‹‹ታዳጊ-ወጣት ጥፋተኞች››  ክፍል 2  

በጌታቸው ወርቁ

 

አዲስ አበባ/ኢትዮጵያ፡-

የኤደን ታሪክ

በአዲስ አበባ/ኢትዮጵያ በርካታ ታዳጊ ወጣቶች በቤተሰብ መለያየት፣ ባልተረጋጋ የቤተሰብ ህይወት (ግጭት)፣ በቤተሰብ ድህነትና በቤተሰብ ምጣኔ አለማወቅ፣ በሕገወጥ የህፃናት ዝውውር፣ በጎዳና ላይ ኑሮ ውስጥ በመወለድ፣ በሱሰኝነት፣ ኋላ ቀርነትና የማኅበረሰቡ ልጆችን አያያዝና አስተዳደግ ላይ ያለው ተባእታዊ (ፓትሪያርኪያል) የግንዛቤ ጉድለት (Poor Parenting style)፣ በአቻ ግፊት፣ እና በተለያዩ ተጽእኖዎች ሳቢያ ወደ ጎዳና ህይወት እንደሚወጡ እንዲሁም ያፈነገጡ ባህሪያት እንደሚያሳዩ የማህበረሰባዊ ሳይንስ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡

ኤደን ማቴዎስ (የአባት ሥም የተለወጠ) ‹‹በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ በወንጀል ነክ ነገር ውስጥ ገብተው የተገኙ ህፃናት ማቆያና ተሀድሶ ተቋም›› በተለምዶ ‹‹ጸባይ ማረሚያ›› ውስጥ በአሁኑ ጊዜ የምትገኝ የ14 ዓመት ታዳጊ ወጣት ናት፡፡ ተወልዳ ያደገችው በደቡብ ክልል ሀዋሳ ከተማ አንድ ቀን ከጎረቤት ልጅ ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ተደባድባ ልጅቷን በመፈንከቷና ጉዳት በማድረሷ በወጣት ጥፋተኝነት ተከሳ፣ ብይን ተሰጥቶባት ወደ ጣቢያ እንደወረደች ነግራኛለች፡፡ በፍርድ ሂደትም (የስምንተኛ ክፍል ትምህርቷን መቀጠል እንዲያስችላት ) በሚል ከሀዋሳ ወደ አቃቂ ቃሊቲ (ገብርኤል ቤ/ክርስቲያን) አካባቢ ያለ ጣቢያ ተዛውራ፣ ከዚያም እድሜዋ ከግምት ገብቶ ወደ ‹‹ጸባይ ማረሚያ›› ወርዳለች፡፡ በአሁኑ ጊዜ (ህዳር 2011 ዓ.ም) በተቋሙ ውስጥ ከሚገኙ 97 ወንዶችና 10 ሴቶች መካከል አንዷ ነች፡፡

ልደታ አካባቢ የሚገኘው የታዳጊዎች ማረሚያ ቤት ጊቢ በጣም የላላ ጥበቃ ያለው እና ለአገልግሎቱ የተመቻቸ ሳይሆን እንደአንድ መኖሪያ ቤት እንደነገሩ የተከለለ ነው።

እኔ በዚህ ተቋም ውስጥ በተገኘሁበት ጊዜ (ዓርብ ህዳር 14 ቀን 2011 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ) የተቋሙ የህክምና ሠራተኞች የኤች አይ ቪ/ ኤድስ ነፃ ምርመራ በፈቃደኝነት አድርገው ስለነበር፣ ይህን ምክንያት አድርገው የልጆቹን ማህበራዊ ህይወት ለማጠናከር በሚል በደጋፊ አካላት ለስላሳ መጠጦች፣ ድፎ ዳቦ እና ቆሎ እየተመገቡ ልዩ ልዩ ስፖርታዊ ትዕይንቶች ከቀረቡ በኋላ ሙዚቃ ተከፍቶ የተወሰኑ ጭፈራና ዳንስ የሚችሉ ልጆች ተጋበዘው ነበር፡፡ኤደን ከተወዳዳሪዎች መካከል አንዷ ነበረች፡፡ ከውድድሩ መልስ ጠጋ ብዬ (የተቋሙ ሠራተኞች ሳይሰሙ)፡-

የተቋሙ አያያዝ ለልጆች እንዴት ነው፤ ልጅነታችሁን ከግንዛቤ ያስገባል፤ መብታችሁ ይጠበቃል? ስል ጠየቅኳት

ኤደን፡- (የተቋሙ ሠራተኞች እንዳይመለከቷት ዘወር- ዘወር ብላ መልከት ካደረገች በኋላ) እስር ቤት ውስጥ ደግሞ ምን መብት አለ?! (በማለት እኔኑ መልሳ ጠየቀችኝ፡፡)

የጓጓሽለትን የስምንተኛ ክፍል ትምህርት እዚህ በተሟላ ሁኔታ እያስቀጠሉሽ ነው?

ወይ ትምህርት! ፌዝ ነው- ቀልድ፤ ከጠዋቱ 2፡30 እስከ 6፡00 ሰዓት ክፍል እንገባለን፤ ብዙ ጊዜ አስተማሪዎች ይቀራሉ፤ ሥራም የለቀቁ አሉ፡፡ ከሰአት በኋላ ሁልጊዜ እንዲሁ ሜዳ ላይ ተበትነን እንደ ከብት እየጠበቁን ነው ያለነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ በመኪና እጥረት የፍርድ ቤት ቀጠሮም ያልፈናል፤ በአግባቡ አይወስዱንም፡፡ እኔ ትምህርቴን ለመቀጠል እችላለሁ ብዬ ነበር ወደ እዚህ እንድዘዋወር የጠየቅኩት፤ እዚህ ወንድሜ እና አጎቶቼም ስላሉ እየመጡ ይጠይቁኛል የትምህርት ጊዜዬ አይቃጠልም ብዬ ተስፋ በማድረግ ነበር፤ ነገር ግን ቤተሰብ በሳምንት ሁለት ቀን (ማክሰኞና ዓርብ፤ ከስምንት እስከ አስር ሰዓት) ለ30 ደቂቃ ብቻ እንዲያነጋግረን ነው የሚፈቅዱት፡፡

ቤተ-መጻሕፍት ትጠቀማላችሁ፤ ለማጥናት?

ትቀልዳለህ?! ወፍ የለም፡፡

ወፍ የለም ስትይ?

የለም፤ አይሰራም፡፡

ገላችሁን መታጠቢያ ቦታስ አላችሀ?

አዎን፤ በሳምንት አንድ የገላ፣ አንድ የልብስ ሳሙና ይሰጡናል፤ ልብሳችንንም እናጥባለን፡፡ አሁን አሁን ለሴቶች በየወሩ ‹‹ሞዴስም›› ይሰጡን ጀምረዋል፡፡

ሰብዓዊ መብታችሁ ይከበራል?

ታሾፋለህ መሰል፤ እዚህ ውስጥ …

(እኔ እና ኤደን በማውራት ላይ ሳለን፣ አንድ የማህበራዊ ባለሙያ ወደ አጠገባችን መጥታ ‹‹ልጆቹን አሁን ማናገር አትችልም፤ ወረቀት ካመጣህ በኋላ ነው ማናገር የምትችለው›› በማለት ከገሰጸችኝ በኋላ፣ ንግግርችንን አስቆመች፤ ኤደንንም በዓይን የሆነ መልዕክት ነገረቻት፤ ኤደን እኔ ካለሁበት ራቅ አለች፡፡ )

Leave a Reply

Your email address will not be published.