የቂሊንጦ ማ/ቤት አስተዳደር አቶ ዮናታን ተስፋዬን በቀጠሯቸው መሰረት ፍ/ቤት አላቀረበም

በማህበራዊ ሚዲያ በተለይም ፌስቡክ ላይ በጻፋቸው ጹሁፎች ምክንያት የሽብር ክስ ቀርቦበት ጉዳዩ በፍ/ቤት እየታየ የሚገኘው የቀድሞው የሰማያዊ ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ በእስር የሚገኝበት የቂሊንጦ ማረሚያ ቤት አስተዳደር በቀጠሮው መሰረት ፍ/ቤት ሳያቀርበው ቀርቷል፡፡

አቶ ዮናታን ተስፋዬ ባለፈው አመት ሐምሌ 28/2008 ዓ.ም የፌደራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት የቀረበበትን ክስ እንዲከላከል መወሰኑ የሚታወቅ ሲሆን፣ በዚህ መሰረት አቶ ዮናታን ዛሬ ጥቅምት 14/2009 ዓ.ም መከላከያ ምስክር ለማሰማት ቀጠሮ ተይዞለት ነበር፡፡

ከፍተኛ ፍ/ቤት 4ኛ ወንጀል ችሎት ዳኞች በላይሁን አወል፣ ያዕቆብ መኩሪያ፣ ግርማ ደባሱ የአቶ ዮናታንን ጉዳይ በቢሮ የተመለከቱ ሲሆን፣ ዳኞቹ አቶ ዮናታን አለመቅረባቸውን በመመልከት የቂሊንጦ ማ/ቤት ተወካይ ም/ሰርጀንት ዘውዱ ወ/ማርያምን ተከሳሹን ለምን እንዳላቀረቡ እንዲያስረዱ ጠይቀዋል፡፡ ም/ሰርጀንት ዘውዱ፣ ‹‹ማ/ቤቱ ላይ በደረሰው አደጋ ምክንያት እስረኞች ወደተለያዩ ማ/ቤቶች ስለተበታተኑ እየቀረቡ አይደለም›› ብለዋል፡፡

በጽሁፍ የተዘጋጀ መልስ አላችሁ ወይ ተብለው የተጠየቁት የማ/ቤቱ ተወካይ፣ ‹‹የተጻፈ ምክንያት አላመጣንም፡፡ እስከዛሬ እንዲሁ ነበር የምናስረዳው›› በማለት ምላሽ ሰጥተው፣ ‹‹ቀጠሮ ለመቀበል ነው የመጣሁት›› ብለዋል፡፡ ተከሳሹ የት ማ/ቤት እንዳለ ያውቁ እንደሆን የተጠየቁት ተወካዩ፣ አቶ ዮናታን ቂሊንጦ ስለመኖር አለመኖራቸው አላውቅም ብለዋል፡፡

ሆኖም የተከሳሽ ጠበቃ ደንበኛቸው ቂሊንጦ እንደሚገኝና በቤተሰብም ስንቅ እንደሚደርስለት አረጋግጠው፣ ነገር ግን በደፈናው ‹ጠበቃ አናገናኝም› የሚል ምላሽ እየተሰጣቸው ደንበኛቸውን ለማነጋገር እንደተከለከሉ ለፍ/ቤቱ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡

ፍ/ቤቱም የቂሊንጦ ማ/ቤት አስተዳደር ተከሳሹን በቀጣይ ቀጠሮ ዛሬ ለምን እንዳላቀረበው ከሚያስረዳ በቂ የጽሁፍ መልስ ጋር ተከሳሹን ይዞ እንዲቀርብ፣ ከጠበቃ ጋር የመገናኘት መብቱን አክብሮ ከጠበቃው ጋር እንዲነጋገር እንዲፈቀድለት ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በዚህም የተከሳሽ መከላከያ ማስረጃዎችን ለማድመጥ ለህዳር 19/2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

አቶ ዮናታን ተስፋዬ የጸረ ሽብር አዋጁን አንቀጽ 4 በመተላለፍ ተከሶ የነበር ቢሆንም ተከላከል የተባለው ግን አንቀጽ ተለውጦ በአዋጁ አንቀጽ 6 የተመለከተውን ‹ሽብርተኝነትን ማበረታታት› የሚለውን እንደሆነ ይታወቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *