የሸዋ ሮቢቱ ስቃይ

(ሰይፉ ግርማ ተርኮት አጥናፉ ብርሃኔ እንዳቀነባበረው)

ሰይፈ ግርማ እባላለሁ፤ የግንቦት ሰባት አመራር አባል ከሆነው ወንድሜ ጋር ግንኙነት አለህ፣ አባላትን ለድርጅቱ ትመለምላለህ ተብዬ በ2007 በእነመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ የክስ መዝገብ በሽብር ወንጀል ተከስሼ፣ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት እቀርብ ነበር፡፡

በነሐሴ 26፤2008 በማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች ከቤተሰብ ለታራሚ የሚገባ ምግብ መከልከሉን ተከትሎ ታራሚዎች ተቃውሞ ማቅረብ ጀመሩ፤ ይሁንና ይሀን ተቃውሞ ከምንም ያልቆጠሩት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ኃላፊዎች በእስር ቤቱ ውስጥ የአተት ወረርሽኝ ስለተነሳ ከነሐሴ 28፤2008 ጀምሮ ከቤተሰብ ምንም ዓይነት ምግብ እንደማይገባ በማረሚያ ቤቱ በሚገኙ ዞኖች ውስጥ ማስታወቂያ ለጠፉ። ወትሮውንም በማረሚያ ቤቱ የሚቀርበው ምግብ ጥራቱ በጣም የተጓደለ በመሆኑ ክልከላው እስረኛውን አስቆጥቶ ወደ ረሀብ አድማ ተሻገረ።

እስረኞች ከማረሚያ ቤቱ የሚቀርብላቸውን ምግብ አልመገብም በማለት ተቃውሞ ማስማት ቀጠሉ። የእስር ቤቱ ኃላፊዎችም ተቃውሞው እየበረታ ሲመጣ እኔ የምገኝበትን ዞን 2 ጨምሮ ወደ ቤተሰብ መገናኛ የሚወስዱ ኮሪደሮችን በሰንሰለት ዘጉ። ቅዳሜ ማለዳ ነሐሴ 28፣ 2008 ጩኸትና ፉጨት ከየዞኖቹ መሰማት ቀጠለ፤ የተቆጡ እስረኞች ዩኒፎርማቸውን ሜዳ ላይ አውጥተው ማቃጠል ጀመሩ፤ በዚህ ጊዜ የእስር ቤቱ ጠባቂዎች መሣሪያ በመያዝ ወደተዘጋው ኮሪደር ተጠጉ። እኔ ካለሁበት ዞን ካሉ ቤቶች ውስጥ ከ5ኛ ቤት እሳት ተነሳ፤ ቤቱ የተያያዘ ስለነበረ እሳቱ በኮርኒስ በኩል በመሔዱ ቤቶቹ ሙሉ ለሙሉ በጭስ ታፈኑ። ከእሳት ለማምለጥ ወደ ሜዳ የወጡት እስረኞች ከማረሚያ ቤቱ ጠባዊዎች በተለቀቀ አስለቃሽ ጭስ ታፍነው መተያየት ባለመቻላቸው አንዱ በአንዱ ላይ እየተረማመደ ነፍሳቸውን ለማዳን ይፍጨረጨሩ ነበር።

ሰይፈ ግርማ በቂሊንጦ ቃጠሎ ሳቢያ ከፍተኛ ስቃይ ከደረሰባቸው ሰዎች አንዱ ነው፡፡

ከእሳቱና ከሚተኮስባቸው አስለቃሽ ጭስ ለማምለጥ በሰንሰለት ወደቆለፈው የኮሪደው መውጫ ስንሔድ በሩ ጋር ቆመው በሚጠባበቁ መሣሪያ በታጠቁ ወታደሮች ጥይት ይተኮስብን ነበር። ከእሳቱና ከሚያፍነው ጭስ ወደ ቤተሰብ መጠየቂያ የሮጡ ብዙ እስረኞች ቆጥ ላይ ሆነው በሚጠብቁ የእስር ቤቱ ወታደሮች ተገደሉ። ጋዲሳ የተባለ እስረኛ በጥይት ተመቶ ወድቆ ነበር፤ እስረኛው እንደምንም ብሎ የተመታውን የሰውነት ክፍል በጨርቅ ጠቅልሎለት የነበረ ቢሆንም ዓይናችን እያየ ሕይወቱ አለፈ።

 

ጉዞ ወደሸዋ ሮቢት

ሕይወታችንን ለማትረፍ ሁሉንም ዞኖች ጠቅልሎ ወደያዘው ዋናው ግቢ ሮጥን፤ ፖሊስ ክብ ሠርቶ ይጠብቀን ስለነበረ እዛው ሜዳ ላይ እንድንቀመጥ አረጉን። ልብሳችንን እና ጫማዎቻችንን እንድናወልቅ አድርገው እስከምሽት ድረስ ዝናብ እየዘነበብን አስቆዩን። ምንም ምግብ ሳንመገብ፣ ልብስና ጫማ ሳናደርግ ከምሽቱ ሦስት ሰዐት ላይ ወደ ሸዋ ሮቢት ጭነው ወሰዱን።

ሸዋ ሮቢት እንደደረስን በባዶ እግራችን ፒስታ መንገድ ላይ እያሯሯጡ ይደበድቡን ነበር። ሸዋ ሮቢት በነበርንበት ወቅት እጃችንን ሳንታጠብ ነበር የምንበላው፤ ጫማ ስለሌለን በባዶ እግራችን ነበር የምንንቀሳቀሰው። በዛ ሁኔታ ለ17 ቀን ከታሰርን በኋላ እስር ቤቱን ረብሸዋል የተባሉ እስርኞች እዛው ሲቀሩ እኔን ጨምሮ 600 እስረኞች ወደቂሊንጦ እንድንመለስ ተደረግን።

 

የአንድ ቀኑ ሰቆቃ

ቂሊንጦ ከተመለስን በኋላ ብዙ ጭቆናዎች ደርሰውብን ነበር። ለቀናቶች ቤት ተቆልፎብን ነበር የምንውለው፤ ግቢ ውስጥ እንዲንቀሳቀሱና ንፁህ አየር እንዲያገኙ የሚፈቀድላቸው ከእስር ቤቱ ዞኖች አስተዳዳሪዎች ጋር አንድ ዓይነት ብሄር ያላቸው እስረኞች ነበሩ።

ለ19 ቀናት በዛ ሁኔታ ከቆየሁ በኋላ እቃህን ሰብስበህ ውጣ ተብዬ ድጋሚ ወደ ሸዋ ሮቢት ተጫንኩ። ሸዋ ሮቢት ምሽት ላይ ነበር የገባሁት፤ ጩኸት ይሰማኝ ስለነበር የአእምሮ በሽተኛ ያለ ነበር የመሰለኝ። ከፍተኛ ፍተሻ ከተደረገብኝ በኋላ ከአልጋ ጋር አስረውኝ አደርኩ።

ጠዋት ሲነጋ ዳቦ በሻይ ሰጥተውኝ እየበላሁ እያለ ፖሊስ ጠርቶኝ ወደ አንድ ወደተዘጋ በር ይዘውኝ ሔዱ፤ ክፍል ውስጥ ከገባሁ በኋላ ስሜንና የከዚህ በፊት የተከሰስኩት በምን እንደሆነ ጠየቁኝ፤ በክፍሉ ውስጥ 5 መርማሪዎች ነበሩ፤ አንደኛው መርማሪ “መከበር የምትፈልግ ከሆነ የምንጠይቅህን ምንም ሳትደብቅ ንገረኝ” አለኝ እኔም የማቀውን እንደማልዋሽ ነገርኳቸው።

መርማሪዎቹ ጥያቄያቸውን የጀመሩት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት እሳት እንዴት እንደተነሳ አንድነግራቸው በመጠየቅ ነበር። ከቤተሰብ የሚመጣ ምግብ መከልከሉ ጋር ተያይዞ ረብሻ እንደተነሳና ቃጠሎው እንደቀጠለ ነገርኳቸው። ይህ መልሴ ያልተዋጠላቸው መርማሪዎቹ ክብር እንደማይወድልኝ ነግረውኝ ከዚህ በፊት የተመረመሩ ታራሚዎች እውነቱን እንደተናገሩ እና ረብሻው ላይ ያለኝን አስተዋፅዖ የማልናገር ከሆን ወደ ኃይል እርምጃ እንደሚገቡ ገለጹልኝ። ረብሻው ላይ የኔ አስተዋፅዖ እንዳልነበረበትና የርሃብ አድማውንም እንዳልደገፍኩ ነገርኳቸው፤ በመልሴ ደስተኛ ስላልነበሩ ለአራት እየተፈራረቁ ይደበድቡኝ ጀመር፤ ከዱላው ባሻገር የተለያዩ ማሰቃያ ተግባራትን መፈፀማቸውን ቀጠሉ። አውራ ጣቴን በሲባጎ ሸምቅቀው በማሰር በእጄ ላይ ያለ ካቴና በገመድ ወደላይ ወጥረው በማሰር አሰቃዩኝ። ይህ አልበቃ ስላላቸው “አንተ በዚህ ልትናገር አትችልም” በማለት እጅና እግሬን በማሰር፤ ወፍራም ዱላ በመሐል በማስገባት አንጠልጥለው ሰቅለው ውስጥ እግሬል ገረፉኝ፤ ስቀዩን ልቋቋመው ያልቻልኩት ነበር። በካቴና አስረው ያንጠለጠሉኝ ጊዜ የእጄ ቆዳ ተልጦ ተላቆ ነበር። ሚስማር ባለው ዱላ ይመቱኝ ስለነበር ሚስማሩ ወደ እግሬ እየገባ ከፍተኛ የሕመም ስቃይ ረጅም ጊዜ ድረስ ይሰማኝ ነበር።

በዚህ ሁኔታ ለግማሽ ቀን ካለማቋረጥ ከደበደቡኝ በኋላ እዛው አንጠልጥለውኝ ምሳ ለመብላት ሔዱ። መርማሪዎቹ ምሳ በልተው ሲመለሱ ስቃዩ ስለበዛብኝ እነሱ ባሉኝ እንደምስማማ ነገርኳቸው። እንዳምን የፈለጉት ከእስር ቤት ለማምለጥ ብዬ የእስረኞች ቡድን እንደመራሁ፤ እስር ቤቱ እንዲሰበር ፕሮግራም ይዤ ስንቀሳቀስ እንደነበር፤ ከዶክተር ፍቅሩ ማሩ ገንዘብ በመቀበል እስር ቤት ውስጥ አመፅ እንዲነሳ እንዳደረኩ ካሜራ ፊት እንድናገር ዛቻው እና የደረሰብኝ ድብደባ ያልፈፀምኩትን ወንጀል እነደፈፀምኩ አድርጌ እንድናገር አስገደደኝ። አቅም ስላነሰኝ በሚሉት ተስማምሁ፤ ወደ ኃላፊው ቢሮ ወስደውኝ ካሜራ ፊቴ እመን ያሉኝን አመንኩ።

 

“ለ23 ሰው ሞት ተጠያቂ መሆን”

መርማሪዎቹ በግማሽ ቀን ውስጥ ሕይወቴን ለዘላለሙ ሊቀይር የሚችል በዓለም ላይ ያለ ከባድ ወንጀል አሸከሙኝ። ሸዋ ሮቢት እስከነበርኩበት ሕዳር 11፣ 2008 ድረስ እጄን ታጥቤ መመገብ አልቻልኩም ነበር፡፡ ሽንት ቤት የምንጠቀምበት ወረቀትም ሆነ ሶፍት አልነበረም፤ በካቴና ጥንድ ጥንድ ታስረኘን ነበር ሽንት ቤት የምንጠቀመው።

ኅዳር 23፣ 2008 እኔን ጨምሮ 38 ተከሳሾች ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው የክስ ወረቀታችንን ተቀበልን። ክሱን ያነበብኩት ከፍርድ ቤት ወደ ቂሊንጦ እየተመለስን ነበር፤ ለ23 ሰው በእሳት ተቃጥሎ መሞት እና ለ15 ሚሊዮን ብር የንብረት ውድመት ተጠያቂ እንደሆንኩኝ ክሱ ያስረዳል። በማስረጃነት ከተያያዙት ሰነዶች ውስጥ አብረውኝ ታስረው የነበሩት እና በእስርቤቱ በተነሳው እሳት ተቃጥለው የሞቱ ሰዎችን ፎቶ ነበር፤ በጣም ነበር ያዘንኩት፡፡ ክሱን እያዩ የሚያለቅሱ እስረኞቹ ነበሩ፤ ሁሉ ነገር ያበቃ መስሎ ተሰማኝ፡፡

(ሰይፈ ግርማ በአሁን ሰአት የተከሰሰበት ክስ በአቃቤ ሕግ ውድቅ ተደርጎ ከቤተሰቦቹ ጋር ከተቀላቀለ ወራቶች ተቆጥረዋል።)

Leave a Reply

Your email address will not be published.