የመሬት መብት ተሟጋቹ ቄስ ኦሞት አግዋ ሁለት መከላከያ ምስክሮቹን አሰማ። (ሰኔ 05/2009)

በእስር ላይ የሚገኙት የቀድሞው የጋመቤላ ክልል ፕሬዝዳንት ኦኬሎ አኳይ የቄስ ኦሞት መከላከያ ሆነው ቀረቡ።
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት ዛሬ ቀን ሰኔ 05/2009 ዓ.ም በዋለው ችሎት ኦሞት አግዋን መከላከያ ምስክሮች ሰምቷል። ተከሳሹ በመጋቢት 18/2009ዓም ካሰማቸው 5 የመከላከያ ምስክሮች በተጨማሪ ዛሬ ሁለት መከላከያ ቀርበው ምስክርነታቸው ሰጥተዋል።
የተከሳሹ ጠበቃ በእለቱ ከተገኙት ሁለት ምስክሮች በተጨማሪ ከዘዋይና ሸዋ ሮቢት የፌደራል ማረሚያ ቤቶች መምጣት የነበረባቸው ምስክሮች አንዳሉ ጠቅሰው ዛሬ የቀረቡት ምስክሮች እንዲሰሙላቸው ለፍርድ ቤቱ አስመዝግበዋል። አቃቤ ህግም ቅሬታ አለኝ በማለት ምስክሮቹ የሚመሰክሩበት ጭብጥ ተመሳሳይ ስለሚሆንና ቀሪ ምስክሮች የሚመሰክሩበትን ጉዳይ አጥንተው ሊመጡ ስለሚችሉ ሌላ ቀጠሮ ተይዞ ሁሉም ምስክሮች ይመስክሩ ብሏል። የተከሳሽ ጠበቃም አሁን የተገኙት ምስክሮችና ከማረሚያ ቤት የሚመጡት ምስክሮች የሚመሰክሩበት ጉዳይ ጭብጥ ተመሳሳይ ስላልሆነ በእለቱ የተገኙት ምስክሮች ቢመሰክሩ ችግር እንደሌለው ጠቅሰው ፍርድ ቤቱም ተቀብሎታል።

በእለቱ የቀረቡት መከላከያ ምስክሮች አቶ ሳምሶን አባተና የቀድሞው የጋምቤላ ክልል ፕሬዝዳንት ዳኞት ፊት ቆመው ቃለ መሀላ ከፈፀሙ በኋላ ምስክር የመስማት ሂደቱ ተጀምሯል።
በቅድሚያ የአቶ ሳምሶን አባተ ምስክርነት የተደመጠ ሲሆን፤ ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ በመንግስት ስራ የሚተዳደሩ ግለሰብ መሆናቸውን ተናግረው ኦሞት አግዋን የሚያቋቸው በ1996 ዓ.ም ጋምቤላ ክልል በተነሳ ግጭት በክልሉ መንግስት በተቋቋም የሰላም ኮሚቴ ውስጥ አባል ሆነው ግጭቱን ለማብረድና ግጭቱን በመሸሽ የተሰደዱ ዜጎችን ለማስመለስ ሲሰሩ እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ተናግረዋል።
ምስክሩ ሲቀጥሉ አቶ ኦሞት አግዋ በ1996 ዓ.ም ህዳር ወር በጋምቤላ በተፈጠረው ግጭት ምክንያት ሸሽተው ጫካ የገቡና ወደ ደቡብ ሱዳን የተሰደዱ ዜጎች ወደ ሚኖሩበት መንደር እንዲመለሱ በክልሉ መንግስት በተቋቋመው ኮሚቴ ውስጥ ከሌሎች ሽማግሌዎች ጋር በመሆን ይሰሩ ነበር፤ “የጋምቤላ ሰለምና ልማት ጉባኤ” የሚባል ምግባረ ሰናይ ድርጅትም መስርተው ሲሰሩ ነበር፤ መንግስትም ከዚህ ግብረሰናይ ድርጅት ጋር በጋራ በመሆን 20ሺ የሚጠጉ ስደተኞች ወደ መንደራቸው እንዲመለሱ አርገዋል ብለዋል።
ምስክሩ በመቅቱ ጋምቤላ ክልል ምን ሲሰሩ እንደነበር በተከሳሽ ጠበቃ በቀረበላቸው ጥያቄ የክልሉ መንግስት ጋዜጠኛ ሆነው ይሰሩ እንደነበርና አቶ ኦሞትንም የሚያወውቋቸው የጋዜጠኝነት ስራቸውን ሲሰሩ እንደሆን ገልፀዋል።
በማስቀጠል የእለቱ ሁለተኛ ምስክር የሆኑት የቀድሞ የጋምቤላ ርእሰ መስተዳድርና “ጋምቤላን ከፌደራል መንግስቱ ለማስገንጠል ተንቀሳቅሰዋል” ተብለው የ9 ዐመት እስር ተፈርዶባቸው በቃሊቲ ማረሚያ ቤት ፍርዳቸውን እየፈፀሙ የሚገኙት አቶ ኦኬሎ አኳይ ናቸው። አቶ ኦኬሎ አኳይ ቄስ ኦሞትን የሚያውቋቸው ከልጅነት ጀምሮ ይኖሩበት የነበረው ቀበሌ ውስጥ አንድ ላይ እንዳደጉ ተናግረዋል። “እርሶ ይመሩት በነበረው ክልል ውስጥ በ1996ዓ.ም የተፈጠረው ግጭት እንዲረጋጋ ቄስ ኦሞት የነበራቸው ሚና ምንድን ነበር?” ተብለው የተጠየቁት አቶ ኦኬሎ አኳይ ሲመልሱ “በጋምቤል ክልል በተፈጠረ ግጭት ብዙ ንብረቶች ወድመው ነበር፤ በአንድ ከተማ ብቻ 850 ቤቶች ተቃጥለው ነበር፤ በኩልኒዶ ከተማ 3ሺ ሰው ከቀዬው ለቆ ወደ ሱዳን የተሰደደ ሲሆን ከተማዋ ወደመረጋጋት እንድትመለስና የፌደራል መንግስት ባዘዘው መሰረት የሀይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ያሉበት የሰለምና መረጋጋት ኮሚቴ እንዲመሰረት ተደርጓል።

በዚህ ወቅት የመካነ እየሱስ የምስራቅ ጋምቤላ ሲኖድ የነበሩት ኦሞት አግዋ የተቋቋመው ኮሚቴ ውስጥ አባል እንዲሆን አርጌዋለው። በግጭቱ ወቅት በኩልኒዶ ከተማ ከተሰደዱት 3ሺ ዜጎች 2ሺ 4መቶውን እንዲመለስ ያረጉት በዚህ ኮሚቴ አማካኝነት ነው። እኔም የሚሰራውን ስራ ከፌደራል ምንግስቱ ለተላከው ዶር ገብረአብ ባርናባስ ሪፖርት አረግ ነበር።” ብለዋል።
አቃቤ ህግ በበኩሉ እርሶ ከስልጣን ከተወገዱ በኋላ ከኦሞት ጋር ተገናኝተው ያውቃሉ ወይ በሚል ላቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ኦኬሎ ምላሽ ሲሰጡ እሳቸው ከስልጣን ወርደው የተሰደዱት ታህሳስ 30/1996 ዓ.ም እንደሆነና ኦሞትን በአካል ያገኙት በ2007ዓ.ም እስር ቤት መሆኑን፤ ኦሞት በተከሰሰበት ክስ ላይም ከኦኬሎ ጋር ይገናኛል መባሉ ሀሰት መሆኑን የገለፁት አቶ ኦኬሎ ኦሞት አግዋ የሀይማኖት መሪ እንጂ ፖለቲካ ውስጥ እንደማይገባ፤ አብዛኛውን ጊዜውንም ያጠፋው አዲስ አበባ መካኒሳ አካባቢ መፅሃፍ ቅዱስን ወደ አኝዋ ቋንቋ በመተርጎም እንደሆነ ተናግረዋል።
የእለቱን ምስክር የማሰማት ሂደት ያጠናቀቀው ፍርድ ቤቱ ከተከሳሽ ጠበቃ በቀረበለት ጥያቄ መሰረት 3 ቀሪ ምስክሮች ከዝዋይ እና ሸዋ ሮቢት የፌደራል እስር ቤቶች በሚቀጥለው ቀጠሮ እንዲቀርቡ ለማረሚያ ቤት ትእዛዝ ተሰጥቷል። ፍርድ ቤቱ ቀሪ ምስክሮችን ለመስማት ለሀምሌ 20/2009 ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።
ኦሞት አግዋ በ2007 ዓ.ም መጋቢት ወር ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር ለአካባቢ ጥበቃ ወርክሾፕ ኬንያ አገር ሊሄዱ ሲሉ ቦሌ አየር ማረፊያ ተይዘው በፌደራል አቃቤ ህግ ‘በትጥቅ ትግል ስልጣን ለመያዝ የሚነቀሳቀሰው ጋህነን አመራር ናቸው” የሚል የሽብር ክስ ቀርቦባቸው እስከ 2009 ዓ.ም የካቲት ድረስ በእስር ላይ ይገኙ ነበር። የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ህዳር 05 በዋለው ችሎት ተከሳሹ የቀረበባቸው ማስረጃ የሽብር ወንጀል ለመፈፀም እየተንቀሳቀሱ መሆኑን ሳይሆን ጋምቤላን ከፌደራል መንግስቱ ለመገንጠል መሆኑን ነው የሚያሳየው በማለት የተከሰሱበትን የፀረ ሽብር አንቀፅ ወደ መደበኛ ወንጀለኛ መቅጫ አንቀፅ ቁጥር 256/ሀ “ወታደሮችን፣ የሽምቅ ተዋጊዎችን፣ ሽፍቶችን መመልመል” ቀይሮታል። ይህን ተከትሎ ኦሞት አግዋ የዋስትና መብት ቢጠይቁም ፍርድ ቤቱ ዋስትናውን ከልክሏቸው ቢቆይም የፍርድ ቤቱን ውሳኔ ለፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ብለው የ50ሺ ብር ዋስትና ተፈቅዶላቸው ጉዳያቸውን ከእስር ቤት ውጪ ሆነው እየተከታተሉ መሆኑ ይታወቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *