ካርድ በግል መረጃ ጥበቃ ረቂቅ አዋጅ ላይ የማሻሻያ ጥቆማዎችን አቀረበ

የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) በኢትዮጵያ የግል መረጃ ጥበቃ ረቂቅ አዋጅ ያሉበትን ክፍሎችን በመለየት ሕጉ ፀድቆ ከመውጣቱ በፊት ትኩረት እንዲደረግባቸው የማሻሻያ ሐሳቦችን አቀረበ።

በመጀመሪያ በ2012 በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ በኋላ በ2013 የተሻሻለው ረቂቅ አዋጅ የግል መረጃን ጥቅም በመገንዘብ ጥበቃ ሊደረግለት እንደሚገባ ያወሳል፡፡ ይሁን እንጂ ረቂቅ ሕጉ ያለመውን የግል መረጃ ጥበቃ ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመጠበቅ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ክፍተቶችን ይገኙበታል።

ይህ የካርድ የማሻሻያ አቋም ሰነድ እነዚህ ጉድለቶች ቁልፍ መሆናቸውን በማስገንዘብ ከመግቢያው ጀምሮ የግል መረጃ ጥበቃ እና የመረጃ ደኅንነትን አስፈላጊነት በግልፅና በአፅንኦት እንዲቀመጥ የሚጠይቅ ሲሆን፣ ሥልጣንን እና ኃላፊነትን የሚዘረዝሩ ድንጋጌዎች እንዲሁም የመረጃ ጥበቃ ኮሚሽኑ ነፃነትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች ትኩረት እንዲሰጣቸው ያሳስባል።

የካርድ የግል መረጃ ጥበቃ ረቂቅ አዋጅ የማሻሻያ አቋም “ረቂቅ ሕጉ እና የሕጉን መጽደቅ ተከትሎ የሚቋቋመው ኮሚሽን፤ የኮሚሽኑ የበላይ አካል ሙሉ ነፃነት እንዲኖረው እና የዜጎችን የግል ዳታ ከመጠበቅ አንፃር ኮሚሽኑ አቅም ወይም ብቃት ሊኖረው እንደሚገባ ማረጋገጥ እንደሚኖርበት የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) ያምናል። ስለሆነም ለዚህ የሕግ ማዕቀፍ አርቃቂዎች እና የሕግ አውጪ አካላት ሊያተኩሩበት የሚገባው ምንጊዜም ቢሆን ዋናው ጉዳይ የግል ዳታ ጥበቃ ኮሚሽኑ ነፃነት የተሟላ መሆኑን ማረጋገጥ መሆን እንዳለበት ነው” ይላል፡፡

ስለዚህም በአዋጁ መሠረት የሚቋቋመው የግል መረጃ ጥበቃ ኮሚሽን የኮሚሽነሮቹ ምልመላ እና ሹመት በብቃት ላይ የተመሠረተ እና ሂደቱም ግልፅ እንዲሆን፣ የኮሚሽኑ የገንዘብ እና የበጀት ምንጮች ምንም ዓይነት የጥቅም ግጭት ካላቸው አካላት ሊሆኑ እንደማይገባ፣ የኮሚሽኑ ሥልጣን በምንም ዓይነት ሁኔታ በአገሪቱ የሕግ አስፈፃሚ አካል ጣልቃ ገብነት ሊጣስ እንደማይገባ እንዲሁም የኮሚሽኑ ሥልጣን እና ኃላፊነት ተገቢውን አስተዳደራዊ እርምጃዎች መወሰን በሚያስችል አግባብ በግልፅ መጠቀስ እንዳለበት ያስገነዝባል፡፡

ከኢንተር ኒውስ አድቮኬቲንግ ፎር ዳታ አካውንቴቢሊቲ፣ ፕሮቴክሽን ኤንድ ትራንስፓረንሲ (ADAPT) ፕሮጀክት ጋር በመተባበር በተዘጋጀው የግል መረጃ ጥበቃ የማሻሻያ አቋም ሰነድ የኮሚሽኑ ነፃነት መጠበቁ መረጋገጥ እንዳለበት ያሳስባል። የአቋም መግለጫው ከሌሎች አገሮች ተመሳሳይ ተፈጥሮ ካላቸው ሕጎች ትምህርት በመውሰድ ረቂቅ ሕጉ ከመጽደቁ በፊት በረቂቅ ሕጉ ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመፍታት የሚያስችሉ አማራጮችን ይመክራል።

የዚህን የግል መረጃ ጥበቃ ረቂቅ አዋጅ ማሻሻያ አቋም ሰነድ በማስመልከት የተናገሩት የካርድ ዋና ዳይሬክተር በፍቃዱ ኃይሉ “የግላዊነት (ፕራይቬሲ) መብት ከመሠረታዊ የሰብዓዊ መብቶች መካከል አንዱ ነው። የግል መረጃ መሰብሰብና ማዛባት፣ እንዲሁም ለትርፍ ወይም የፖለቲካ ዓላማ ማዋል በዚህ የቴክኖሎጂ ዘመን፣ በግል ነጻነቶች እና ግላዊ ምሥጢር አጠባበቅ ላይ የተጋረጠው ትልቁ አደጋ ነው። ካርድ የሰብዓዊ መብቶች ተኮር ድርጅት እንደመሆኑ በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ባሕልን እውን ለማድረግ የበኩሉን እየሠራ ሲሆን፣ ቴክኖሎጂ በዘመናዊ ማኅበረሰቦች የዜጎችን ሕይወት ለማቅለልና መብቶቻቸውን ከጥቃት ለመጠበቅ የሚደረገውን ጥረት ከቴክኖሎጂ ፈጠራ አስፈላጊነት ጋር ሚዛን እንዲጠብቅ፣ የመረጃ አሰባሰብ እና አቀነባበር ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር በትኩረት ይከታተላል። ስለሆነም አጠቃላይ የግል መረጃ ጥበቃ ሕግ በአስቸኳይ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ኮርፖሬሽኖች፣ መንግሥታት እና ሌሎችም አካላት ግዙፍ የግል መረጃዎችን በሚሰበስቡበት፣ በሚያስተላልፉበት እና በሚያቀናብሩበት ውስብስብ የዲጂታል ዘመን የመረጃ ጉዳዮችን መብት በሚያስቀድም መልኩ ሕጉ መቀረጽ አለበት” ብለዋል።

የአቋም ሰነዱን ለማውረድ እዚህ ይጫኑ አልያም ከታች ያንብቡ፡፡

በዳታ-ጥበቃ-ረቂቅ-አዋጁ-ላይ-የካርድ-የአቋም-ሰነድ

Center for Advancement of Rights and Democracy (CARD)

Making Democracy the Only Rule of Game!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

*

code