ዮናስ ጋሻው፤ “እስር ቤት ውስጥ አኮላሽተውኛል”

ጸሐፊ፡- በላይ ማናዬ

ዮናስ ጋሻው ደመቀ ይባላል፡፡ ዕድሜው 29 ዓመት ሲሆን፣ የሚኖረው ባህር ዳር ከተማ ነው፡፡ የአንድ ልጅ አባት ነው፡፡

ዮናስ ከ2008ቱ የክረምት ወራት ጀምሮ በአማራ ክልል ከተስተዋለው ሕዝባዊ ጥያቄ ጋር በተያያዘ በደኅንነት አካላት ከፍተኛ ክትትል ሲደረግበት እንደቆየ ይናገራል፡፡ በወቅቱ ይኖርበት የነበረው ባህር ዳር ከተማ ክትትሉ ሲበዛበት አድራሻ በመቀየር ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡ ነገር ግን በአጭር ጊዜ ውስጥ (ጥር 04/2009) በታክሲ ከሁለት እህቶቹ ጋር እየተጓዘ እያለ በአራት ፒክአፕ መኪና ሞልተው በመጡ ፌደራል ፖሊስ እና ሲቪል የለበሱ ደኅንነቶች በሕዝብ ፊት ከታክሲ አስወርደው አስፓልት ላይ እየደበደቡ ለእስር እንደዳረጉት በሐዘን ያስታውሳል፡፡ ዮናስ ከታሰረ በኋላ ከአንገቱ በላይ በጥቁር ልብስ ሸፍነው ወደማያውቀው ቦታ ወስደውታል፡፡ “ጫካ ውስጥ ከዛፍ ጋር አስረው ደብድበውኛል፡፡ በወቅቱ የጋብቻ ቀለበቴን እና የአንገት ሀብሌን ወስደውብኛል” ይላል፡፡ “‹ከዚህ በኋላ ልጅ ስለማትወልድ ትዳር ምን ይሰራልሃል?› እያሉ ንብረቴን ወስደውብኛል፡፡ ተሳልቀውብኛል፡፡ የግድያ ዛቻ ዝተውብኛል፡፡”

 

ዮናስ የማዕከላዊ ‹8 ቁጥር› ውስጥ

– ተገልሎ በጨለማ ውስጥ መታሰር

– አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ማሰቃየት

– ማንነትን መሠረት ያደረገ ዘለፋ

– ጠበቃ እና ቤተሰብ ጥየቃ ክልከላ

ዮናስ ጋሻው ወደ ፌደራል ወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) የተወሰደው በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ከዋለ ከሳምንት በኋላ ነበር፡፡ የማዕከላዊ መርማሪ መጀመሪያ እሱን ያገኘው ቀን እንደተፀየፈ ሰው እየተመለከተው “ይህን ጊዜ መስጠት አያስፈልግም፤ መግደል ነው” ይል እንደነበር ይናገራል፡፡ “ወስደው ለእሱ ያስረከቡኝ ሰዎችም፣ ‹ስንይዘው እህቶቹ አይተዋል፤ ብዙ ሰዎች አይተውናል› ብለው ሲነግሩት ተበሳጭቶ ነበር፡፡ ሊገድለኝ ነበር ፍለጎቱ፡፡ ሽጉጥ አውጥቶ ግንባሬ ላይ ደቅኖብኝ ነበር” በማለት በሕይወት መትረፉ ይገርመዋል፡፡

የ29 ዓመቱ ዮናስ ጋሻው በ2010 ከተፈቱ የፖለቲካ እስረኞች አንዱ ነው፡፡ ወደ እስር ቤት በጤና ገብቶ ከአካል ጉዳት ጋር ተፈትቷል፡፡ ከሁሉም በላይ በድብደባ መውለድ እንዳይችል ተደርጓል፡፡

ዮናስ ማዕከላዊ እንደገባ በቀጥታ ‹8 ቁጥር› የምትባል ጨለማ ክፍል ነው የታሰረው፡፡ ‹8 ቁጥር› በጣም ጠባብ፣ ጨለማ እና ቀዝቃዛ ክፍል ነው፡፡ መርማሪዎቹ ዮናስን ‹በ8 ቁጥር› ውስጥ ለስድስት ወራት አቆይተውታል፡፡ ለብዙ ቀናት እጅና እግሮቹ በሰንሰለት ታስረው ነበር ቀን እና ሌሊት የሚያሳልፈው፡፡ ምርመራው ሁሌም ሌሊት፣ ሌሊት እንደነበር የሚደረግበት ይናገራል፡፡ የማዕከላዊ ቆይታውን ሲያስታውስ፣ ዮናስ “መርማሪዎቹ ሰክረው መጥተው ነው የሚመረምሩኝ፡፡ ለምርመራ ወጥቼ ያል