የሰላም ሥምምነቱን እናበረታታለን፤ ለቁርጠኛ አፈፃፀሙም ጥሪ እናቀርባለን!   

ሥማችንን ከዚህ በታች ያኖርን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) መንግሥት እና ሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ጦርነቱን በዘላቂነት ለማቆምና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን በተሟላ መልኩ ለማስከበር መሥማማታቸውን ከልብ እናደንቃለን። ይህ ሥምምነት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ለሁለት ዓመታት በዘለቀው ጦርነት ለተጎዱ መላ ኢትዮጵያውያን ትልቅ ትርጉም እንዳለው እናምናለን።

ሁለቱም ወገኖች ልዩነታቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ቁርጠኛ ሆነው በዘላቂነት ግጭት የማቆም ሥምምነት መፈረማቸውን ከልብ እናደንቃለን። ይህም ቆራጥነትን የሚጠይቅ ተግባር እንደሆነ እንገነዘባለን። ካሁን ቀደም ደጋግመን እንዳልነውም ሰላም ብቸኛው አማራጭ ሲሆን፣ ዴሞክራሲ ደግሞ ለፖለቲካ ልዩነቶች ሁሉ መፍትሔ ነው።

ይህን ግጭት ለማስቆም የአፍሪካ ኅብረት እና ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ላሳዩት ቁርጠኝነትም አድናቆታችንን ለማቅረብ እንወዳለን። የኢፌዴሪ መንግሥትም ሰላምን ከማፅናት ባሻገር መልሶ የማገገሚያ ፍትሕ ሥራዎችን እንዲሠራ እናበረታታለን።

የኢፌዴሪ መንግሥትና ሕወሓት ቃላቸውን አክብረው ሥምምነቱን ተግባራዊ እንዲያደርጉም ጥሪ እናቀርባለን። የአፍሪካ ኅብረት እና ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ለሰላም ሥምምነቱ ተግባራዊነት እንዲሁም ለቀጣይ የመልሶ ማቋቋም እና መልሶ ግንባታ ሥራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን። እኛም እንደ ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በሥምምነቱ አተገባበርም ሆነ በመልሶ ግንባታው የሚጠበቅብንን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆናችንን በድጋሚ እንገልጻለን።

ይህንን መግለጫ በጋራ ያወጣነው ሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣

 1. የመብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ)
 2. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ህብረት (ኢሰመድህ)
 3. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል (EHRDC)
 4. የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር (EWLA)
 5. ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ (AHRE)
 6. የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት (NEWA)
 7. የኢትዮጵያ ሴቶች እና ሕፃናት ማኅበራት ኅብረት (UEWCA)
 8. ሴታዊት ንቅናቄ
 9. የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብቶች
 10. ኢትዮጵያን ውመን ራይትስ አድቮኬትስ (EWRA)
 11. ኢንተር አፍሪካ ግሩፕ
 12. ኢንክሉሲቭ ቪዥን ፎር ዴሞክራቲክ ኢትዮጵያ
 13. የሴቶች ህብረት ለሰላምና ለማህበራዊ ፍትህ
 14. ትምራን
 15. ኤምፓቲ ፎር ላይፍ ኢንቲግሬትድ ዲቬሎፕመንት አሶሴሽን

Center for Advancement of Rights and Democracy (CARD)

Making Democracy the Only Rule of Game!

Leave a Reply

Your email address will not be published.