣ አመጸኛና ተደባዳቢ ሆንኩ፤ እናም በመምህራኖቼ ‹‹ወላጅ አምጣ›› ሲደጋገምብኝ ወንድ አያቴ ትምህርቴን እንዳቋርጥ አደረጉኝና በእረኝነት ሥራ ላይ አሰማሩኝ“

አንድ ቀን በዓመት በዓል ማግስት እናቴ ቤተሰቦቿን ለመጠየቅ መጥታ፣ ከሴት አያቴና ከአክስቶቼ ጋር ሲያወሩ፣ አባቴ ከሌላ ሴት ጋር ግንኙነት እንደጀመረ፣ ለእኔ ተቆራጭ ማድረግ ማቆሙን በቁጭት ስትናገር ሰማሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ለእርሱ ደውዬለት አላውቅም፡፡ ቀኑን ሙሉ ከብት የመጠበቅ የእረኝነት ኑሮ ሲከብደኝና በረባ ባልረባው ስህተት ዘወትር ከወንድ አያቴና አጎቶቼ የሚደርስብኝ የቀን ዱላ፣ ከትልልቆቹ አክስቶቼ የሚገጥመኝ የምሽት የታፋ ላይ ቁንጥጫና ግልምጫ ሲመረኝ ከዚህ ህይወት ለመውጣት ወሰንኩ፡፡

አንድ ቀን የዘመን መለወጫ በዓል ቀን ሲቃረብ፣ የአያቴን አንድ ሙክት በግ እና የአንዷን አክስቴን ሁለት ዶሮዎች ይዤ ወደ አስኮ ገብርኤል አካባቢ በመምጣት ከአንድ ከምግባባው ትልቅ ልጅ ጋር ተሻርከን ሸጥንና ምሳ ጋብዞኝ ሰባት መቶ ሃያ አምስት ብር አካፈለኝ፤ በጊዜው እንዲህ አይነት ብዙ ብር አይቼም ሆነ ይዤ ስለማላውቅና የሚያልቅ ስላልመሰለኝ ወደ መሐል አዲስ አበባ ገባሁ፡፡ ነገር ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ ኪሴ ባዶ ሆነ፡፡ ሲርበኝ የምጠጋው የማውቀው የዘመድ ቤት ስላልነበረኝና ተቀብሎ የሚያሳድገኝ ህፃናት ማሳደጊያ ስለሌለ የተወሰነ ጊዜ የሸቅል ሥራ (ሸክም) ሞከርኩና ሲመረኝ ወደ ጎዳና ህይወት ወጣሁ፡፡

“መጀመሪያ የተሰማራሁት ጊዮርጊስ ፒያሳ አካባቢ ነበር፡፡ እዛ ግን ከነባር ጎዳና ተዳዳሪዎች ጋር አልተስማማሁም፤ ምናልባትም የሚያውቀኝ ሰው በአጋጣሚ በመኪና ተሳፍሮ ሲወርድ ሊመለከተኝ ይችላል በማለት ወደ ለገሃር እና ስታዲዮም ዙሪያ አመራሁ፣ እናም እዛው ከተምኩ” ይላል ልጅ ዳዊት፡፡

(ዳዊት የሚናገረው ቋንቋ ቃላት በተለምዶ የአራዳ ወይም የዱርዬ ቋንቋ የሚባለውን ዘዬ ነው የሚጠቀመው፤ እርሱ የሰጠኝን መረጃ ይዤ በተለምዶ ጸባይ ማረሚያ የሚባለው ቦታ ውስጥ ያሉ የእርሱ ብጤ ‹‹ወጣት ጥፋተኞችን›› ሳናግርም ይኸው የዳዊት የቋንቋ አጠቃቀም ነው በብዙዎቹ አንደበት የጠበቀኝ፡፡) የዳዊት ቀጥተኛ አንደበት ሲደመጥ እንደሚከተለው ነበር፡-

‹‹ከጓደኞችህ ጋር ተማክረህ ከጸባይ ማረሚያ ለምን አምልጣችሁ ወጣችሁ፤ ከጎዳና ህይወት ‹‹ጸባይ ማረሚያ›› አይሻልም?

ዳዊት፡- ቦታው አይነፋም! አንተ ውስጡን ስለማታውቀው ነው፡፡ አሰልቺ፣ አታካች ለሰው ልጅ ምንም የማይመች ማጎሪያ ነው፡፡ እረ ቦታው አይነፋም!

ቦታው አይነፋም ማለት?

ደንበኛ ሸቤ (እስር ቤት) ነው!

‹‹ጸባይ ማረሚያ›› ተቋም አይደለም እንዴ?

እንደርሱ የሚሉት ሲያንቆለጳጵሱት ነው!

ማነው ያሳሰረህ?

እሙካ ናት! (እናቴ)

ለምን?

ጸባዬ እንዲሻሻልና እንድስተካከል!

‹‹ጸባይ ማረሚያ›› ተቋም ጸባይህ እንዲሻሻልና እንዲስተካከል አልረዳህም?

እንዲያውም በእልክ አብሰውኝ ነው የወጣሁት፡፡ ከዚያች ጠባብ ግቢ ውጪ (የፍርድ ቤት ቀጠሮ ወይም ህክምና) ከሌለህ የትም አያንቀሳቅሱህም፤ በትንሽ ጥፋት ይጋረፋሉ፤ ይደበድቡኃል፤ ከልጆች ጋር ከተጣላህ ድንጋይ ላይ ያንበረክኩኃል፤ በስፖርት ይቀጡኃል፤ ለተወሰነ ጊዜም ለብቻ አግልለው ያስቀምጡሃል፤ ቦታው ከባድ ነው- አይነፋም ብዬሃለሁ እኮ፡፡

እነማን ናቸው ስታጠፉ የሚደበድቧችሁ?

መግዚቶችም፣ ጥበቃዎችም፣ ሁሉም ናቸው አይለዩም፤ ሶሻል ወርከሮቹና የህክምና አባላቶች ግን ይሻላሉ እነርሱ አይማቱም፤ ይመክራሉ፡፡

በመደብደብህ የደረሰብህ ነገር አለ?

ጣቴን በዱላ ሰብሮኛል፤ (ተጎጂ አውራ ጣቱን እያሳየኝ) ወገቤን በውሃ ጎማ ለምጦኛል (ሰውነቱ ላይ የወጣውን የግርፊያ ሰምበር እያመላከተኝ)

ማነው የመታህ?

አንድ ገገማ ጠባቂ ነው፡፡ ጥምድ አድርጎኝ ነበር፡፡ ከዛ ያላደረግኩትን ያወራል፤ ሊያመልጥ እየሞከረ ነው ብሎ ለሌሎች ያሳብቅብኛል፡፡ (ዳዊት ይህንን የፀባይ ማረሚያ አያያዝ ሸሽቶ ከ25 ጓደኞቹ ጋር አምልጦ ጎዳና ላይ ይገኛል፡፡)

Leave a Reply

Your email address will not be published.