የእነ ጉርሜሳ አያኖ መዝገብ በተያዘው ቀጠሮ ምስክሮች ሰይደመጡ ቀሩ። (ጥቅምት 28 ፣2010)

* ችሎቱ ምስክሮች በተከሳሾች እና ዳኞች አለመግባባት ተቋርጧል።
የእነ ጉርሜሳ አያኖን መዝገብ ለዛሬ ጥቅምት 28 ፣ 2010 የተቀጠረው ከአንደኛ እሰከ አራተኛ ካሉት ተከሳሾች ውጪ ያሉ ተከሳሾችን መከላከያ ምስክሮች ለመስማት በሚል ነው። በጠዋቱ ችሎት ዳኞች ሌሎች መዝገቦችን ሲሰሩ ስለነበር ቀጠሮው ወደ ከሰአት ዞሯል። ተከሳሾቹ የሚመገቡትን ምሳ በተመለከተ ጠበቃ አቶ ወንድሙ ኢብሳ ዳኞቹን ለማረሚያ ቤት ሃላፊዎች ትእዛዝ እንዲያስተላልፉ ያስታወሷቸው ሲሆን የመሃል ዳኛዋ በትላንትናው ችሎት በተወሰነው መሰረት ከቤተሰብ የሚቀርብላቸውን ምግብ በጥንቃቄ እንዲመገቡ እንዲያደርጉ ለማረሚያ ቤቱ ሃላፊዎች ተናግረዋል።

በከሰአቱ ችሎት ተከሳሾችን በስም ጠርተው መቅረብ አለመቅረባቸውን በሚያረጋጥበት ወቅት 11ኛ ተከሳሽ አቶ በየነ ሩዶ ዛሬም አለመቅረባቸው ታውቋል። በመቀጠል ምስክር መስማት ሂደት እንደሚጀምሩ ዳኛው ሲናገሩ ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ደጀኔ ጣፋ አስተያየት እንዳላቸው ተናግረው የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል።

” በመጀመሪያ ከቂሊንጦ ስላልመጣው በየነ ሩዶ ነው አስተያየቴ። አንድ መዝገብ ላይ በጋራ ነው የተከሰስነው። ከዛሬ ጋር ሲቀር ለ3ኛ ጊዜ ነው። ቤተሰቦቹም እዚ መጥተው ሲንገላቱ ነው የዋሉት። ለምን ማረሚያ ቤቱ አላቀረበውም? ሌላው ትላንት መዝገቡን እያየን ወደፊትም ወደኃላም እንሰራለን ብላችሁናል። ስለዚህ ትላንት የወሰናችሁትን ውሳኔ ስለሚጎዳን ነገ ባለን ቀጠሮ ለቆጠርናቸው ምስክሮች መጥሪያ እንዲወጣ በድጋሚ እንዲታዘዝልን ነው የምንጠይቀው። አቃቤ ህግ ምስክር ሲያቀርብ አሰተያየት ማቅረብ ካለበት ተከሳሽ ነው። ተከሳሽ ሲያቀርብ ደግሞ አቃቤ ህግ አስተያየት ያቀርባል። ከዚህ ማስረጃ አሰማም ውጪ የአሰራር ህግ የለንም። የፌደራል አቃቤ ህግም አልተቃወመንም። በወቅቱ ችሎቱን የመሩ ዳኞች ምስክሮቹ እንዲቀርቡ ብለው ትእዛዝ ሰጥተዋል። ምስክሮቹ ይቅረቡ አይቅረቡ የሚለው ሃሳብ የፍርድ ቤቱን ኮንፊዴንሻሊቲ እና ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው። እንደ ቅድመ ሁኔታ አስቀምጦ ይሄ ማስረጃ ይመጣል ይሄ አይመጣም የሚል ህግ የለም እኔ እስከማቀው። የፍርድ ቤትን ነፃነት ጥያቄ ውስጥ ያስገባል። ለናንተም ጥሩ አይደለም። አገርም ያስወቅሳል። ስለዚህ ተነጋገሩና ውሳኔ ስጡን። ህዳር 6 የምትሉትን ተውና ነገ በተያዘው ቀጠሮ መጥሪያው እንዲወጣ ይታዘዘው ይፈፀምልን። ምሰክሮቹ ሃገር አስተዳዳሪዎች እንደመሆናቸው ከተከሰስንበት ጉዳይ ጋርም በተያያዘ የሚያውቁትን የሚያስረዱ የኤክስፐርት ምስክሮቻችን ናቸው። ለምን ትእዛዙ እንዳልወጣም ይነገረን። እኛ ኢትዮጵያዊ ነን። አትጉዱን። እኔ ለግሌ ብዬ አይደለም የታሰርኩት። ታሪክም ህዝብም ያቀኛል። ለሃገሬ ለህዝቤ ብዬ ነው እዚህ የመጣሁት። እንደ ግለሰብ ብኖር የመንግስት ስራም የግል ስራም እየሰራሁ ከማንም በላይ መኖር አያቅተኝም። ያንድ ቤተሰብ ያንድ ዘር እንዲህ ሲሰቃይ ሊሰማችሁ ይገባል።”

አራተኛ ተከሳሽ በቀለ ገርባ በበኩላቸው የሰጡት አስተያየት ይህን ይመስላል።

“መብታችን ተረግጧል ባዮች ነን። መከላከያ ምስክሮች አሉን ብለን ጠራን። የፍርድቤት ስራ መጥራት ነው። በየትኛውም መዝገብ የምስክሮች ሁኔታ ቀድሞ ሚመረመርበት አግባብ አይተን አናቅም። በፍርድ ቤት ሂደት ያለፍን ሰዎች ነን። ከታሰርን ሁለት አመታችን ነው። ከዛም በፊት እስር እና የተለያዩ እንግልቶች ደርሶብናል። መጥሪያ እንዲታዘዝ የተወሰነው ውሳኔ የማይፈፀም ከሆነ እናንተን ለመስማት ፈቃደኞች አይደለንም። መቀጠል አንፈልግም። እኔ በበኩሌ በዚህ ምክንያት የሚመጣብኝን ማንኛውም ቅጣት መቀበል እችላለው። ፍርድ ቤቱን ማዳመጥ አልፈልግም። እኔን የማያዳምጠኝ ከሆነ እኔ ለምን አዳምጣለው? ይሄ አይነት አሰራር አይተን አናውቅም። [ዳኞች «ጊዜያችሁን ለመቆጠብ የሌሎችን መከላከያ ምስክርነት እንስማ። የናንተን ጊዜ እንዳይባክን ነው» ካሉ በኃላ አቶ በቀለ አስተያየታቸውን ቀጥለዋል።] ለኛ ጊዜ ያሰባችሁ አትምሰሉ። እኛ የሚታዘንልን ሰዎች አይደለንም። ”
አንደኛ ተከሳሽ አቶ ጉርሜሳም “ከዚህ በፊት የተሰጠው ትእዛዝ ይከበርልን። በትእዛዙ መሰረት ሳይወጣ ከቀረ ድጋሚ ይታዘዝልን። ማስረጃችንን ከማቅረባችን በፊት አትመርምሩብን።”
ብለዋል።

Picture credit Addis Standard Magazine

ዳኞችም ከተወያዩ በኋላ ህዳር 6 የተያዘው ቀጠሮ እንደማይቀየር ጠቅሰው ጉዳዩን ሲመረምሩ ዛሬ ያቀረቡት በአስተያየታቸው የጠቀሷቸው ጉዳዮችን ጨምረው እንደሚያዩ ገልፀው ወደ ተቀሩት ተከሳሾች መከላከያ ምስክር መስማት ሂደት እንዲገባ ሃሳብ አቅርበዋል። ሆኖም ከአንደኛ እስከ አራተኛ ያሉ ተከሳሾች ትእዛዙ ማይፈፀምልን ከሆነ ችሎቱን ለመከታተል እንደማይፈልጉ ሲገልፁ የተቀሩት ተከሳሾችም መስማማታቸውን «ትእዛዙ ካልተከበረ አንቀጥልም» በማለት ጮክ ብለው ተናግረዋል። በመቀጠልም በማእከላዊ አቶ በቀለ ገርባ እንደደረሱት የሚነገረውን ከመሬት ወረራ ጋር በተያያዘ የሚያወራ የኦሮምኛ መዝሙር በችሎት መዘመር ጀመሩ። ዳኞች መዘመራቸውን እንዱያቆሙ ቢነግሯቸውም ተከሳሾቹ መዘመራቸውን ቀጥለዋል። ዳኞችም የችሎቱን ስራ አቋርጠው ወጥተዋል። ተከሳሾቹ ዘምረው ከጨረሱ በኋላ ነው ከችሎት የወጡት።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *