Photo Credit - Addis Standard

እነ ጃዋር መሐመድ ጉዳያቸው ከምርጫው በኋላ እንዲታይ ጠይቀው ተከለከሉ

  • በቀለ ገርባ፤ “ሰው በአደባባይ በሚረሸንበት አገር… የኛ እዚህ [ፍርድ ቤት] መቅረብ ዕድለኛነት ነው”
  • ጃዋር መሐመድ፤ “እናንተ [ችሎቱ] ብትፈቱንም እነሱ [መንግሥት] መልሰው ያስሩናል”
  • ደጀኔ ጣፋ፤ “ለፖለቲካ ብለን አገር አናፍርስ ብለዋል”

ግንቦት 12፣ 2016 – የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት የጠቅላይ ፍርድ ቤት የምስክር ሒደትን በሚመለከት የሰጠው ውሳኔ በዕለቱ ስላልደረሳቸው ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ።

ተከሳሽ ሸምሰዲንን ጨምሮ አብዛኛው ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ ከዚህ ቀደም በነበረው ችሎት ከቤተሰቦቻቸው ጋር በስልክ መገናኘት እንዲችሉ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም እንኳን ማረሚያ ቤቱ ግን ትዕዛዙን ተፈፃሚ አላረግልንም በማለት አቤቱታ አሰምተዋል።  ፍርድ ቤቱም የማረሚያ ቤት አስፈፃሚ በችሎት ቀርበው ትዕዛዝ ያለመፈፀማቸው ተጠይቀው ስለነበር፤ አሁን የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ እንዲያስፈፅሙ እና ማስፈፀማቸውን ደሞ በጽሑፍ እንዲያቀርቡ ነገር ግን ይህን ማቅረብ ካልቻሉ ፍርድ ቤቱ የራሱን እርምጃ እንደሚወስድ አሳስበዋል።

በመዝገቡ አራተኛ ተከሳሽ ጉቱ ሙሊሳ በሆስፒታል ቀጠሯቸው መሠረት ማረሚያ ቤቱ አጃቢ የለኝም በማለት ሊያስወጣቸው እንዳልቻለ እና አሁንም ሕመም ላይ መሆናቸውን በማስረዳት ችሎቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸው ጠይቀዋል።

በመዝገቡ ሁለተኛ ተከሳሽ በቀለ ገርባ  “ሰው በአደባባይ በሚረሸንበት፣ በፍርድ ቤት ይፈቱ ተብሎ ደብዛቸው በሚጠፋበት፣ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሰጥቶ በማይከበርበት፣ ለአንድ ዓመት በማረሚያ ታስሮ ፍርድ ቤት በማይቀርብበት አገር የኛ እዚህ መቅረብ ዕድለኛነት ነው” ነገር ግን መቅረባችን ለውጥ ስለሌለው ቀጣይ ቀጠሮ ምርጫ ካለፈ በኋላ ይሰጠን ብለዋል፤ የተቀሩት ተከሳሾች በሙሉ ሐሳባቸውን በጭብጨባ ተቀብለዋቸዋል።

ጃዋር በማከልም “እናንተ [ችሎቱ] ብትፈቱንም እነሱ [መንግሥት] መልሰው ያስሩናል” በማለት ጉዳዩ ኮለኔል ገመቹ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በነፃ አሰናብቷቸው ደብዛቸው እንደጠፉት ማለታቸው እንደሆነ አብራርተዋል “የኛ የፍትሕ ጉዳይ አይደለም። መንግሥት እኛን አስሮ ማቆየት ብቻ ነው የሚፈልገው። እኛ በቀረብን ቁጥር የእናንተን ሰዓት ማባከን የአገርንም ሀብት ማባከን ስለሆነ፥ እኛ እናንተን እናከብራለን” በማለት መንግሥት “ምርጫውን ጨርሶ መሆን የሚፈልገውን በሙሉ ሆኖ” ሲያጠናቅቅ ቀጠሮውን ለ2015 ወይንም 2016 አድርጉልን፤ ምናልባት የዛኔ ለውጥ የሚመጣ ከሆነ በማለት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩላቸው ለችሎቱ መቅረብ የሌለበት ጉዳይ መቅረብ እና መስተናገድ የለበትም፤ የቀጠሮ ቀንን በሚመለከት በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ስርዓት ሕጉ መሠረት ነው መሆን ያለበት ብለዋል።

በመጨረሻም ደጀኔ ጣፋ “ፍርድ ቤት እና ዐቃቤ ሕግ ስለዲሞክራሲ ካልተመለከተው ማነው ታዲያ የሚመለከተው? በሌላው ዓለም ፍርድ ቤቶች ምርጫው ልክ አደለም ብለው እስከማስቆም ይሔዳሉ፤ ይህቺ አገር ወደ ጥፋት እየሔደች ነው። እናድናት። ለፖለቲካ ብለን አገር አናፍርስ” ብለዋል። በማከልም ሕግ በመማሬ አፍረየያለው ሲሉ ተደምጠዋል።

ችሎቱ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ለማስፈፀም የሚደረጉ ጥረቶች ይቀጥላሉ፤ በናንተም ጉዳይ እንደምናስፈፅም ቃል እንገባለን በማለት ቀጣይ ቀጠሮ ለግንቦት 28 ሰጥተዋል።

Center for Advancement of Rights and Democracy (CARD)

Making Democracy the Only Rule of Game!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *