የዩኒቨርሲቲ ውስጥ ግጭቶች፦ መንስዔ እና ጉዳት (2012)

በተገባደደው 2012 የትምህርት ዓመት በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የተከሰቱ ግጭቶችን እና ያደረሱትን ጉዳት የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ካርድ) ሲከታተል ቆይቷል። በዚህም፦

  • 12 ተማሪዎች ለሞት መዳረጋቸውን፣
  • ከ58 ተማሪዎች በላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን፣ እና
  • 28 ዩኒቨርሲቲዎች ቀላል እና ከባድ ግጭቶች በማስተናገዳቸው የትምህርት ሒደቱ መስተጓጎሉን አስተውሏል።

የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል የሚከሰቱ ግጭቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀቡ መሔዳቸውን በመረዳት ካርድ የተለያዩ ቅድመ ዳሰሳዎችን እና ውይይቶችን ያስደረገ ሲሆን፣ (ዳሰሳ አንድዳሰሳ ሁለትውይይት) በውጤቱም የችግሮቹ ምንጮች ከትምህርት ስርዓቱ፣ ከአስተዳደር ሁኔታዎች እና ከአገሪቱ የፖለቲካ እውነታ ጋር የተያያዘ መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎችን አግኝቷል።

በዚህ የትምህርት ዓመት በጥቅምት 30፣ 2012 በወልዲያ በተከሰተ ግጭት የሁለት ተማሪዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን፣ ይህንን ተከትሎ በሕዳር ወር 16 ያህል ዩኒቨርሲቲዎች ግጭቶችን አስተናግደዋል። ግጭቶቹ የብሔር መልክ ያላቸው ሲሆን፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በሐሰተኛ መረጃዎች ግጭቶቹን የማቀጣጠል ሚና እንደተጫወቱም ተስተውሏል። ዓመቱ በግጭቶቹ ምክንያት ትምህርት የተስተጓጎለበትና የተማሪዎች ደኅንነት አደጋ ላይ የወደቀበት ሆኖ አልፏል።

ካርድ ባለው ውሱን አቅም ግጭቶቹን በመገናኛ ብዙኀን የተደረጉትን ዘገባዎች በመከታተል ለተጨማሪ ምርመራ እና የመከላከል ሥራ እንዲያግዝ በማለት የሚከተለውን ጥቅል ዓመታዊ መግለጫ በዩኒቨርሲቲዎች ግጭት ጉዳይ አዘጋጅቷል።

ካርድ ግጭት አገናዛቢ የወጣቶች ተዋስዖን በማበረታታት ረገድ ከዩኒቨርሲቲ ክበቦች እና ማኅበራት መሪዎች ጋር በጣምራ እየሠራ መሰንበቱ ይታወቃል። የካርድ ሥራዎች ግጭት አገናዛቢ ውይይቶችን በማድረግ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደሚቻል ሥልጠና በመስጠት ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ አምቦ ዩኒቨርሲቲ እና ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ሥልጡን የርስ በርስ ግንኙነቶችን የማዳበሪያ ክሕሎቶችን ሲገነባ ቆይቷል። ካርድ በመጪው የትምህርት ዓመትም ተመሳሳይ እገዛዎችን ማድረጉን ይቀጥላል።

Center for Advancement of Rights and Democracy (CARD)

Making Democracy the Only Rule of Game!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *