አቶ ማሙሸት አማረ ያቀረቡት የክስ መቃወሚያ ሙሉው ውድቅ ተደርጓል:: (ጥቅምት 24/2010)

የሽብር ክስ የቀረበባቸው የመኢአድ የቀድሞው ፕሬዚዳንት አቶ ማሙሸት አማረ ጥቅምት 13/2010 ዓ.ም ለፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ያቀረቡት አራት ገጽ የመጀመሪያ ደረጃ የክስ መቃወሚያቸው ሙሉ በሙሉ ውድቅ ተደርጓል፡፡

ዛሬ ጥቅምት 24/2010 ተከሳሹ ቀደም ብለው ባቀረቡት መቃወሚያ ላይ ብይን የሰጠው ፍ/ቤቱ የተከሳሽን መቃወሚያ ሙሉውን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡

አቶ ማሙሸት የቀረበባቸው የሽብረተኝነት ክስ ግልጽ አለመሆኑን በማስታወስ፣ በክሱ ላይ የወንጀል ድርጊቶቹ የት፣ መቼና በምን ሁኔታ እንደተፈጸሙ የማይገልጹ መሆናቸውን ጠቅሰው ያቀረቡት መቃወሚያ፣ አቃቤ ህግ የሽብር ወንጀል በተወሰነ ጊዜና ቦታ የሚፈጸም ባለመሆኑ እያንዳንዱን ጊዜና ቦታ መጥቀስ እንደማይችል፣ በተቻለ መጠን ግን በክሱ ላይ ለመጥቀስ እንደሞከረ በመግለጽ የሰጠውን ምላሽ በመቀበል ፍ/ቤቱ መቃወሚያውን አልተቀበለውም፡፡

አቃቤ ህግ በማስረጃነት ከክሱ ጋር ያያዘውን የአቃቤ ህግ ማስረጃ በሚመለከት፣ ተከሳሹ በሰነድ ማስረጃነት የቀረበባቸው የደህንነት ሪፖርት የሰነድ ማስረጃ ሳይሆን አንድ ግለሰብ ‹አውቃቸዋለሁ› ያላቸውን የተለያዩ መረጃዎች ያሰፈረበት የራሱ የደህንነት መስሪያ ቤት ሰራተኛ ቃል ወይም ሪፖርት በመሆኑ ተቀባይነት የለውም በማለት ውድቅ እንዲደረግላቸው የጠየቁበት መቃወሚያም እንዲሁ ውድቅ ተደርጓል፡፡

ፍ/ቤቱ በተከሳሽ በኩል የቀረቡትን መቃወሚያዎች ውድቅ በማድረግ ብይኑን ማሰማቱን ተከትሎ የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ የተጠየቁት አቶ ማሙሸት አማረ፣ ‹‹በክሱ ላይ የቀረበብኝን የወንጀል ድርጊት አልፈጸምሁም፣ ጥፋተኛም አይደለሁም›› ሲሉ ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡

አቃቤ ህግ በበኩሉ ተከሳሹ ክደው የተከራከሩ በመሆኑ በማስረጃነት ያቀረባቸው የሰነድ ማስረጃዎች ተመርምረው ብይን እንዲሰጥለት ችሎቱን ጠይቋል፡፡ ችሎቱም ማስረጃዎችን መርምሮ ብይን ለማሰማት ለህዳር 05/2010 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

አቶ ማሙሸት አማረ ከመጋቢት 20/2009 ዓ.ም ጀምሮ በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡ አቶ ማሙሸት አማረ የቀረበባቸው ክስ አርበኞች ግንቦት ሰባት በተባለ በሽብርተኝነት በተፈረጀ ድርጅት ‹‹ተመልምለው›› ተሳትፎ በማድረግ የጸረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 4 ስር የተመለከተውን በመተላለፍ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም ማቀድ፣ መዘጋጀት፣ ማሴር እና መነሳሳት ሙከራ ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ እንደቀረበባቸው ይታወቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *