እነ ከድር መሃመድ በድጋሜ ለፍርድ ቀጠሮ ተሰጣቸው

December 15/2016
*ተከሳሾቹ የሰብዓዊ መብት ጥሰት አቤቱታ ለፍ/ቤቱ አሰምተዋል

በእነ ከድር መሃመድ የክስ መዝገብ የሽብር ክስ ተመስርቶባቸው ጉዳያቸው በፍ/ቤት እየታየ የሚገኙት የራዲዮ ቢላል ጋዜጠኞችን ጨምሮ 19 ተከሳሾች ላይ ፍርድ እንደሚሰጥ ቀጠሮ ተይዞ የነበር ቢሆንም ፍ/ቤቱ ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው በመግለጽ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ በዕለቱ ተከሳሾች በማረሚያ ቤት እየደረሰብን ነው ያሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት አቤቱታ ለችሎት በቃል አሰምተዋል፡፡

ታህሳስ 4/2009 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 19ኛ ወንጀል ችሎት የቀረቡት ተከሳሾች በፍ/ቤቱ በተሰጠው ተለዋጭ ቀጠሮ ቅሬታቸውን በመግለጽ፣ በተደጋጋሚ በሚሰጡ ቀጠሮዎች ምክንያት አፋጣኝ ውሳኔ ባለማግኘታቸው ለእንግልት መዳረጋቸውን አስረድተዋል፡፡
ተከሳሾቹ በእስር በሚገኙበት እስር ቤት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው እንደሚገኝ ለችሎቱ በማስረዳት ፍ/ቤቱ የሚደርስባቸው ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ እንዲያበቃ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል፡፡

በክስ መዝገቡ 13ኛ ተከሳሽ የሆነው የራዲዮ ቢላል ጋዜጠኛ ዳርሰማ ሶሪ ለእስር ከተዳረገበት ጊዜ ጀምሮ በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራና አሁንም በቂሊንጦ እስር ቤት ድብደባና ሌሎች ኢ-ሰብዓዊ ድርጊቶች የተፈጸሙበትና እየተፈጸሙበትም እንደሚገኝ ለችሎት አስረድቷል፡፡ ጋዜጠኛ ዳርሰማ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ መሰል አቤቱታቸውን በጽሁፍ ለፍ/ቤት አቅርበው ይህ ነው የሚባል መፍትሄ እንዳልተሰጣቸው በማስታወስ፣ በዚሁ የተነሳ ከፍተኛ የሆነ የስነ-ልቦና ጉዳት እየደረሰባቸው እንደሚገኝ ገልጹዋል፡፡ ተከሳሹ ንብረቶቻቸው በእስር ቤት እንደተወሰዱባቸው በመግለጽም ፍ/ቤቱ ንብረቶቻቸው እንዲመለሱላቸው ትዕዛዝ እንደሚሰጥላቸው ጠይቋል፡፡

በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የመጸዳጃ ቤት ችግር መኖሩን፣ እንዲሁም ለጎናቸው ማረፊያ የተሰጣቸው አንድ በመጠኑ አነስተኛ በሆነ ፍራሽ ላይም ለሁለት ለመጋራት መገደዳቸውን አስረድቷል፡፡ ተከሳሹ እሱን ጨምሮ ሌሎች አብረውት የተከሰሱት ከተከሰሱበት ክስ ሌላ ከአርበኞች ግንቦት 7፣ ኦነግ እና አልሻባብ ከተባሉ በኢትዮጵያ መንግስት በሽብር ከተፈረጁ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት አላችሁ በሚል ኢ-ሰብዓዊ የሆነ ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ ለፍርድ ቤቱ ገልጹዋል፡፡
በመዝገቡ 5ኛ ተከሳሽ ኢብራሂም ካሚል በበኩሉ ቂሊንጦ እስር ቤት ላይ የደረሰውን ቃጠሎ ተከትሎ ወደሸዋሮቢት እስር ቤት ከተዛወረ ጀምሮ ሸዋሮቢት እስር ቤት በተገኙ መርማሪዎች ሽብርተኛ ከሚሏቸው አካላት ጋር ተባብረህ ትሰራለህ፣ በቂሊንጦ ለደረሰው ቃጠሎም እጅህ አለበት በሚል ኢ-ሰብዓዊ የማሰቃየት ድርጊቶች እንደተፈጸሙበት ለፍ/ቤቱ ተናግሯል፡፡ ተከሳሹ በሚከተለው ኃይማኖት ምክንያት በደል እንደተፈጸመበትም ለችሎት አስረድቷል፡፡ በዚህም አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት እንደደረሰበት ገልጹዋል፡፡

የተከሳሾች ጠበቃ አቶ ሰይድ አብደላ በበኩላቸው ጥቅምት 9/2009 ዓ.ም እና ከዚያም በፊት በነበሩ ችሎቶች የደንበኞቻቸውን ኢ-ሰብዓዊ አያያዝ የሚመለከቱ አቤቱታዎችን በፅሁፍ ጠቅሰው ለፍ/ቤት ቢያሳውቁም ተፈፃሚነት ሳያገኙ በመቅረታቸው በደንበኞቻቸው ላይ እየደረሰ ያለው እንግልት መባባሱን አስረድተዋል፡፡ በእነ ከድር መሀመድ የክስ መዝገብ የተካተቱት ተከሳሾች ቀደም ባሉት ቀጠሮዎች ፍ/ቤት በቀጠሮዎቻቸው መሰረት ማ/ቤት ሳያቀርባቸው መቅረቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ማ/ቤት ለዚህ ይሰጠው የነበረው ምክንያት ‹ተከሳሾች በተለያዩ ማ/ቤቶች ስለተበተኑ ማቅረብ አልቻልንም› የሚል እንደነበር ይታወሳል፡፡
ፍ/ቤቱ በተከሳሾች የቀረቡለትን አቤቱታዎች ካዳመጠ በኋላ ተገቢውን ትዕዛዝ እንደሚሰጥ በመግለጽ፣ መዝገቡን መርምሮ ፍርድ ለማሰማት ለታህሳስ 12 ቀን 2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *