አስቸኳይ የሰላም ጥሪ!

በቅድሚያ ይህንን የሰላም ጥሪ ጋዜጠኞች በተሰበሰቡበት ለማድረግ ዛሬ ጠዋት አቅደን የነበረ ቢሆንም፣ ማንነታቸውን ያልገለጹ ነገር ግን የመንግሥት አካል ነን ያሉ ግለሰቦች፣ ባልተገለጸ ምክንያት ጋዜጣዊ መግለጫውን መስጠት እንደማይፈቀድልን ነግረውን አስተጓጉለውብናል። ይህንን ክልከላ ያዘዘው አካል ማን እንደሆነ ብንጠይቅም መልስ አላገኘንም። የዚህ መግለጫ አዘጋጅ አገር በቀል ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እስከምናውቀው ድረስ፣ ለመንግሥት የፀጥታ አካላት ቅድሚያ ማሳወቅ የሚጠይቁት የአደባባይ ሰልፎች ብቻ ናቸው። ይህ ዓይነቱ አሠራር የሕግ የበላይነትን የሚፃረር ከመሆኑም ባሻገር የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ለሰላም ሊጫወቱ የሚገባቸውን ድርሻ ይነፍጋል። ስለዚህ በድርጊቱ ማዘናችንን እና እንዲታረም እያሳሰብን የመግለጫውን ፍሬ ሐሳብ እናነባለን።

አስቸኳይ የሰላም ጥሪ!

ከአገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች

ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በፊት በትግራይ ክልል ተቀስቅሶ ወደ ተጎራባች አማራ እና አፋር ክልሎች የተዛመተው ጦርነት በብዙ መልኩ አገራችንን እና ሕዝባችንን ከፍተኛ ዋጋ አስከፍሏል። በጦርነቱ በርካታ ንፁኃን ዜጎች ለዘፈቀደ ግድያ፣ በተለይም ሴቶች ለፆታዊ ጥቃቶች የተዳረጉ ሲሆን፥ ሌሎችም ግጭቶችን በመሸሽ በተለያዩ መጠለያ ሥፍራዎች እንዲቆዩ እና አስከፊ ለሆኑ ሰብዓዊ ቀውሶች እንዲዳረጉ ሆነዋል። በጦርነቱ አካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው፣ ንብረቶቻቸው የወደሙባቸው እና ቤተሰቦቻቸው የተበተኑባቸው ኢትዮጵያዊያን ዛሬም ከጉዳታቸው አላገገሙም። በትግራይ ክልል እና ጦርነቱ በተስፋፋባቸው ሌሎች ሥፍራዎች የሚገኙ ሰላማዊ ሰዎች በተራዘመው ጦርነት ምክንያት ተቋርጠው በቆዩት መሠረታዊ የአገልግሎት አቅርቦቶች እንዲሁም የሰብዓዊ ዕርዳታዎች በበቂ ሁኔታ አለመዳረስ ሳቢያ ለከፋ ስቃይ እና እንግልት መዳረጋቸው እርግጥ ነው። 

ከዚህ ጥሪ ግርጌ ፊርማችንን ያኖርነው አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የዛሬ ዓመት ተመሳሳይ የሰላም ጥሪ ማድረጋችን ይታወሳል። ዘንድሮም፣ በተፋላሚ ወገኖች መካከል ሰብዓዊነትን መሠረት ያደረገ የተኩስ አቁም ሥምምነት መደረጉ እና ተፋላሚ ወገኖች ለሰላም ድርድር ፍላጎት ማሳየታቸው ትልቅ ተስፋ እንድንሰንቅ አድርጎን ነበር። ይሁንና ይህ ተስፋችን ከጫፍ ሳይደርስ ከሳምንታት በፊት የተደራዳሪ ወገኖች መካከል የከረሩ የቃላት ልውውጦች ከቁጥጥር ውጭ ወጥተው እንደገና አዲስ ጦርነት መቀስቀሱ እጅግ አሳዝኖናል።

ከሰሜኑ ጦርነት ባሻገር በምዕራብና ደቡብ ኦሮሚያ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ እና በአንዳንድ የደቡብ ክልል አካባቢዎች ግጭቶች እየተካሔዱ ነው። እነዚህ ግጭቶች የበርካታ ዜጎችን ሕይወት እየቀጠፉ እና የአካል ጉዳት እያስከተሉ ነው። ሴቶች መደፈርና ሌሎችም ዘግናኝ ጥቃቶች እየተፈፀሙባቸው ይገኛል። በርካታ ኢትዮጵያውያንም በግጭቶቹ ምክንያት ከቀያቸው ተፈናቅለው ዕርዳታ ጠባቂ ሆነዋል። 

ግጭቶቹ መሠረታዊ የዜጎችን በሕይወት የመኖር፣ የአካል ደኅንነት፣ ንብረት የማፍራትና የመንቀሳቀስ መብቶችን የነፈጉ ከመሆኑም ባሻገር፥ የአገርን ኅልውናን የሚፈታተኑበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል። እነዚህ ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ ካልተፈቱ አገራችን መውጣት የማትችልበት ቀውስ ውስጥ ትገባለች የሚል ስጋት አለን።

ስለሆነም፣ እኛ የዚህ ግልጽ የሰላም ጥሪ አቅራቢዎች፣ ከላይ የዘረዘርናቸው ፈተናዎች በመጪው ዓመት ተቀርፈው ለማየት፣ የሚከተሉትን አስቸኳይ ጥሪዎች እናስተላልፋለን፤

1ኛ) በሰሜኑ የአገራችን ክፍል በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልል ያለው ጦርነት እና በሌሎችም አካባቢዎች ያሉ ግጭቶች በአስቸኳይ ቆመው፣ ሐቀኛ፣ ሰላማዊና የግጭቶቹ ተሳታፊ አካላትን በሙሉ ያካተቱ የእርቅ ንግግሮች እንዲጀመሩ፤

2ኛ) በትግራይ እና ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች የተቋረጡ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አገልግሎቶች በአፋጣኝ እንዲጀመሩ እና ዕርዳታ ያለ እንቅፋት እንዲደርስ፤ 

3ኛ) የፆታ ጥቃትን የፈፀሙ የተዋጊ አካላትን ጨምሮ ሌሎችም የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን ያደረሱ አካላት ላይ ተጨማሪ ምርመራ ተደርጎ የተጠያቂነት እርምጃ እንዲወሰድ፤ 

4ኛ/  በግጭቶቹ ተጎጂ የሆኑ ሴቶች እና ሕፃናት እንዲሁም ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች ፈጣን የሕክምና እና የማኅበረ ሥነ ልቦናዊ ድጋፍ እንዲደረግላቸው፣ እንዲሁም በግጭቶች ተሳታፊ ያልሆኑ ንፁኃን ተጋላጮች በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ የጥበቃ ከለላ እንዲደረግላቸው፤

5ኛ) ብሔር ተኮር ጥቃቶችና አግላይ ድርጊቶች በአስቸኳይ እንዲቆሙ እንዲሁም በፌዴራሉ እና ክልል መንግሥታት በቁጥር አነስተኛ ለሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎች (minorities) እና ግፉዓን (marginalized) ዜጎች የልዩ ጥበቃ ስርዓት እንዲዘረጋ፤ 

6ኛ) ተፋላሚ አካላትና ደጋፊዎቻቸው ከማንኛውም የጦርነት ፕሮፓጋንዳ እና የግጭት አባባሽ ንግግሮች እንዲሁም ድርጊቶች እንዲቆጠቡ፤

7ኛ) በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ያሉ መገናኛ ብዙኃን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የእምነት ተቋማት፣ የፖለቲካ ኃይሎች እና አክቲቪስቶች ድምፃቸውን ለሰላም እና ለእርቅ ብቻ እንዲያውሉ፤

8ኛ) የተጀመረው የአገራዊ ምክክር ሒደት ሁሉን አካታችና አሳታፊ፣ ግልጽ እንዲሁም የአገሪቱን የአጭርና የረዥም ጊዜ ችግሮች ለመፍታት የብዙኃንን ይሁንታ ያገኘ አካሔድ እንዲከተል ጥሪ እናቀርባለን። 

ይህንን የሰላም እና የተጠያቂነት ጥሪ ያስተላልፍነው የአገር በቀል ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችም በበኩላችን ለግጭቶች በሰላማዊ መንገድ መፈታት እና ለሰላም ግንባታ፣ የበኩላችንን ለመወጣት እና የሰላም መድረኮችን ለማመቻቸት እንዲሁምማኅበረ ሥነ ልቦና ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናችንን እንገልጻለን። 

የዚህ የሰላም ጥሪ ፈራሚ ድርጅቶች የሚከተሉት ነን፣ 

 1. አድቮኬሲ ሴንተር ፎር ዴሞክራሲ ኤንድ ዴቨሎፕመንት (ACDD)
 2. ስብስብ ለሰብአዊ መብቶች በኢትዮጵያ (AHRE) 
 3. የአማራ ጋዜጠኞች ማኅበር (AJA)
 4. የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (CARD)
 5. ሴንተር  ፎር ዴሞክራሲ ኤንድ ሂዩማን ራይትስ (CDHR)
 6. የዲሞክራሲያዊ ማህበረሰብ ማዕከል (CDS)
 7. የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ኅብረት (CEHRO)
 8. የሰብአዊ መብቶች እና የ ሰላም ግንባታ ማዕከል (CHPB)
 9. ዲሊጀንስ ፎር ሂዩማን ራይትስ ፕሮቴክሽን (DHRP)
 10. ኢምፓወር ጄኔሬሽን ቻሪቲ አሶሴሽን (EGCA)
 11. የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር (EGE)
 12. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል(EHRDC)
 13. የኢትዮጵያ ኢኒሼቲቭ ፎር ሂዩማን ራይትስ (EIHR) 
 14. ኢምፓቲ ፎር ላይፍ ኢንትግሬትድ ደቨሎፕመንት አሶሲዬሽን (ELiDA)
 15. ዕንቁዋ ታብራ ውሜን ኢምፓወርመንት
 16. የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር (EWLA)
 17. ኢትዮጵያን ዉሜን ራይትስ ዎች (EWRA)
 18. ኢስት አፍሪካን ኢኒሼቲቭ ፎር ቼንጅ (I4C)
 19. ኢንተርአፍሪካ ግሩፕ – ኢትዮጵያ (IAG)
 20. ኢኒሼቲቭ ፎር ፒስ ኤንድ ዴቨሎፕመንት (IPD) 
 21. የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች (LHR)
 22. ምስጋና የሕፃናትና ቤተሰብ ልማት ማኅበር (MCFDA)
 23. ሙጄጄግዋ ሎካ ዉሜንስ ደቨሎፕመንት አሶሴሽን (MLWDA)
 24. የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት (NEWA)
 25. ኒው ሚሌኒየም ዉሜን ኢምፓወርመንት ኦርጋናይዜሽን (NMWEO)
 26. ኦርጋናይዜሽን ፎር ገልስ አደልትስ ኤንድ አድቮኬሲ (OGAA)
 27. አወንታ ምላሽ ሰጪ ህጻናትና ወጣቶች ልማት በኢትዮጵያ (PRCYDE)
 28. ፕሮጃይኒስት (Progynist)
 29. ሳራ ፍትሕ ለሁሉም የሴቶች ማኅበር 
 30. ሲቄ ዉሜንስ ዴቨሎፕመንት አሶስዬሽን (SWDA)
 31. ሴታዊት ንቅናቄ (Setaweet Movement)
 32. ትምራን (Timran)
 33. የኢትየጵያ ሴቶችና ሕፃናት ማኅበራት ኅብረት (UEWCA)
 34. የሴቶች ህብረት ለሰላምና ለማህበራዊ ፍትህ (WAPS)
 35. ሴቶች ይችላሉ (WCDI)

Center for Advancement of Rights and Democracy (CARD)

Making Democracy the Only Rule of Game!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

*

code