ከልካይ የሌለው የፀበልተኞቹ ፍዳ

ጸሐፊ፡- ማሕሌት ፋንታሁን

አንድ ጓደኛዬ ታሞ ሽንቁሩ ሚካኤል ሆኖ ፀበል  እየተጠመቀ መሆኑን ሰምቼ ልጠይቀው ወደ ፀበሉ ቦታ አመራሁ። ተረፈ ይባላል። ተረፈን በቅርበት የማቀው ጓደኛዬ በመሆኑ እና ሳውቀውም ፍፁም ጤነኛ ሆኖ ስለነበረ እስካገኘው ተጨንቄ ነበር። ለቦታው አዲስ በመሆኔም ከመንገድ ወጥቶ እንዲቀበለኝ አደረግኩ። “የመጠጥ ሱስህ እንዲተውህ ተብዬ ነው ቤተሰቦቼ ወደዚህ ያመጡኝ” በማለት ወደ ፀበል የመጣበትን ምክንያት ነገረኝ። ተከራይቶ ወደ ሚኖርበት ቦታ ስንሔድ በመንገዳችን፣ እጅ እና እግራቸውን (እግር ከወርች) ወይም እግራቸውን ብቻ የታሰሩ ሰዎችን አልፈን ነው ቤቱ የደረስነው። ባየሁት ነገር ተደናግጬ ለምን እንደታሰሩ ስጠይቀው፣ “ፀበልተኞች ናቸው። አብዛኛዎቹ ወደ ቤታቸው ወይም ሌላ ቦታ እንዳይሔዱ ነው የሚታሰሩት። ተመልሰው ከሔዱ ደግሞ አስጠማቂዎቻቸው ብር አያገኙም። ለፀበልተኞች የሚደረገው ቁጥጥር በሚከፈልላቸው ብር መጠን እና ጠያቂ መኖር እና አለመኖር ይለያያል። ብዙ ብር የሚከፈልላቸው እና  ጠያቂ በየጊዜው የሚመጣላቸው ፀበልተኞች ጥሩ ጥበቃ እና ክትትል ይደረግላቸዋል። አስጠማቂዎች ከአንድ ፀበልተኛ በወር በአማካኝ ከ3000 እስከ 3500 ይቀበላሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ እራሳቸውንም ሌላውንም ይጎዳሉ በሚል ነው የሚታሰሩት። እኔም የመጣሁ ጊዜ 3000 ብር ነበር የሚከፈልልኝ። እንዳየሻቸው ፀበልተኞች ታስሬ ነበር የምውለው። አሁን ስረጋጋ ጊዜ እና ነገሮችን ስረዳ በራሴ እጠመቃለው ብዬ በግሌ ቤት ተከራይቼ መኖር ጀመርኩ።” ሲል አስረዳኝ ተረፈ። ተረፈን ለመጠየቅ ‹ሽንቁሩ ሚካኤል› በመባል የሚታወቀው የፀበል ቦታ በተመላላስኩባቸው ጊዜያት ያየሁትን እና የሰማሁትን መግለጽ በቻልኩት መጠን በዚህ ጽሑፍ ለመዳሰስ እሞክራለው።

 

ፀበልተኞች

በሽንቁሩ ሁለት ዓይነት ፀበልተኞች (ፀበል ተጠማቂዎች) አሉ። የመጀመሪያዎቹ በፈቃዳቸው ፀበል ለመጠመቅ የሚመጡ ሲሆኑ፣ ሁለተኞቹ ደግሞ ያለፈቃዳቸው በቤተሰብ ወይም የቅርብ ሰው አስገዳጅነት ወደ ፀበሉ ቦታ የሚመጡ ናቸው። ይህ ጽሑፍ የሚያወራው በሁለተኛው ምድብ ስለተካተቱት ብቻ ይሆናል።

ፀበልተኞቹ በአብዛኛው በተለያየ ሱስ የተያዙ ወይም ቤተሰብ ሱስ ይዟቸዋል ብሎ ያመነባቸው፣ የአእምሮ እድገት ውሱንነት ያለባቸው፣ የሚጥል በሽታ ያለባቸው፣ እና  የጭንቀት ወይም ከአእምሮ መታወክ ጋር የተያያዘ ችግር ያለባቸው ናቸው። ጤነኞችም ሆነው በተንኮል እና በሴራ ቤተሰብ የተለያየ ጥቅም ለማግኘት ሲል ወደ ፀበል እንዲመጡ የሚደረጉ እንዳሉም ተረድቻለሁ፡፡ ቤተሰብ የተለያዩ ማታለያ ዘዴዎችን ተጠቅሞ ወይም በኃይል አስገድዶ ወደ ሽንቁሩ እንዲመጡ ያደርጋቸዋል።

ተረፈ እንዴት ወደ ሽንቁሩ እንደመጣ ሲነግረኝ “ለሊት 10:30 ሰዐት ይሆናል። አንድ ጓደኛዬ ሌላ ጓደኛችን ታማለች ሐኪም ቤት እንውሰዳት ብሎ ከእንቅልፌ ቀሰቀሰኝ። ስጠጣ አምሽቼ ለሊት ላይ ስለነበር ወደ ቤት የገባሁት ሞቅታው ሙሉ ለሙሉ አልለቀቀኝም ነበር። እንደምንም ተነስቼ ከቤቴ ወጣሁ እና ጓደኛዬን ተከትዬ መሔድ ጀመርኩ። ከሰፈራችን ወጣ ብሎ ያለ አስፋልት ላይ ደረስን። አስፓልቱ ላይ ቆማ የነበረች መኪና ውስጥ እንድገባ ጓደኛዬ ነገረኝ። የታመመችው ጓደኛችን እንዳለች ገምቼ ገባሁ። አልነበረችም። መኪና ውስጥ ያለ የማላቀው ወንድ ‘ፖሊስ ነኝ’ ብሎ እግሬ እና እጄን በጉልበት ይዞ በሰንሰለት አሰረኝ። መኪናዋ ውስጥ እህቴን አየኋት። ደንግጬ የምለው ጠፋኝ። ‘ጓደኛዬ እና እህቴ ከፖሊስ ጋር ተባብረው እንዴት ያሳስሩኛል?’፣ ‘ለምን ያሳስሩኛል?’ አእምሮዬ በጥያቄዎች ተሞላ። እህቴ በተደጋጋሚ  ‘እንድትድን እኮ ነው’ ትለኛለች። ‘ምን ሆኛለው? ደሞስ መዳን እና በፖሊስ መታሰር ምን ያገናኘዋል?’ እያልኩ አውጠነጥናለሁ። እጄም እግሬም በመታሰሩ እና አቅም በማጣቴ ተበሳጭቻለው። መኪናዋ አስፓልት የሆነ መንገድ ጨርሳ ረጅም የኮሮኮንች መንገድ ተጉዛ የሆነ ቦታ ስትደርስ አቆመች። ያሰረኝ ‹ፖሊስ ነኝ› ያለኝ ሰው አንስቶ የሆነ ቤት በር ላይ አስቀመጠኝ። እህቴ አብራኝ አልመጣችም፤ ከመኪናዋ ጋር የተመለሰች መሰለኝ። እጄ እና እግሬ እንደታሰረ ነው። የሚጠጣ ውኃ ፈለኩና ‹ፖሊሱን› ጠየቅኩት። የደፈረሰ ውኃ እንድጠጣው ሰጠኝ። ‘ይሄን ውኃ ነው የምጠጣው?’ ስለው ‘ውኃ አይደለም ፀበል ነው’ አለኝ። ያኔ ነው ፀበል ቦታ መሆኔ የገባኝ።”  በማለት ወደ ሽንቁሩ የመጣበትን አጋጣሚ ይናገራል።

በሽንቁሩ በርካታ ፀበልተኞች ሌት ተቀን እግር ከወርች ታስረው ነው የሚቆዩት

ተረፈ ማስረዳቱን ሲቀጥልም “ትንሽ ከተረጋጋሁ፣ ስካሬም ከበረደልኝ በኋላ ፖሊስ የመሰለኝ ሰውዬ እኔን ሊያስጠምቅ እና ሊቆጣጠር የተመደበ ሰው መሆኑን ተረዳሁ። ማውራት ጀመርን እና በመሐሉ ግራ የሚገባ ጥያቄ ጠየቀኝ። ‘በቤተሰባችሁ መሐል የውርስ ጉዳይ አለ እንዴ?’ ሲል ጠየቀኝ። እንደ ሌለ ነገርኩት። የጥያቄው አግባብነት የተገለፀልኝ ከሰነባበትኩ በኋላ ነው። ቤተሰብ የውርስ ጉዳይ ወይም የሐብት መካፈል ጥያቄ እንዳያነሳ የሚፈልጉትን ሰው ጉዳዩ እስኪፈፀም ለጊዜው ዞር እንዲልላቸው በማለት ሰበብ ፈልገው እጅ እና እግራቸውን አሳስረው ፀበል ቦታ እየከፈሉ ያስቀምጧቸዋል። እንደዚህ ዓይነት ፀበልተኞች ብዙ ይመጣሉ። ለምን ፀበል ቦታ እንደመጡም ያውቁታል። ግን አቅም ስለሌላቸው ምንም ማድረግ አይችሉም። እንዳይመለሱ እጅ እና እግራቸው ይታሰራል። በዛ ላይ ርቀው እንዳይሔዱ ይጠበቃሉ። አስቢው ሱስም ሳይኖርባቸው ጤነኛ እንደሆኑ እያወቁት በተንኮል ታስረው ፀበል እንዲጠመቁ ሲገደዱ?” በማለት ጥያቄ አዘል አስተያየት አቀረበልኝ፡፡

ሌሎቹም ፀበልተኞች በተመሳሳይ ሁኔታ ቤተሰብ የተለያየ ቴክኒክ እየተጠቀመ እንደሚያስመጣቸው ተረፈ እንዲህ ሲል አጫውቶኛል። “ያ ፀበልተኛ እንዴት እንደመጣ ታውቂያለሽ?” አለኝ ወደ አንዱ እየጠቆመኝ፡፡ “አልኮል ሱስ አለበት። አልኮል ሲጠጣ ነው የሚውለው አሉ። ግን ስለሚበላ ሰውነቱ አልተጎዳም። እንደምታይው ጠጪም አይመስልም። እና አንድ ቀን ቤተሰቦቹ መሬት ልንገዛልህ ነው ብለው ከደላላ ጋር ያገናኙታል። ደላላው መሬቱን ላሳይክ ብሎ በመኪናው ካስገባ በኋላ እጅ እና እግሩን አስሮ ሽንቁሩ አመጣው። ለኔ ጊዜ እንደ ፖሊስ ሆኖ የመጣው አስጠማቂ፣ ለሱ ጊዜ ደግሞ ደላላ ሆኖ ነው ያገኘው። እሱ አራት ሺሕ ብር ነው በወር የሚከፈልለት። ‘ባላ አራት ሺው’ ነው የሚባለው። የሱ ጥበቃም ጠንከር ያለ ነው” በማለት ከፊት ለፊቴ እግሩ ታስሮ የሚታየኝን ፀበልተኛ አመጣጥ ነግሮኛል።

 

አስጠማቂዎች

‹አስጠማቂዎች› የሚባሉት ፀበልተኞችን ካሉበት ቦታ ተቀብለው በተከራዩት ቤት የሚያኖሩ፣ ምግብ የሚያቀርቡ፣ ወደ ፀበል ቦታ እየወሰዱ የሚያስጠምቁ፣ የሚያስሩ፣ በአጠቃላይ ከቤተሰብ ስለተረከቡት ፀበልተኛ የሚመለከታቸው ግለሰቦች ናቸው። በሽንቁሩ ከመቶ በላይ አስጠማቂዎች ሲኖሩ እያንዳንዳቸው በአማካኝ ከዐሥር እስከ ዐሥራአምስት ተጠማቂዎች ይኖሯቸዋል። ከአንድ ተጠማቂ ከቤተሰብ በወር የሚቀበሉት ገንዘብ በአማካኝ ከ3 ሺሕ እስከ 3,500 ብር ይሆናል። ከቤተሰብ የሚቀበሉት ብር እጅ እና እግር የሚታሰርበትን ሰንሰለት ወጪ ጨምሮ፣ የምግብ፣ የቤት ኪራይ እና ለማስጠመቂያ የሚውል ነው። የፀበልተኞቹ ጠያቂዎች ፀበልተኛው/ዋን ለመጠየቅ ሲሔዱ የሚወስዱት ምግብም ሆነ ማንኛውም ነገር በአስጠማቂዎች በኩል ነው የሚያልፈው። አስጠማቂዎች ለፀበልተኞቹ የመጣውን ነገር እየቀነሱ ነው በየቀኑ የሚሰጧቸው፡፡ አስጠማቂዎቹ ለፀበልተኞቹ የመጣውን ነገር ሳይሰጧቸው ለራሳቸው የሚጠቀሙበት አጋጣሚ እንዳለም ሰምቻለሁ፡፡ ፀበልተኞቹ ከሚኖሩበት ግቢ እንዲወጡ አይፈቀድላቸውም፣ ከወጡም መጠጥ እና ሲጋራ እንዲጠጡ አይፈቀድላቸውም። ሲጠጡ የተገኙ ፀበልተኞች በእንጨት ይደበደባሉ። ሊያመልጡ ሲሉ የተያዙ ፀበልተኞችም እንዲሁ።

አልፎ አልፎ ደግሞ አንዳንድ አስጠማቂዎች መጠጥ ሲጠጡ አምሽተው ለሊት ላይ ሲመለሱ ሴት ፀበልተኞችን አስገድደው የሚደፍሩበት አጋጣሚም አለ ተብያለሁ። የሚደበደቡትም ሆነ የሚደፈሩት ፀበልተኞች በሚጮሁበት ጊዜ አንድም ‘ሰይጣን ነው የሚያስጮሃቸው’ በሚል አንድም ደግሞ ድብደባ እንዳይደርስባቸው ስለሚሰጉ ሌሎች ፀበልተኞች ለመገላገል ወይም ለማስጣል አይጥሩም።

አስጠማቂዎች በሽንቁሩ የሁሉ ነገር አድራጊ ፈጣሪ ናቸው። የገቢ ምንጫቸው ፀበልተኞች ስለሆኑ ፀበልተኞቹ እንዳይጠፉባቸው እግራቸውን ከማሰር ጀምሮ ሌላ የሚከታተላቸው ሰው(ረዳት) በመመደብ ቁጥጥር ያደርጋሉ። ከቤተሰብ የሚቀበሉት ብር ብዛት ተገቢ አለመሆኑን እና በሁሉም ነገር ላይ ዋጋ ጭማሪ እንደሚያደርጉባቸው ተረፈ እንዲህ ሲል አጫውቶኛል። “እኔ ስመጣ የቤት ኪራይ በወር ሦስት መቶ ብር፣ የምግብ 1,200 ብር እና የማስጠመቂያ 1,500 ብር ባጠቃላይ 3,000 ብር ለወር ነው የተቀበለው ከቤተሰቦቼ። ከዛ በሦስተኛ ወሬ የቤቱ ባለቤት መጣና አስጠማቂዬን አጥቶት ነው መሰለኝ የቤት ኪራይ ብር እንድሰጠው ጠየቀኝ። ሦስት መቶ ብር ስሰጠው ‘የስንት ወር ነው?’ አለኝ። ከዛ ሦስት መቶ ብር ከዋጋው በላይ መሆኑ ገባኝና ‘የሁለት ወር’ አልኩት። ሰማኒያ ብር መለሰልኝ። ለካ 120 ብር እየተከራየ ነው ለኔ ሦስት መቶ ብር ይቀበለኝ የነበረው። በዛ ላይ ሌሎች ፀበልተኞችም ቤቱን እንዲጋሩት ይደረጋል። በቤቱ የሚኖረው ፀበልተኛ ሁሉም የኪራይ ይከፍላሉ።”

 

መስታወት ከስሟ እና ከአገሯ ውጪ የምታውቀው ነገር የለም፡፡ ለአስጠማቂዎች አስረክበዋት የሔዱት ሰዎች ደግመው መጥተው አላይዋትም፡፡

አልቦ-ዘመዷ መስታወት

መስታወት በግምት ከ17 እስከ 20 ዓመት ዕድሜ ይሆናታል። ከሁለት ወር በፊት ነው ወደ ሽንቁሩ የመጣችው። በሁለት ኩርቱ ፌስታል ልብሷን እንደያዘች “መንገድ ላይ አገኘናት ተባበረን” ብለው ለአንዱ አስጠማቂ የአንድ ወር ከፍለው መስታወትን ይሰጡታል። በየወሩም እየመጡ እንደሚያዩአት እና እንደሚከፍሉት የነገሩት በመንገድ ላይ አገኘናት ያሉት ሰዎች ሳይመለሱ የውኃ ሽታ ሆነው ቀሩ። ባስመዘገቡት አድራሻም መገኘት አልቻሉም። መስታወት ከሥሟ እና አገሯ ጎንደር ከመሆኑ ውጪ የምትናገረው ነገር የለም። የተከፈለላት አንድ ወር እንዳለቀ አስጠማቂዋ አንድ ጠዋት ፌስታሏን አስይዞ እንጦጦ ማርያም ጥሏት ይመለሳል። መስታወት የዛኑ ቀን ወደ ከሰዐት በኋላ አካባቢ ፌስታሏን ይዛ ወደሽንቁሩ ትመለሳለች። ይህን ያዩ ፀበልተኞች አዋጥተው ቤት ተከራይተው አስቀመጧት። ሌላ አስጠማቂም በነፃ እንደሚያስጠምቃት ቃል ገባ። ይህ የፀበልተኞቹ እና የአስጠማቂ ዕርዳታ ግን እስከመቼ እንደሚቀጥል አይታወቅም። የመስታወት የወደፊት ዕጣ ፈንታ ምን ይሆን? ቤተሰቦቿ ያገኟት ይሆን? ወይስ የሚሊዮን ዕጣ ይደርሳት ይሆን? የሚሊዮንን ታሪክ ደግሞ ቀጥለን እንመለከታለን፡፡

 

ሚሊዮን ማነው?

በሽንቁሩ የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ያለባቸው በርካታ ‹ፀበልተኞች› ያለ ጠያቂ እየተንገላቱ ይገኛሉ፡፡

ሚሊዮን ቤተሰቦቹ ማን እንደሆኑ፣ ማን ወደ ሽንቁሩ እንዳመጣው እና ከየት አካባቢ እንደመጣ የሚታወቅ ነገር የለም። እነዚህ መረጃዎች የጠፉት በርካታ ዓመታትን በሽንቁሩ ያለጠያቂ በማሳለፉ ነው። ሽንቁሩ ከመጣ ከስምንት ዓመት በላይ ይሆነዋል። የአእምሮ ዕድገት ውሱንነት ያለበት ወጣት ሲሆን፣ ዕድሜው በግምት 20ዎቹ ውስጥ ይመስላል። ሚሊዮንን ያመጡት ሰዎች ቢጠፉም እንደ መስታወት አልተጣለም። ከባባድ ሥራዎችን ለአስጠማቂዎች እየሠራ ከሌሎች ፀበልተኞች ጋር መኝታ እየተጋራ አሁን ድረስ አለ። ውኃ በጀሪካን ከሩቅ ቦታ እየቀዳ እያመጣ፣ እንጨት እየፈለጠ እና በመላላክ ጉልበቱን በመገበር ይኖራል። አልታዘዝም ወይም ደክሞኛል ማለት አይችልም። የታዘዘውን ነገር በፍጥነት ወይም በተባለው አኳኋን ካልፈፀመ በእንጨት ጭካኔ በተሞላው መልኩ ይደበደባል። ከድብደባው ሳያገግምም ሥራውን እንዲሠራ ይገደዳል። ሚሊዮን ሌሎች ፀበልተኞች ቤተሰቦቻቸው ሲመጡ እና ከፀበል ሲወጡ እሱም ቤተሰቦቹ መጥተው እንዲያዩት እና እንዲወስዱት ሲመኝ እስከመቼ ይቆይ ይሆን?

 

‹ላርጋቲን›

በሽንቁሩ ያሉ ፀበልተኞች ለሊት የማይተኙ ወይም እየጮሁ የሚያስቸግሩ ካሉ የሚሰጣቸው መድኃኒት እንዳለ ሰምቻለው። መድኃኒቱን በዓይኔ ባላየውም ፀበልተኞቹ ‹ላርጋቲን› እንደሆነ ነግረውኛል። ሁሉም አስጠማቂዎች እጅ እንደሚገኝ እና “አስቸጋሪ” ለሆነ ፀበልተኛ እንደሚሰጥም ጭምር ተነግሮኛል።

 

የመሠረታዊ ፍላጎቶች መጓደል

በሽንቁሩ መፀዳጃ ቤት የማይታሰብ ነገር ነው። ሁሉም ፀበልተኛ የሚቀመጠው ወደ ጫካ ወይም ወደ ሜዳ በመውጣት ነው። የቧንቧ ውኃም ለማግኘት በጣም ነው የሚቸገሩት። በአካባቢው አንድ የቦኖ ውኃ ቢኖርም ወረፋ ስለሚበዛበት ረጅም ርቀት ተጉዘው ከጉድጓድ ውኃ ቀድተው ነው የሚጠቀሙት።

 

ገንዘብ ካለ…

“ቤተሰብ የአእምሮ በሽተኛ ወይም ሰካራም ልጅ ካለው ጎረቤት ወይም ዘመድ ቢያያቸው ስለሚያሳፍራቸው፣ ገንዘብ ከፍለው ፀበል ቦታ ያስቀምጣቸዋል። ቤተሰቦች ከዓይናቸው መራቃቸውን እንጂ እዚህ ስለሚደርስባቸው በደል አያውቁም፡፡ ፀበልተኞቹ የሚደርስባቸውን ለቤተሰብ ከተናገሩ ደግሞ ቅጣቱ ይብስባቸዋል እንጂ አይቀንስላቸውም። በዛ ላይ ቤተሰብ ከልጁ ይልቅ አስጠማቂውን ነው የሚያምነው። ልጁ ከፀበል ቦታው ለመውጣት የሚዋሻቸው ነው የሚመስላቸው። በውርስ ጉዳይ ችግር ያለባቸውም ሀብቱን እንዳይካፈል እዚህ አሳስረው ያመጡታል። ብቻ ገንዘብ ያለው ሰው ብዙ ነገር ማድረግ ይችላል – እዚህ ሽንቁሩ። ማስገደልም ይቻላል። በኋላ ላይ ፀበል ሲጠመቅ ሞተ/ች ይባላል” ይላል ሔኖክ ገንዘብ በሽንቁሩ ፀበል ቦታ ስላለው ኃይል ሲናገር።

በተጨማሪም የመጠጥ እና የሲጃራ ሱስ አለባቸው ተብለው የመጡ ፀበልተኞች ገንዘብ ያላቸው ከሆኑ መጠጥም ሆነ ሲጃራ የሚያገኙበት መላ አያጡም። አካባቢውን ከለመዱ በኋላ ራሳቸው በመሔድ ወይም ሔዶ በገንዘብ የሚያመጣላቸው ሰው ፈልገው ፉት የሚሉት አረቄ እና ተደብቀው የሚያጨሱት ሲጋራ አያጡም። አስጠማቂያቸው ካወቀ ወይም ከደረሰባቸው ግን በእንጨት ክፉኛ ይደበደባሉ። ከዛ በኋላ የማይታሰሩ ከነበረ በሰንሰለት እግራቸውን ይታሰራሉ።

ባጭሩ ሽንቁሩ መለስተኛ እስር ቤት ነው። ይህ በሹንቁሩ ፀበል ቦታ ብቻ ያለ ታሪክ አይደለም። ይህ የተረፈ፣ የመስታወት እና የሚሊዮን ብቻ ታሪክ አይደለም። በሽንቁሩም ሆነ በተለያየ ፀበል ቦታ የነሱን ታሪክ የሚጋሯቸው ፀበልተኞች በየቦታው አሉ። በፀበል ቦታዎች ስለሚደርሱ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችም ሲወራ ዓመታቶች ተቆጥረዋል። በተለይ ሱስ እና የአእምሮ ችግር ያለባቸው ወጣቶች እና ሕፃናት ቁጥር በየፀበል ቦታው ቁጥራቸው ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አለመሆኑ የሚታይ ነው።

ሃይማኖታዊ ተቋምን ከለላ በማድረግ ለሚሠሩ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች ማነው ተጠያቂው? ዘላቂ መፍትሔውስ ምንድን ነው? የሚሉት ጥያቄዎች የሚመለከተው አካል ተከታትሎ ምላሽ መስጠት ያለበት ዐቢይ ጉዳይ ሲሆን በእኔ ዕይታ ዋነኛው ችግር ብዬ የማስበው የግንዛቤ እጥረት፣ ከሱስ ማገገሚያ ማዕከላትና  የአእምሮ መታወክ ሕክምና መስጫ ተቋማት በሚፈለገው መጠን አለመኖር ነው። ጉዳዩ ትኩረት እና አስቸኳይ መፍትሔ ሊሰጠው ይገባል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.