የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ፕሮጀክት (ኢሰመፕ) ባለፈው አመት ታውጆ ለአስር ወር የቆየው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መንስኤ እና ውጤት ላይ ያካሄደው ጥናት፡፡

ኢትዮጵያ በ2009 ለዐሥር ወራት በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ውስጥ ከርማለች፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ፕሮጀክት (ኢሰመፕ) የተዘጋጀ ጥናት ዐዋጁን ከመዳሰሱም ባሻገር፣ በአገሪቱ የሰብኣዊ እና ፖለቲካዊ መብቶች አያያዝ ላይ ያሳደረውን ተፅዕኖ ይዳስሳል፡፡ ጥናቱን ለማካሔድ ለዓላማው በሚመች መልኩ ከተመረጡ (purposive sampling) ሰዎች ጋር ቃለ ምልልሶች ተደርገዋል፤ የመስክ ቅኝቶች እና የሰነድ ትንተናዎችም ተከናውነዋል፡፡ አቀራረቡም ገለጻዊ ዘዴን የተከተለ ነው፡፡

በጥናቱ እንደተዳሰሰው፣ ለዐዋጁ መጣል ዋናው ምክንያት ከ2008 ጀምሮ ሲካሔድ የነበረውን ሕዝባዊ ተቃውሞ መቆጣጠር ነው፡፡ ተቃውሞው ዋና ዋናዎቹን ክልሎች – ማለትም ኦሮሚያ፣ አማራ እና አንዳንድ የደቡብ ክልል አካባቢዎችን ያዳረሰ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ በመስከረም ወር 2009 በቢሾፍቱ ከተማ የተከበረው የኢሬቻ በዓል ላይ የተነሳውን ተቃውሞ ለመበተን የፀጥታ ኃይሎች ጣልቃ በመግባታቸው እና የብዙ ሰው እልቂት በማስከተሉ፣ ተቃውሞው በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተፋፍሞ መቀጠሉ ለዐዋጁ መጣል ቅፅበታዊ መነሾ ሆኗል፡፡

ዐዋጁን መጣል ሳያስፈልግ በተቃውሞው ወቅት ተፈፀሙ የተባሉትን ችግሮች በመደበኛ ሕግጋት መቆጣጠር ይቻል የነበረ ቢሆንም፣ መንግሥት ዐዋጁን በመጣል ሕጋዊ ተቃውሞዎችን ለማፈን እና ለማዳከም ተጠቅሞበታል፡፡ የዐዋጁ ድንጋጌዎች ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው የዓለማቀፍ ድንጋጌዎች ጋር የሚጋጭባቸው አንቀፆችን ያካተተ ነበር፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ድንጋጌ እንዲሁም የኮማንድ ፖስቱ የዐዋጁ አፈፃፀም መመሪያ የሚከለክላቸው ተግባራት እና የፀጥታ ኃይሉ የተሰጠው የተለጠጠ ሥልጣን፣ ከአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ በፊት እና በኋላም እንደነበር ጥናቱ አረጋግጧል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁን መጣል ያስፈለገው በአንድ በኩል ከዐዋጁ ውጪ ያለሕግ አግባብ የተወሰዱትን እርምጃዎች በሕግ አግባብ ለመሸፈን እና የፀጥታ ኃይሉን ከተጠያቂነት ለማውጣት ሲሆን፣ በሌላ በኩል የዘፈቀደ ግድያ እና የጅምላ እስር እንዲሁም የመረጃ እና ግንኙነት መረቦችን ማቆራረጥ ያላስቆመውን ሕዝባዊ ተቃውሞ በፍርሐት ለማፈን እንደሆነ የጥናቱ ውጤት ያስረዳል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ትልቁ ክስተት የጅምላ እስር ሲሆን፣ የእስር ዘመቻው ተቃውሞ የነበረባቸውንም ያልነበረባቸውንም አካባቢዎች አዳርሷል፡፡ እስረኞቹ ክስ ሳይመሰረትባቸው፣ በቂ ምግብና የመጠጥ ውኃ እንዲሁም የመፀዳጃ ሥፍራ በሌለበት ማቆያ በጅምላ እንዲቆዩ ተደርገዋል፡፡ ብዙ እስረኞች በግዳጅ ምርመራ ወቅት ዘላቂ እና ጊዜያዊ የሥነ ልቦና እንዲሁም የአካላዊ ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ ከተፈቱ በኋላም ለኢኮኖሚያዊ ቀውስ እና በፍርሐት ውስጥ ለመኖር ተገደዋል፡፡ አብዛኞቹ እስረኞች መንግሥት ‹ተሐድሶ› ያለውን ሥልጠና እንዲወስዱ የተገደዱ ሲሆን፣ ጥቂቶች ‹በምክር› መታወቂያቸውን ብቻ ዋስ አስይዘው ሲለቀቁ፣ ቀሪዎቹ ክስ ተመሥርቶባቸው፣ ከፊሎቹ በነጻ ሲሰናበቱ ቀሪዎቹ የወራት እስር ፍርድ ተቀብለዋል፡፡ በዐዋጁ ወቅት ለደረሱ የሰብኣዊ መብቶች ጥሰቶች ‹አጣሪ ቦርድ› በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቢሰየምም ያጋለጠው የሰብኣዊ መብቶች ጥሰትም ሆነ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ያደረገው ሙከራ የለም፡፡ የዘፈቀደ ግድያን በተመለከተም እንዲሁ ከዐዋጁ በፊት፣ በዐዋጁ ወቅት እና ከዐዋጁ በኋላም የተከሰተ ቢሆንም የፀጥታ ኃይሉ ላይ ምንም ዓይነት ተጠያቂነት አላስከተለም፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ ለሚዲያ፣ ለማኅበራት እና የተቃውሞ ድርጅቶች ሥራ እንቅፋት ሆኗል፡፡ የብዙኃን መገናኛ እና የሲቪል ማኅበራት መደበኛ ተግባራት በዐዋጁ ሳቢያ ተደናቅፈዋል፡፡የሰብአዊ መብት አክቲቪስቶችም በትንሽም ቢሆን የሚንቀሳቀሱበት የነበረው የኢንተርኔት ምህዳርም በተደጋጋሚ ከመታፈኑ በተጨማሪ አዋጁ በፈጠረው ፍርሃት የተነሳ ከአገር ውስጥ የሚደረጉ የመብት ጥሰት ሪፓርቶች እና ፓለቲካዊ ውይይቶችም ተገድበዋል፡፡

በጥቅሉ፣ የ2009ኙ የኢትዮጵያ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ሠላምና ማረጋጋትን የማምጣት ሳይሆን ተቃውሞዎችን የማፈን ዓላማ እንደነበረው ጥናቱ ይደመድማል፡፡ ይህም የተደረገው በሰብኣዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት እና በፀጥታ ኃይሉ የተለጠጠ ወይም ሕጋዊ ተጠያቂነት በማያስከትል የፀጥታ ኃይሎች ሥልጣን ሽፋን ነው፡፡
የጥናቱ ዝርዝር ሪፓርት ከስር የሚገኘው መስፈንጠሪያ ላይ ይገኛል
በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ላይ የኢሰመፕ ጥናት ፒዲኤፍ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *