ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብቶች ቀንን በማስመልከት የተወሰኑት ፖለቲካ እስረኞች ሁኔታ

የሰብአዊ መብቶች ፕሮጄክት ዓለም አቀፉን የሰብዓዊ መብቶች ቀንን በማስመልከት በሺዎች ከሚቆጠሩ የፓለቲካ እስረኞች መካከል የጥቂቶቹን ታሪክ በማጋራት ስናስባቸው እንውላለን፡፡
HRD
1. ‹‹እኔ ስያዝ ያየ የ4 አመት ህጻን ለቀናት በፍርሃት ይቃዥ ነበር›› ዘላለም ወርቃገኘሁ

ዕለቱ ሀምሌ 1/2006 ዓ.ም ነበር፤ ሦስት ሰዓት አካባቢ ይሆናል፡፡ ገና ከእንቅልፌ መነሳቴ ነበር፡፡ እስከ ሰኔ 30/2006 ዓ.ም ድረስ የማስተርስ ዲግሪ መመረቂያ ጽሁፌን እየሰራሁ ስለነበር የተጠራቀመ ድካም ነበረብኝ፡፡ በዚህ ጠዋት አንድ የማውቀው ሰው ደውሎ ‹‹ፈልጌህ ነበር፣ አንዴ ወደ በር ወጣ በልልኝ›› አለኝ፡፡

ከዚያ በቅጡ እንኳ ሳልለባብስ ዓይኖቼን እያሻሸሁ ወደ በር ስወጣ አካባቢው ተከብቧል፡፡ ዞር ዞር ስል ፖሊስና ደህንነት ከቦኛል፡፡ ለሰከንዶች ያህል በድንጋጤ ተሞላሁ፤ በቃ ድርቅ ነበር ያልኩት፡፡ ወዲያው ግን ተመልሼ ተረጋጋሁ፡፡ የሆነ ስሜ ያለበት ወረቀት አጠፍ አድርገው አሳዩኝ፡፡ ከእኔ ስም በተጨማሪ ዳንኤል ሺበሺ የሚል ስም ማየቴ ትዝ ይለኛል፡፡ ሁኔታው ሁሉ ስለገባኝ ድንገት፣ ‹‹ታዲያ ውሰዱኛ!›› አልኳቸው፡፡ በቅጽበት የመጣልኝ ሀሳብ ከዚያ ቦታ ቶሎ ይዘውኝ መሄድ አለባቸው የሚለው ነበር፤ ምክንያቱም እናቴ ይሄን ካየች በድንጋጤ ትሞትብኛለች ብዬ ፈርቼ ነበር፡፡ ደግነቱ በሰዓቱ እናቴ ቤት አልነበረችም፤ ስለዚህ ቶሎ ይዘውኝ ከሄዱ በእንዲህ ያለ ሁኔታ በፖሊስ ተከብቤ ልታየኝ አትችልም፣ ያ ደግሞ ለእኔ ትልቅ እፎይታ ነበር፡፡

ሆኖም ከአካባቢው ቶሎ መሄድ የሚለው ሀሳቤ አልተሳካልኝም፤ ፖሊሶችና ደህንነቶች አካባቢውን ሁሉ ከዘጋጉ በኋላ ወደቤት ገቡ፡፡ ልክ ሲገቡ ፖሊሶቹ መሳሪያቸውን አነጣጥረው ነበር የሚራመዱት፡፡ ለመተኮስ የተዘጋጁ ነበር የሚመስሉት፡፡ በሰዓቱ ከእኔ ሌላ ሁለት የእህቴ ልጆች ግቢው ውስጥ ነበሩ፤ እየተጫወቱ ነበር፡፡ መሳሪያ የለበሱ ሰዎችን ውክቢያ አይተው ህጻናቱ በጣም ደነገጡ፤ አለቀሱ፡፡ አንደኛው ህጻን 4 አመቱ ነበር፡፡ በዚህ ቀን ባየው ሁኔታ ለቀናት ማታ ሲተኛ ይቃዥ ነበር፡፡ እንዲያውም ወንድሜ ይሄን ተመልክቶ እንዴት ህጻን ልጅ ፊት እንዲህ ታደርጋላችሁ በማለቱ ታስሮ ነበር፤ በበነጋታው ቢፈታም፡፡

ቤት እንደገቡ ፍተሻ ጀመሩ፡፡ እያንዳንዷን ነገር አስሰዋል፡፡ እያንዳንዷ ወረቀት ላይ አስፈርመውኛል፡፡ በጣም ረጂም ጊዜ የወሰደ ፍተሻ ነበር ያደረጉት፡፡ እናቴ ሳትመጣ ቶሎ እንዲጨርሱ ብመኝም ሊጨርሱ አልቻሉም፡፡ ስልክ እየተደዋወሉ ስለሚያገኙት ወረቀት ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ አንድ ‹‹ቃሊቲን በጨረፍታ›› የሚል ጽሁፍ ያለበት ጋዜጣ ሲያገኙ፣ ‹‹ይሄ ምንድነው የሚለው?›› አሉኝ፡፡ ‹‹ቃሊቲን በጨረፍታ›› አልኳቸው፡፡ እነሱም የፌዝ እየሳቁ ‹‹በጨረፍታ ሳይሆን በደንብ ታየዋለህ›› አሉኝ፡፡ ለማስፈራራት የተጠቀሙት እንደሆነ በማሰብ ዝም አልኳቸው፡፡

ሶስት ሰዓት የጀመረው ፍተሻ እስከ ቀኑ ስድስት ሰዓት ዘልቋል፡፡ ሳትመጣ እንዲወስዱኝ ብፈልግም እናቴ መጣች፡፡ በህይወቴ እናቴ እንዲያ ፊቷ ሲለዋወጥ አይቼያት አላውቅም፡፡ በጣም ደነገጠች፡፡ በኋላ ቀስ እያለች እየተረጋጋች መጣች፤ እንዲያውም በኋላ ላይ ምኝታ ቤቷን ቆማ ያስፈተሸችው ራሷ ናት፡፡ ፍተሻው ሲያልቅ ከነጋ ስላልበላሁ በጣም እርቦኝ ነበር፡፡ ትዝ ይለኛል…ፓስታ ነገር ነበር እሱን በላሁ፡፡ ‹‹እንሂድ›› ሲሉኝ እናቴ ‹‹ልጄን የት ነው የምትወስዱት?›› አለቻቸው፡፡ ከመካከላቸው አንዱ ‹‹ማዕከላዊ›› አላት፡፡ እኔም በዚሁ የምሄድበትን አወቅሁ፡፡

መኪና ላይ ወጥቼ ከፊትና ከኋላ በታጠቁ ሰዎች በመኪና ታጅቤ ወደ ማዕከላዊ ወሰዱኝ፡፡ እኔን ለመያዝ ወደ አስራ ሁለት ፖሊሶችና አራት ደህንነቶች ነበሩ የተሰማሩት፡፡ ማዕከላዊ እንደደረስን ተመዝግቤ ወደ ውስጥ እንድገባ ተደረግሁ፡፡ መጀመሪያ የገባሁበት ቤት ውስጥ የተቀበለኝ ድምጽ በኦሮምኛ ቋንቋ ስለነበር አልተረዳሁትም፡፡ እኔ የገባሁበት ክፍል ውስጥ የነበሩት እንዳለ ኦሮሞዎች ነበሩ፡፡ ‹‹እስር ቤቶች ቋንቋቸው ኦሮምኛ ነው›› የሚለው ዓረፍተ ነገር በአዕምሮየ መጣ፡፡ ሁሉም በኦሮምኛ ሲያወሩኝ ኦሮምኛ እንደማልችል ነገርኳቸው፤ አማርኛ የሚችሉት አወሩኝ፡፡ ከመካከላቸው አበበ ኡርጌሳ የሚባል ልጅ በጣም አረጋጋኝ፡፡ አወራን፡፡ የሚያወራኝ ስላገኘሁ ደስ አለኝ፡፡

2. ‹‹ቆሻሻ ስድባቸው አጥንት ይሰብራል›› አበበ ኡርጌሳ

ሚያዝያ 2006 ዓ.ም ላይ ሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ችግር ነበር፡፡ በዚያ ወቅት እኔ ሀሮማያ ነበርኩ፡፡ ያኔ አንተ ነህ ችግር የምትፈጥረው ተብዬ ታስሬ ነበር፡፡ ግን ከቀናት በኋላ ተፈታሁ፡፡ ስፈታ ወደ ሸዋ መጣሁ፡፡ እዚህ መጥቼ ግን ሰላም አልነበረኝም፡፡ ደህንነቶች እየደወሉ ያስቸግሩኝ ነበር፡፡ ስራ ለመፈለግ ከአክስቴና ከእህቶቼ ጋር ነበር የምኖረው፡፡ ግንቦት 17/2006 ዓ.ም ጠዋት አክስቴ ቤት አልነበረችም፤ እኔ ቤት ውስጥ ፊልም እያየሁ ሳለ በሩ በኋይል ተደበደበ፡፡ ተነስቼ መጋረጃውን ገለጥ አድርጌ ሳይ በፖሊስና በደህንነት ተከብቤያለሁ፡፡ ቤቱን ሳልከፍት ትንሽ ቆየሁ፤ በሩን በጉልበት ሊገነጥሉት ሲሆን ከፈትኩላቸው፡፡

በሩን ከፍቼ ወጣ እንዳልኩ አንዱ ደህንነት በቡጢ መታኝ፡፡ ወዲያው በራሴ ቀበቶ እጆቼን የፊጥኝ አሰሯቸው፡፡ እግሬንም አሰሩኝ፡፡ አካባቢውን በደንብ ቃኘት ሳደርግ ስድስት መኮኖችና 18 ፖሊሶች እንዲሁም 8 ደህንነቶችን (ሲቪል የለበሱ) ቆጠርኩ፡፡ ይሄ ሁሉ እኔን ለመያዝ ነው ብዬ ተከረምኩ፡፡ እመቤት የምትባል እህቴ ‹‹ወንድሜን አትሰሩት›› በማለቷ ደብድበዋታል፡፡ ደጅ ላይ አስረው ትንሽ ከቆዩ በኋላ (ይደዋወላሉ፣ ይጠቃቀሳሉ) ተሸክመው መሀል ላይ ካለው መኪና ውስጥ አስገቡኝ፡፡ ለምን አሰሩኝ፤ ራሴ መኪና ውስጥ እገባላቸው ነበርኮ እያልኩ አስባለሁ፡፡

መኪና ውስጥ አስገብተውኝ ትንሽ እንደተጓዝን ደግሞ መኪኖችን ወዲህና ወዲያ ካሽከረከሯቸው በኋላ ዓይኔን ሸፍነው ሌላ መኪና ውስጥ አስገቡኝ፡፡ ሁኔታው ሁሉ ድብልቅልቅ ሲልብኝ ይታወቀኛል፡፡ የሆነ ቦታ ስንደርስ ‹‹እኛ እንኳን አንተን…›› እያሉ መኪናው ላይ ይደበድቡኝ ጀመር፡፡ ዓይኔ ስለተሸፈነ ወዴት እየወሰዱኝ እንዳለ አላውቅም፡፡ ከዚያ የሆነ ቦታ ወስደው ሲያወርዱኝ ይታወቀኛል፡፡ እዚያ ቦታ ለአምስት ቀናት ያህል ዓይኔን እየሸፈኑ ደብድበውኛል፡፡ ደሞ ከዱላው በላይ ቆሻሻ ስድባቸው አጥንት ይሰብራል፤ ‹‹እናትህ እንዲህ ትሁን…ምናምን…›› እያሉ ይሳደባሉ፡፡

የተያዝኩ ለታ ማታውን ሲደበድቡኝ ነበር ያደሩት፡፡ በድብደባው ምክንያት ኩላሊቴን ታመምኩ፡፡ ሽንቴን መቆጣጠር አልችልም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት የነበርኩበት ክፍል ጠረኑ ደስ አይልም ነበር፡፡ በጣም ስታመምባቸው ጊዜ ዓይኔን እየሸፈኑ ሀኪም ቤት ሁለቴ ወስደውኛል፡፡ ግን ስመለስ ድብደባው አይቋረጥም፡፡ ሀኪም ቤቱ የት እንደነበር አላውቅም፡፡ አንዴ ሀኪሟን ‹‹የት ነው ያለሁት›› ብየ ስጠይቃት ‹‹ያመጡህን ሰዎች ጠይቃቸው›› አለችኝ፡፡

በዚህ ሁኔታ የማላውቀው ስፍራ ለአምስት ቀናት ስቃየን ካየሁ በኋላ ግንቦት 22/2006 ዓ.ም ወደ ሌላ ስፍራ ተወሰድኩ፡፡ ለካ አሁን የተወድኩበት ቦታ ማዕከላዊ የሚባለው ኖሯል፡፡ ይሄንም ሰዎች ናቸው የነገሩኝ፡፡

ዘመዶቼ ሞቷል ብለው ነበር የሚያስቡት፡፡ ከተያዝኩ ጀምሮ እስከ ሰኔ 2/2006 ዓ.ም የት እንዳለሁ የሚያውቅ አልነበረም፡፡ አንድ የሚያውቀኝ ሰው ማዕከላዊ አይቶኝ ነው ለዘመዶቼ ደውሎ ያለሁበትን ቦታ የነገረልኝ፡፡

 

3. ‹‹ማዕከላዊ ስገባ ደጋግሜ አስመልሻለሁ›› ሸህቡዲን ነስረዲን

ዕለቱ የካቲት 14/2007 ዓ.ም ነበር፤ ጠዋት ላይ ነው፡፡ በዚያ ቀን ከእህቴ ጋር ነበርኩ፡፡ በር ተንኳኩቶ ስከፍት አንድ የማውቀው ደህንነት በሩ ፊት ቆሟል፡፡ ሌሎችም ፈንጠር ፈንጠር ብለው ቆመዋል፡፡ ወደ ኋላዬ ዞር ስል እህቴ ሀያት ነስረዲን ሁኔታውን እየተመለከተች ነበር፡፡ በሩ ፊት ለፊት የቆመው ደህንነት ወደውስጥ እየገባ ‹‹ሰላም አሊኩም›› አለን፡፡ ለሰላምታው አጸፋውን መለስን፤ የሰውየው ንግግር ቃናውን ሳየው ሙስሊም ይመስለኛል፡፡

ደህንነቱ ወደ ውስጥ ሲገባ ሌሎች ፈንጠር ፈንጠር ብለው ቆመው የነበሩትም ተከታትለው ገቡ፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን የቤቱ ባለቤት ታላቅ እህታችን ሽንት ቤት ስለነበረች ያወቀችው ነገር አልነበረም፡፡ ፖሊሶችና ደህንነቶች ተከታትለው ወደ ግቢው እየገቡ እያለ ሰላምታ ያቀረበልን ሰው እኔን ‹‹ተንበርከክ!›› አለኝ፡፡ እህቴ ሀያትን ዞር ብዬ ሳያት ‹‹እንዳትንበረከክ! ለምንድነው የምትንበረከከው?›› አለች በኃይለ ቃል፡፡ ወዲያው በሀያት ንግግር የተበሳጩት ደህንነቶች ሀያትን አመናጭቀው ከእኔ አራቋት፡፡ እኔንም በኃይል እንድበረከክ አደረጉኝ፡፡

ታላቅ እህታችን ከሽንት ቤት ስትመለስ የሚሆነውን ሁሉ አየች፡፡ ብዙም አልተደነቀችም፡፡ እህቴን አናገሯትና ወደ ቤት ውስጥ ለፍተሻ ገቡ፡፡ ትንሽ ሶፋውን ገልበጥ ገልበጥ እንዳደረጉ የእህቴ ባል ዱባይ ሀገር ከመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈጌሳ ጋር የተነሳውን ፎቶ አዩ፡፡ (የእህቴ ባልና ሲራጅ ፈጌሳ ወንድማማቾች ናቸው፡፡) ፎቶውን እንዳዩ ‹‹ቤቱ የስርዓቱ ተቃዋሚ አይደለም›› ብለው ፍተሻውን አቋርጠው ወጡ፡፡

መጀመሪያ እኔን ብቻ የሚወስዱ የሚመስሉት ፖሊሶችና ደህንነቶች ከቤት እንደወጡ ወደ እኔና ሀያት እየተመለከቱ ‹‹እንሂድ›› ሲሉ አዘዙን፡፡ ከዚያም በፒክአፕ መኪና አስገብተው ወደሆነ ጫካ ወሰዱን፡፡ እዚያ ጫካ ውስጥ ለሁለት ሰዓት ያህል ቆመን ቆይተናል፡፡ በኋላ እንደገና በመኪና ወደ እናታችን ቤት ወሰዱን፡፡ ወደ እናታችን ቤት እየሄድን ሳለ እህቴ ሀያት እጆቼን እየደባበሰች ‹‹እነዚህ ጥፍሮችህ ሊነቀሉ ይችላሉ…አይዞህ ጠንክር›› አለችኝ፡፡ ሀያት በጣም ጠንካራ ልጅ ናት፡፡ ብዙ ነገሮች በምርመራ ወቅት ሊደርሱብኝ እንደሚችሉ ትነግረኝ ነበር፡፡

እናታችን ቤት እንደደረስን ከመኪና ወርደን ወደውስጥ እንድንዘልቅ ተደረግን፡፡ እናቴ ሁኔታውን ስታይ ደነገጠች፤ ግን ደግሞ  ፍተሻው ተከናውኖ ሲያልቅ የሚበላ ነገር ቀመስን፡፡

ማዕከላዊ ደርሰን ምዝገባ ካከናወን በኋላ እኔና ሀያት ተለያየን፡፡ እኔን ወደ 8 ቁጥር ቤት ነበር የወሰዱኝ፤ ጨለማ ክፍል ነው፡፡ ልክ ክፍሉ ውስጥ ስገባ ባዶ ነው፤ አንዲት ፍራሽ ታጥፋ ተቀምጣለች፡፡ ክፍሉ በጣም ይገማል፡፡ አንድ ጥግ ላይ የሽንት እቃ አለ፤ ሽንት ሞልቶበታል፡፡ ሰገራም ሌላኛው ጥግ ላይ አየሁ፡፡ ግማቱን አልቻልኩትም፡፡ ደጋግሜ አስመለስኩ፡፡ በጣም ይቀፍ ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ሽታውን ረስቼ ሌላ ሀሳብ ውስጥ ሰጠምኩ፡፡ ስለ እህቴ ሀያትም ሀሳብ ገባኝ፡፡

 

(ማስታወሻ፡– ሸህቡዲን ነስረዲን በእድሜ ለጋ ወጣት ሲሆን በእነ ከድር መሃመድ የክስ መዝገብ 16ኛ ተከሳሽ ነው፡፡ በዚሁ መዝገብ እህቱ ሀያት ነስረዲን 17ኛ ተከሳሽ ነች፡፡ የጸረ-ሽብርተኝነት አዋጁን አንቀጽ 7(1)ን በመተላለፍ ወንጀል የሽብርተኝነት ክስ ነው አቃቤ ህግ የመሰረተባቸው፡፡ )

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *