አቶ ማሙሸት አማረ የተመሰረተባቸውን የሽብርተኝነት ወንጀል ክስ ተከላከሉ ተብለዋል፡፡

የመኢአድ የቀድሞው ሊቀመንበር አቶ ማሙሸት አማረ በፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ የተመሰረተባቸውን የሽርተኝነት ወንጀል ክስ ይከላከሉ ሲል የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ህዳር 19/2010 ዓ.ም በዋለው ችሎት በይኗል፡፡

ፍ/ቤቱ መዝገቡን ለዛሬ ቀጥሮ የነበረው የአቃቤ ህግ ማስረጃን መርምሮ ብይን ለመስጠት ሲሆን፣ በዚህም ተከሳሹ የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4 ስር የተመለከተውን በመተላለፍ የቀረበባቸውን የወንጀል ክስ ከሳሽ አቃቤ ህግ እንደክሱ አቀራረብ በሚገባ አስረድቷል ወይስ አላስረዳም የሚለውን ጭብጥ ይዞ እንደመረመረ በመግለጽ ተከሳሹ ክሱን እንዲከላከሉ ሲል ብይን ሰጥቷል፡፡

ፍ/ቤቱ በአቃቤ ህግ በኩል በጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ አንቀጽ 14(1) እና 23(1) መሰረት የተሰበሰበ ነው የተባለ የሰነድ ማስረጃ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ እንደተገኘ ገልጾ  ያቀረበውን ሪፖርት በማስረጃ መመርመሩን አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል ተከሳሹ በሰነድ አስተያየቱ ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት ኤጀንሲ የተገኘው የስልክ ልውውጥ መሆኑን ጠቅሰው ንግግር ተደረገባቸው የተባሉ ስልክ ቁጥሮች የተከሳሹ ስለመሆናቸው ማስረጃ ባለመቅረቡ በዚህ ሁኔታ ተገኘ የተባለው የአቃቤ ህግ ማስረጃ በማስረጃነት ሊያዝ አይገባም የሚለውን ነጥብም ፍ/ቤቱ እንደተመለከተው ገልጹዋል፡፡

ሆኖም የአቃቤ ህግ ማስረጃ ይዘት ሲታይ ከሳሽ እንደክሱ አቀራረብ ተከሳሹ ፈጽመውታል የተባለውን ድርጊት በሚያስረዳ መልኩ በስልክ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ከሚገኙ የሽብር ድርጅት አባላት ጋር የተለዋወጧቸውን መልዕክቶች በሚያሳይ ሁኔታ በበቂና በሚገባ ማስረዳቱን በመግለጽ ፍ/ቤቱ ተከሳሹ የቀረበበትን ክስ፣ ማለትም የጸረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4 ስር የተመለከተውን እንዲከላከሉ ሲል በሙሉ ድምጽ ብይኑን አሰምቷል፡፡

ፍ/ቤቱ በተከሳሽ በኩል አሉኝ የሚሏቸውን መከላከያ ማስረጃዎች አቅርበው እንዲያሰሙ በሚል ለጥር 08/2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

ተከሳሹ አቶ ማሙሸት አማረ ከመጋቢት 20/2009 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፣ ለቀረበባቸው የሽብር ክስ መነሻ የሆነው ደግሞ በ2008 ዓ.ም በኦሮሚያና አማራ ክልሎች አንዳንድ አካባቢዎች ተቀስቅሶ የነበረው ህዝባዊ ‹አመጽ› እንዲቀጥል አርበኞች ግንቦት ሰባት ከተባለና በኢትዮጵያ ፓርላማ ሽብርተኛ ተብሎ ከተፈረጀ ድርጅት ጋር ግንኙነት በማድረግ፣ አባል በመሆንና አባላትን በመመልመል፣ የገንዘብ ድጋፍ በመቀበል፣ ባንክን ጨምሮ የመንግስትን ተቋማት ለመዝረፍና ተያያዥ ድርጊቶችን ለመፈጸም ማቀድ፣ ማሴርና መዘጋጀት ወንጀል ለመፈጸም የጸረ ሽብር አዋጁን አንቀጽ 4 ተላልፈዋል የሚል ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *