የመተከል ነውጥ አዘጋገብ

የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) የግጭት ዘገባዎች እና አዘጋገቦች ግጭትን በመፍታት ወይም በማባባስ ረገድ ሚና ያላቸው መሆኑን እንረዳለን። በዚህ ረገድ በቅርቡ የተከሰተውን ነውጥ (violence) የተመለከቱ ዘገባዎች እና አዘጋገቦችን ቅኝት አድርገናል። በዚህም በርካታ ክፍተቶች እና ተቃርኖዎች አስተውለናል። እንዲህ ዓይነት ክፍተቶች እና ተቃርኖዎች ግጭቶች እና/ወይም ጥቃቶች በተከሰቱ ቁጥር በቅጡ ተረድቶ መፍትሔ ለመፈለግ የሚያስችል መረጃ እንዳይኖር ከማድረጉም በላይ ፅንፈኝነትን እንዲባባስ እያደረገ መሆኑን አስተውለናል።

በ2012 ማብቂያ፣ ወርሐ ጳጉሜ ጀምሮ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካባቢዎች በንፁኃን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት በተመለከተ የዜና ጣቢያዎች ሲዘግቡበት የነበረበት መንገድና የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ደግሞ መረጃውን በማኅበራዊ ሚዲያው ሲያዘዋውሩበት የነበረው መንገድ ከዚህ እንደሚከተለው ይቀርባል።

የዋና ዋና ሚዲያዎች ዘገባ…  

  1. ትግራይ ቲቪ

የትግራይ ክልላዊ መንግሥት የሚደጉመው ትግራይ ቲቪ ዘገባ የማዕከላዊው መንግሥት ጥቃቱን የመከላከል ሥራ አልሠራም የሚለው መልዕክት ላይ አተኩሯል።

በመተከል ዞን 8 ቀበሌዎች ከጫካ በመጡና ማንነታቸው ባልታወቁ ኃይሎች ጥቃት የተፈፀመ ሲሆን፥ 35,000 የሚሆኑ ነዋሪዎች ቤትና ንብረታቸውን ጥለው ተፈናቅለዋል። በመቀጠልም የብልፅግና አሐዳዊ መንግሥት/ቡድን ጥቃቱን ለማስቆምሞክሯል ያለው ከእውነት የራቀ ነው ሲሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹበሚል አንድ የአካባቢው ነዋሪ ነው ከተባለ ግለሰብ አገኘን ያሉትን መረጃ አቅርበዋል።

የአማራ ክልል የሚደጉመው የአማራ ቲቪ በበኩሉ ነውጡ መንግሥታዊ ባልሆኑ የታጠቁ ኃይሎች የተፈፀመ እና በአማራ እና አገው ብሔረሰብ ተወላጆች ላይ የተፈፀመ ጥቃት ነው የሚል መልዕክት አለው።

የአማራ ክልል የፀጥታና ደኅንነት ግንባታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ገደቤ ኃይሌ  ለክልሉ ቴሌቪዥን በሰጡት መግለጫ የፀረ ለውጥ ኃይሉ በሚያንቀሳቅሳቸው ኃይሎች ሆን ብሎ የሕዳሴውን ግድብ ለማስተጓጎል የተፈፀመ ነው። በጉባና ቡላን ወረዳ አከባቢ የክልሉ መንግሥት የሚያውቀው የታጠቀ ኃይል የሚንቀሳቀስበት ቦታ አለ። ይሄ ኃይል ቤኒን ብሎ ራሱን የሚጠራና የኦነግ ሸኔና ጎህዴድ ጥምረት  ሲሆን የሚደገፈውም በፀረ ሰላም ኃይሉ ነው። በመካከላቸውም ትግርኛ ተናጋሪ አሉበት ብለዋል።  በተወሰኑ የአማራ ተወላጆች ላይ ጥቃት የተደረገ ሲሆን፣ ተፈናቅለው የነበሩ 25,000 ነዋሪዎች ተመልሰዋል ነገር ግን የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ መረጃ ሲጠናቀር እናቀርባለን ብለዋል። ጉዳቱ የደረሰው ‘አማራና አገው ላይ ነው፤ አልፎ አልፎ ጉምዝና ሽናሻ ላይም ጉዳት ደርሷል’፣ ‘…በማኅበራዊ ሚዲያው የሚናፈሰው የተጋነነ ነው፤ ሞቱ ተጎዱ የተባሉ ነገር ግን በሕይወት የተገኙ አሉ’ ሲሉም ጨምረው ገልጸዋል።

በፌዴራል መንግሥቱ የሚደጎመው ኢቲቪ በአንድ በኩል ማንነትን ያደረገ ጥቃት ሳይሆን የአካባቢውን መረጋጋት በማይፈልጉ ሰዎች የተፈፀመ ወንጀል ነው ሲል፣ በሌላ በኩል ከአካባቢዬ ውጡልኝ የሚል መልዕክት ይተላለፍ ነበር የሚል መልዕክት አስተላልፏል።

የመንግሥት ኃላፊዎችን ጠቅሶ በሰራው ዘገባ በቡለን ወረዳ የተፈጠረውን የፀጥታ እግር አስመልክቶ የፌደራልና የሁለቱ ክልሎች አመራሮች ውይይት ማድረጋቸውን አስታውቋል። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን “ከጳጉሜ 1 ጀምሮ የተፈፀመው ድርጊት ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት ሳይሆን የቀጠናውን መረጋጋት በማይፈልጉ ኃይሎች የተፈፀመ ወንጀል ነው።’’  የቤሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አሻይድሌ ሐሰን እንደገለጹት “በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ሽፍታና አሸባሪዎች ኃይሎች፣ በውስጥና በውጪ ፀረ ሰላም ኃይሎች በገንዘብና ሥልጠና የሚደገፉ ቡድኖች የፈፀሙት ድርጊት ነው’’ ብለዋል። የአካባቢው መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ምቹ አለመሆን የክልሉ የፀጥታ ኃይል እርምጃ ለመውሰድ እንዳይችል እንዳረገውና በመከላከያ ሠራዊቱ ፀጥታ ሊመለስ ችሏል ሲሉ ተደምጠዋል።

በተመሳሳይ የኢፌዴሪ መከላከያ ኢንዶክትሪኔሽን ዋና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሜጀር ጀነራል መሐመድ ተሰማ  በሰጡት መግለጫ  በወንበራ፣ ጉለንና ጉማ ወረዳዎች በአካባቢው በሕገ ወጥ መንገድ የተሰባበሰቡ ሽፍቶች ሕዝብ ላይ ተኩስ ከፍተው የደረሰ አደጋ እንደነበረ በዚህም ሰው እንደሞተ፣ እንደቆሰለ፣ ንብረት እንደወደመና እንደተፈናቀለ አስረድተዋል። ‘’የተፈፀመው ሁኔታ ከአካባቢዬ ውጡልኝ በሚል ቅስቀሳ የተደረገ ነው፣ በዳንጉር፣ መንድራና ፓዌ ደግሞ ሌላ ጥቃት ሰንዝረዋል። በተለያየ ጊዜ ከመንግሥት ፀጥታ ኃይል በዲሲፕሊን የተባረሩ፣በአካባቢው ያኮረፉ ራሳቸውን ወደሽፍትነት የቀየሩ ናቸው ይህንን የፈፀሙት’’ ብለዋል

ከተቃዋሚዎች ጋር ግንኙነት አለው የሚባለው ኢሳት ቴሌቪዥን የጉዳቱን መጠን በመግለጽ ላይ ያተኮረ እና ከድርጊቱ ጀርባ ሕወሓት አለበት የሚሉ አስተያየቶችን ያዘለ መልዕክት አስተላልፏል።

በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ አይጋሊ እና ኤጳር ቀበሌ ጳጉሜ 1 ቀን 80 ንፁኃን ዜጎች በስለትና በቀስት መገደላቸውን፣ ከነዚህም መካከል ከልጆቿና ባለቤቷ ጋር የተገደለችው የ3 መንትዮች እናት ትገኛለች ሲል አስደምጧል። ቤታቸውን ጥለው የሸሹት ደግሞ ቤታቸው እየተዘረፈና ሰብላቸው እየወደመ መሆኑን ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። ጥቃት አድራሾቹ ፍላጎታቸው ምንድነው ማናቸው ተብለው ለተጠየቁትም “የተቀናቃኝ ፓርቲ ተልኮ ያላቸውና ውስጣቸው ኦነግ የሆነ ነው’’፣ “ከመለስ ጋር ይሠራ የነበረ ቤኒን የሚባል ያሰለጠናቸው ናቸው”፣ “ሕወሐት ከመስከረም 1 በኋላ መንግሥት የለም አስወጡ እያለ ጉምዞች ናቸው ያስወጡት የሚሉት’’፣ ‘’የሕወሓትና ኦነግ የተቀላቀሉ ተልዕኮ ያላቸው ናቸው ሲባል እንሰማለን’’ ሲሉ የየራሳቸውን ሐሳብ ሰጥተዋል። በተጨማሪም ነዋሪዎቹ የደረሰባቸውን እንግልት አስረድተዋል።

በእንግሊዝ ሕዝብ የሚደጎመው ቢቢሲ የአማርኛ ክፍል ፕሮግራም ደግሞ ጉዳተኞችን በማነጋገር የጉዳቱን መጠን፣ መንስዔና ተጠቂዎች ማንነት የሚያመላክት መልዕት አቅርቧል።

በአካባቢው ማንነታቸው ያልታወቀ በቁጥር በርካታ የሆኑ ከዚህም በፊት ጥቃት የፈፀሙ የታጠቁ ኃይሎች ጥቃት እንደፈፀሙና ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች እንደተገደሉ፣ ንብረት ላይም ጉዳት እንደደረሰ ዘግቧል። ጥቃት ፈፃሚዎቹ ሰዎችን ከመግደል በተጨማሪ መኖሪያ ቤታቸውንም እንደሚያቃጥሉና ዘረፋ እንደሚፈፅሙ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል። መንስኤውንም ገዳዮቹ ለሚፈፅሙት ግድያ ምንም ዓይነት ምክንያት እንደሌላቸውና ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ አለመታወቁ ነዋሪውን ግራ እንዳጋባ አንድ ጉዳት የደረሰባቸው የአካባቢው ነዋሪ ተናግረዋል ብሏል። እኚህ በጥቃቱ ምክንያት በጳጉሜ 1 ቀን ምሽት 1 ሰዓት አካባቢ በቡለን ወረዳ አባታቸውን ያጡት ግለሰብ ለሳምንት አስክሬን አግኝተው ለመቅበር እንዳልቻሉም አክለዋል።  ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ ደግሞ ጥቃት ከመፈፀሙ በፊት በነዋሪው ዘንድ ስጋቶች እንደነበሩ  ገልጸዋል።

ተመሳሳይ ጥቃት በመተከል ዞን ዲባጢ እና ወንበራ ወረዳዎች ላይ በታጣቂዎች ተፈፅመዋል። በቡለን ወረዳ በሁለት ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ እና ከጉሙዝ ተወላጅ ውጪ የሆኑ ሰዎች ላይ ጥቃት እንደተፈፀመና፣ ወንበራ ላይ ከጳጉሜን 2/2012 በፊት 3 ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም 4 የሚደርሱ ሰዎች ደግሞ ታግተው መወሰዳቸውን ተናግረዋል። በዚሁ ወረዳ ከዚህ ቀደምም ታግተው የተወሰዱ ሴቶች እንደነበሩና እስካሁን የት እንዳሉ እንደማይታወቅ ከነዋሪዎቹ ያገኘውን መረጃ አስፍሯል። በጥቃቱም የተጎዱትን ሰዎች ትክክለኛ ቁጥር ለማወቅ ያደረገው ጥረት እንዳልተሳካና በነዋሪዎች ግምት መሠረት ግን በጥቃቱ እስከ 50 የሚደርሱ ሰዎች መሞታቸው ሲገልጹ፤ የወደመውና የተዘረፈው ንብረት መጠንን ለማወቅ እንዳልቻሉ ተናግረዋል ብሏል።

በአሜሪካ መንግሥት የሚደጎመው የአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ክፍለ ጊዜ በወቅቱ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ የተፈፀመው ምንድን ነው የሚለውን ከአካባቢው ባለሥልጣናት ያገኘውን መረጃ አስተላልፏል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ቡለንና ወንበራ ወረዳዎች የታጠቁ ኃይሎች በነዋሪዎች ላይ ጥቃት እንዳደረሱ ቪኦኤ ገልጿል። የቡለን ወረዳ አስተዳደር ‘’የሰላም ሥጋት እንጂ ጥቃት እንደደረሰ መረጃ አልደረሰንም’’ ብሏል። ጥቂት ሰዎችም ታግተው እንደተወሰዱ የወንበራ ወረዳ አስታውቋል። የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ጥቃቱን የፈፀሙት የቤኒሻንጉል ህዝብ ነፃነት ንቅናቄ /ጉህነን/ ኃይሎች መሆናቸውን ገልጸው፣ ታፍነው የተወሰዱ መኖራቸውን አምነው የተገደሉትን በተመለከተ ግን የተጠናቀረ መረጃ የለንም ብለዋል። አንድ የአካባቢው ነዋሪ እንደሚለው ቁጥራቸውን በትክክለኛ ያላወቃቸው ሰዎች እንደተገደሉና፣ ሴቶችንም አግተው ለሳምንታት በጫካ ውስጥ እንደሚያቆዩ ተናግሯል።

አውሎ ሚዲያ የተባለው የዩቱዩብ ሚዲያ በበኩሉ በጥቃቱ ጉዳት የደረሰባቸውን በማናገር ስለጉዳቱ መጠን በማመላከት የአካባቢው ባለሥልጣናት ማብራሪያ ለመስጠት እንዳልተባበሩ አመላክቷል።

አውሎ ሚዲያ እንደዘገበው በነሐሴ 29 እና ከጳጉሜ 1 ጀምሮ በተፈፀመ ጥቃት 89 ሰዎች ተገድለዋል። በተለይ ይባር፣ ኮሾጎንድ እና ሞጆ ቀበሌ የሚዘገንን ድርጊት እንደተፈፀመ 7 ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ግለሰብ ተናግረዋል።  ከለሊቱ በ9 ሰዓት አካባቢ ከመኖሪያ ቤታቸው እያፈኑ በመውሰድ ት/ቤት ውስጥ ከዘጉባቸው በኋላ ብር አምጡ ሲሉ እንደነበርና እምቢ ያሉትን ከ40 በላይ ሰዎች በት/ቤቱ ውስጥ በየተራ አውጥተው ገደልዋቸው ብሏል። ጥቃት ፈፃሚዎቹ ለምን ይሄን እንደፈፀሙ ሲጠየቁም “ብድር እንመልሳለን ነው የሚሉት አብረናቸው የኖርን ቢኒ የሚባሉትና ሀገርኛው ሆነው ዘርን መሰረት ያደረገ ጥቃት ነው የፈፀሙብን’’ ሲሉ አስረድተዋል። 

የአካባቢው ነዋሪዎች አጥቂዎቹን በሥም ለይተው እንደሚያውቋቸው ነገር ግን የአካባቢውን ፀጥታ አካል ስለማያምኑት መከላከያ እስኪመጣ እንደሚጠብቁ ተናግረዋል። “አጥቂዎች መጀመሪያ ሲነሱ ኦነግ እንደሆኑ ነው የምናውቀው’’ ብለዋል።

ነገር ግን አውሎ ሚዲያ ሌሎች መረጃዎችን ለማግኘት ወደ አመራር አካላት የስልክ ጥሪዎችን በሚያደርግበት ወቅት ምላሽ ሊሰጠው እንዳልቻለ ቪዲዮው ያሳያል።

በጀርመን መንግሥት የሚደጎመው ዶቸ ቨለ የዓይን እማኞችን በማናገር ጥቃቱን እየፈፀሙ የነበሩት ሰዎች በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ ስለመሆናቸው እና ከፍተኛ ጉዳት ማድረሳቸውን ተናግሯል።

በተመሳሳይ ዶቸ ቬለ በሁለቱ ወረዳዎች ማለትም በቡለንና ወንበራ የታጠቁ ኃይሎች በነዋሪዎች ላይ ጥቃት እየፈፀሙ እንደሆነ ዘግቧል።

ነዋሪዎችን አነጋግሮ እንደዘገበው በተለይም በ2 ወረዳዎች ከአንድ ወር ጀምሮ ማንነታቸው ያልታወቁ ታጣቂዎች ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ እንደነበርና ሕንፃ ማፍረስ የሚችል መሣሪያ እንደታጠቁ የሚናገሩት ነዋሪዎቹ የፀጥታ ኃይሉ ለመከላከልና ተከታትሎ ለመያዝ ቢሞክርም አስቸጋሪ መሆኑንና በአንድ አቅጣጫ ሲታዩ በሌላ አቅጣጫ በመምጣት በሰው ልጅ ሊፈፀም የማይገባው ጥቃት እየፈፀሙ እንደሆነ አመልክተዋል። በዋናነት ታጣቂዎቹ ጥቃቱን የሚፈፅሙት በቀን እንደሆነና ከአንዳንድ የመንግስት መዋቅር አካላት ጋር ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚችልም ገምተዋል፤ ምክንያታቸውን ሲገልፁም «ታጣቂዎች ወደነበሩበት አካባቢ የፀጥታ ኃይል ሲንቀሳቀስ ቀድሞ መረጃ ስለሚደርሳቸው አካባቢውን ለቅቀው ይሰወራሉ» ብለዋል፡

በዚህ ሁኔታ በርካታ የቆሰሉ፣ ሕይወታቸው ያለፈ ነዋሪዎች መኖራቸውንና ከታጣቂ ኃይሉ በኩልም በቁጥጥር ሥር የዋሉ እንዳሉ አስረድተዋል፡፡

የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች

በማኅበራዊ ተጠቃሚዎች ዘንድ በአብዛኛው እውነታቸው ያልተረጋገጡ መረጃዎች፣ በራስ የዕይታ አቅጣጫ ላይ ብቻ ተመርኩዘው የሚሰጡ ትንታኔዎች፣ ሐሰተኛ የሆኑ ምስሎች፣ ለማየት የሚከብዱ ምስሎች ሲዘዋወሩ ነበር። ይህም በመረጃና እውነታ ላይ ባልተደገፈ መልኩ የሚዘዋወሩ ግምታዊ መረጃዎች በተፈጠረው ሁኔታ ስሜቱ የተጎዳውን ማኅበረሰብ ይበልጡኑ ስሜታዊ እንዲሆንና ለበቀል እንዲነሳሳ እንዲሁም ሁሉም በየራሳቸው አተያይ/ግምት የጥቃቱ አስተባባሪ ወይንም አድራሽ ነው ብለው ለሚያስቡት ወገን አንባቢዎች ፍፁም ጥላቻ እንዲያድርባቸው በሚያደርግ መልኩ መረጃዎችና ምስሎች ሲዘዋወሩ ነበር።

ሁኔታውን ብዙዎች በተለያየ መንገድ የየራሱን ሐሳብና ግምት ሲሰጡበትና ራሳቸው የሚፈልጉት አጀንዳ ለማስቀየርም ሲሞከርበት ተስተውሏል፣ በምሳሌነትም፡-

  • በመተከል በጉሙዝ ሕዝቦች ላይ ጭፍጨፋ እየተካሔደ ነው፤ ትናንት የኦሮሞን ጡት መቁረጥ የለመዱ የሚኒልክ ልጆች ዛሬ የወንድን ብልት እየቆረጡ ነው የሚል፣ (ለማየት የሚከብድና ያልተረጋገጠ ምስል ተያይዞበታል)
  • መተከል ሌላኛዋ የግብፅ ካርታ ናት፤ ስለዚህም በመተከል ዞን የሚገኘው ጉባ ወረዳን ለሕልመኛ የግዛት ተስፋፊ ፖለቲከኞች ስጦታ በመስጠት እነሱን ደግፎ ግድቡን በማጨናገፍ አማራን ከነባር ርስቱ አስወግዶ ኢትዮጵያን የማፍረስ ሴራ ውጤት ነው የሚል
  • አማራ አለቀ ይባል እንጂ እልቂቱ የሚፈፀመው በጉምዝና አገው ላይ ነው፣ ስለዚህ የመተከል ጉዳይ የብልፅግና አመራሮች ችግርና የግዛት ማስፋፋት ችግር ነው የሚል፣…  
  • ይህ አማራን የማዳከም ሴራና ለም የሆነውን አካባቢ መሬት ለትግራይ ባለሀብቶች ተፈልጎ ነው፣ ለዚህም ነው ምክንያት እየተፈለገ አማራ እንዲንገላታ፣ እንዲታሰር፣ እንዲገደል እና እንዲባረር የሚደረገው የሚል፣…
  • ሰላም የሰፈነበትን የአማራ ክልል እና የአማራ ሕዝብን በማስቆጣት፣ ለመስከረም 30 ግብዓት ለማድረግ የተፈለገ ይመስላል፣ የሚል… እና
  • በመንግስት ስፖንሰር የተደረገ ነው የሚል ይገኙበታል።

መደምደሚያ

በመተከል ዞን የተፈጠረውን ትክክለኛ ሁኔታ አስመልክቶ በዚህ ዳሰሳ ሊደረስበት የሚችል ጥናት አልተደረገም ስለሆነም እውነተኛ መረጃ ያደረሰው ብዙኃን መገናኛ ይህ ነው ብሎ ለመናገር ባያስደፍርም፣ መደበኛ የዜና አውታሮችን ዘገባ በምንመለከትበት ወቅት ግን የተለያየ አቋም ያላቸው ብዙኃን መገናኛዎች ከአካባቢው ነዋሪዎች አገኘን ብለው የሚያቀርቡት መረጃ እነሱ ከሚያራምዱት ‘ሐሳብና የፖለቲካ አቋም ጋር የሚመሳሰል መሆኑ እውነተኛውን መረጃ ነው ወይ የሚያደርሱት?’፣ ‘በአካባቢው ነዋሪ ነን የሚሉ ንፁኃኖችስ እንዴት እንደዚህ የተራራቀ ሐሳብ ለተለያዩ ሚዲያዎች ሊሰጡ ቻሉ?’ የሚለው የቀረቡትን መረጃዎች እውነትነት ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ ያደርገዋል። ለዚህም ትግራይ ቲቪና ኢሳትን መጥቀስ ይቻላል። በሌላ በኩል ትግራይ ቲቪ ‘አሐዳዊውን የብልፅግና መንግሰት’፣ ኢሳት ‘ኦነግና ህውሀት’ን፣ ኢቢሲ ‘ለውጡን ለማደናቀፍ የሚፈልጉ ፀረ-ሰላም ኃይሎችንና በውስጥና በውጭ ኃይሎች የሚታገዙ ቡድኖች’ን፣ አማራ ቲቪ ደግሞ ‘በፀረ-ሰላም ኃይሎች የሚታገዙና ትግርኛ የሚናገሩ ያሉበት ቡድኖችን’ በየትኛውም የአገሪቷ ሁኔታ ውስጥ ሲወቅሱ ይስተዋላል።

ለዚህም ሁኔታውን ወደራስ አጀንዳ የመውሰድ ነገር የተስተዋለበት የትግራይ ቲቪን ዘገባ ማንሳት ተገቢ ነው። ዜናው በመተከል የተፈፀመውን ሁኔታ ከወገንተኝነት በፀዳ መልኩ እውነታውን ከማቅረብ ይልቅ በትግራይ ክልል በአብዛኛው ተቀባይነት ለሌለው ብልፅግና ፓርቲ ያላቸውን የተቃዋሚነት ድምፅ አጉልቶ ለማሰማት በሚመስል መልኩ የቀረበ ነው። በተለይም አንድ የአካባቢው ነዋሪ ነው የተባለ ግለሰብን ብቻ በማነጋገር ‘የአካባቢው ነዋሪዎች ስለ አሀዳዊው ብልፅግና ፓርቲ የገለፁት’ በሚል እንዲህ ዓይነት በበቂ ማስረጃ ላይ ያልተመሠረተ ዘገባ ማስተላለፍ የተፈለገውን መልዕክት ብቻ ለማስተላለፍ ታልሞ የቀረበ ሪፖርት ነው የሚል ግምት እንዲኖር ያደርጋል።

በተመሳሳይ ኢሳት ብዛት ያላቸው የአካባቢውን ነዋሪዎች አነጋግሮ ዘገባውን የሠራ ሲሆን፣ ነዋሪዎቹ ስለ ጥቃት አድራሾቹ ማንነት ሲጠየቁ የሚሰጡት ሐሳብ ደግሞ ከላይ ከተጠቀሰው ዘገባ ጋር የሚቃረን ነው። ኢቢሲ ደግሞ በዋነኝነት የመንግሥት አመራሮች በሚሰጡት መረጃ ላይ በመደገፍ ነው ዘገባውን የሚያዘጋጀው በዚህም “ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት ሳይሆን የቀጠናውን መረጋጋት በማይፈልጉ ኃይሎች የተፈፀመ ወንጀል ነው’’ ሲል ያለነዋሪዎች ድምፅ ዘገባውን ሠርቷል። አማራ ቲቪም “የትግርኛ ተናጋሪዎች ያሉበት በፀረ ሰላም ኃይሎች የሚደገፍ የኦነግ ሸኔና ጎሕዴድ ጥምረት ነው ይህን ያደረገው” ሲሉ ወቅሰዋል።

ይህ የተራራቀ የሚዲዎች የዜና አዘጋገብ ሚዲያዎች ባላቸው ፖለቲካዊ አቋም የተነሳ በየትኛውም ሁኔታ ሊያንፀባርቁት የሚፈልጉት ሐሳብና ጣት ሊጠቁሙበት የሚፈልጉት አካል/ወገን መኖሩንና  ሁሉም ኃላፊነቱን ከራሱ ላይ በማንሳት ጠላቴ ነው የሚለው አካልን መውቀስ ላይ ያተኮረ እንደሆነ ያሳያል። ኦቢኤን እና ኦኤምኤን በዚህ ዙሪያ የሠሩትን ዘገባ ለጊዜው ማካተት ባንችልም የመንግሥት ሚዲያው ኢቲቪ፣ ትግራይ ቲቪ እና አማራ ቲቪ ይህንን ተቃርኖ በደንብ ሊያሳዩ የሚችሉ ምሳሌዎች ናቸው።

ሌሎች ዘገባ የሠሩ ሚዲያዎች በተለይም እንደነቢቢሲ አማርኛ ያሉት የመረጃ እጥረት ቢኖርባቸውም በተቻለ መጠን ሰፋ ያለ መረጃን ለማካተት ሙከራ አድርገዋል።  በተለይም የአውሎ ሚዲያ ጋዜጠኛ በተደጋጋሚ የሚመለከታቸውን አካላት ለማነጋገር ጥረት ቢያደርግም ምላሽ ባለመስጠት ስልክን እስከመዝጋት የሚደርስ ችግር አጋጥሞት እንደነበር ከቪዲዮው መመልከት ይቻላል፣ ዶቼ ቨለና ቪኦኤ ተመሳሳይ ችግር ስላጋጠማቸው ዝርዝር መረጃ ማቅረብ እንዳልቻሉ ገልጸው ነበር።

ይህ ብዙኃን መገናኛዎች በቂ መረጃ እንዳያስተላልፉ እንቅፋት የሆነባቸው የመረጃ መስጠት አለመፍቀድ ልማድ በማኅበራዊ ሚዲያው ተጠቃሚ ዘንድም ግርታና ጥርጣሬ እንዲፈጠር አድርጓል። ሰለዚህም ሁሉም በማኅበራዊ ሚዲያ አካውንቱ በየራሳቸው ትክክል የመሰላቸውንና እንዲተላለፍላቸው የሚፈልጉትን መልዕክት እንዲያስተላልፍ በር ከፋች ሆኗል። ጩኸቴ ታፍኖብኛል የሚሉ ወገኖችም የሟቾችን ሥምና ዕድሜም በመጥቀስ ዝርዝር እስከማቅረብ ደርሰው እንደነበር ተመልክተናል። ይህም ሁሉም በየራሳቸው በደላቸው እንዲሰማላቸው በተለያየ መንገድ እየታገሉ መሆኑን ያሳያል። ከላይ እንደተመለከተው በማኅበራዊ ሚዲያው ተጠቃሚዎች ዘንድ የጥቃቱ ዋነኛ ተጠያቂ ይሄ አካል ነው፣ ለዚህ ነው ይህንን ያደረገው የሚሉ የተለያዩ መላምቶች እና በማስረጃ ያልተደገፉ ድምዳሜዎች ሲንፀባረቁ አይተናል። የሐሳብና የአቋም ልዩነት መኖሩ ጤነኛ ቢሆንም እንዲህ ዓይነት እጅግ ፅንፍ የያዙ አቋምና መረጃዎች እንዲንሸራሸሩ ምክንያት የሆነው በዋነኝነት እንድተገለፀው የመረጃ እጥረትና ፅንፍ ረገጥ እና በማንነት የተከፋፈለው የፖለቲካ ባሕል በኅብረተሰቡ መካከል የፈጠረው አለመተማመን እንደ አንድ ምክንያት ሊወሰድ ይችላል።

ግጭት ቀስቃሽ መረጃዎች ከዜና ዘገባዎች ይልቅ በማኅበራዊ ሚዲያው ሰፊውን ቦታ ይዘው ታይተዋል። ይሁን እንጂ መደበኛ ሚዲያዎችም ከወገኝተኝነት የፀዳና እውነታን ብቻ የማቅረብ  የአዘጋገብ ስልትን ማስኬድ እስካልቻሉ ድረስ በሕዝቡ ዘንድ ጥርጣሬና ጥላቻን እንዲነግስ በማድረግ ሌላኛውን ሰፊ እጅ እንደያዙ ይቀጥላሉ። በዚህም ምክንያት ግጭቶቹን ለመረዳት እና ለመፍታት እንዳይቻል አስተዋፅዖ ሊያደርጉ ይችላሉ። ለማጠቃለል በዘገባዎች ላይ የታዩት ክፍተቶች፡- ወገንተኛ የዜና ዘጋቢዎች እና ብዙኃን መገናኛዎች መኖር፣ በማስረጃ ያልተደገፈ የጥፋተኞች ፍረጃ በመንግሥት ኃላፊዎችና ፖለቲከኞች ሳይቀር መኖሩ፣ ትክክለኛ መረጃ ፈልገው የሚያቀርቡ ብዙኃን አቅም እና ቁጥር ውሱን መሆኑ ዋና ዋናዎቹ ናቸው። በመደበኛ ብዙኃን መገናኛዎች መካከል ያለው ክፍተት የማኅበራዊ ሚዲያዎች የጥላቻና የተሳሳተ መረጃ ትክክል እና ተአማኒ መስሎ እንዲቀጥል አስተዋፅዖ እያደረገ እንደሆነ ተስተውሏል።

Center for Advancement of Rights and Democracy (CARD)

Making Democracy the Only Rule of Game!

Leave a Reply

Your email address will not be published.