“ድምፅ አልባ ጩኸት!” የታፈነው የመድፈር እና የሕገ ወጥ ጉዲፈቻ ታሪክ

በጌታቸው ወርቁ

ሦስት ጉስቁል ኢትዮጵያዊያን በዕድሜ የገፉ ሴቶች ቁጭ ብለው በምልክት ቋንቋ እያወሩ ለስላሳ ይጠጣሉ፡፡ ፊታቸው የተጎሳቆለ፣ አለባበሳቸውም እነደነገሩ ቢሆንም፣ ልብ የሚያሞቅ እውነተኛ ፈገግታ አላቸውና ተግባቦቴን ቀለል አድርገውልኛል፡፡ አንዲት ረዘም ያለች ግዙፍ ፈረንጅ (አሜሪካዊት) እና አቶ መላክነህ፣ ሦስቱን ሴቶች ያስተናብራሉ፡፡ በምልክት ቋንቋ ያወሯቸዋል፡፡

ሠላምታ ከተለዋወጥን በኋላ፣ ለአሜሪካዊቷ ራሴን እና የጋዜጠኝነት ሙያዬን አትኩሮትና ማኅበራዊ ኃላፊነት በተመለከተ አጭር ገለጻ አደረግኩ (ይህንኑ በምልክት ቋንቋ ነገረቻቸው)፡፡

ወደ እኔ ዘወር ብላ፤ “የታሪኩ መቼት (Setting) የሆነው መስማት የተሳናቸው ዜጎች ት/ቤት፣ ወላጆቼ ከአሜሪካን አገር መጥተው የመሠረቱት ነው፡፡ አዝናለሁ፤ በት/ቤቱ ተፈጥሯል የተባለውን የሰብኣዊ መብቶች ጥሰት አሁን በቅርቡ ወደ አዲስ አበባ ስመለስ ነው የሰማሁት፡፡ ግለሰቡን (የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር የነበረ) በሕግ ተጠያቂ ለማድረግ ‹ይርጋ› ይዘጋዋል የሚል የሕግ ባለሙያዎች ስለገለጹልን በብዙኃን መገናኛ ጉዳዩን ወደ አደባባይ ማውጣት ከቻልን ለሌሎች መማሪያና መነጋገሪያ ሊሆን ይችላል በሚል ነው አንተን ያገኘንህ፡፡” (ለእነርሱም ይህንኑ በምልክት ቋንቋ አስረዳቻቸው፡፡)

 

ታሪኩ ባጭሩ

በ1970ዎቹ መጨረሻ እና በ1980ዎቹ መጀመሪያ በቀድሞ አጠራሩ “የኢትዮጵያ ደናቁራን ማኅበር”፣ በአሁኑ ስያሜው ደግሞ “መካኒሳ መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤት” ዳይሬክተር (ሥሙ ለዚህ ጽሑፍ ሲባል የተሸሸገ) በወቅቱ የትምህርት ቤቱ ተማሪ የነበሩ ታዳጊ ወጣት ሴቶችን ቢሮ ውስጥ አስገድዶ እየደፈረ፣ ወጣቶቹ ሲያረግዙ፣ ከት/ቤቱ ገለል እንዲሉ በማድረግ፣ ሲወልዱ ደግሞ ልጆቻቸውን በግብረ ሰናይ ድርጅት በኩል በጉዲፈቻ ወደ ውጭ አገራት የሚልክ ተባባሪ በመምሰል ድርጊቱን ሲያዳፍን እንደነበረ ተጎጂዎቹ ለዚህ ጽሑፍ አቅራቢ አስረድተዋል፡፡

የትምህርት ቤቱን ሴት ተማሪዎች የመድፈር ተደጋጋሚ ድርጊት መስማት በተሳናቸው ማኅበረሰብ ዘንድ በጉልህ የታወቀ ሲሆን፣ በንግግር በሚግባባው አብዛኛው ማኅበረሰብ ዘንድ ግን የተሰወረ ነበር፡፡ እነሆ አሁን ከሠላሳ ዓመታት በኋላ ሴቶቹ ልጆቻቸውን ከመፈለጋቸው ጋር በተያያዘ ወደ አደባባይ እየወጣ ነው፡፡ “በድብቅ የሠሩትን በአደባባይ…” ይሏል ይህ ነው፡፡

ባለታሪኮቹ መስማት የተሳናቸው ሦስት ጉስቅል ወልደው የተቀሙ ሴቶች ናቸው፡፡ ፅጌ መኮንን፣ ወጋየሁ ወርቁ እና ታደለች አረዳ ይባላሉ፡፡ ከእነርሱ ጋር በምልክት ቋንቋ ለመግባባት በአስተናባሪነት የረዱን አቶ መላክነህ ሙሉጌታ እና በማስተርጎም የተባበሩን ደግሞ አቶ አምሳሉ ደሴ ናቸው፡፡

 

ተጠቂዎቹ ይናገራሉ!

የፅጌ ታሪክ

“በመጀመሪያ መንታ ልጆቼን ማግኘት ነው የምፈልገው፡፡ በታዳጊ ወጣትነቴ ጊዜ በአሁን አጠራሩ “መካኒሳ መስማት የተሳናቸው ት/ቤት” በምማርበት ጊዜ በዳይሬክተሩ ተደፍሬ የወለድኳቸው ሁለት ልጆች አሉኝ፤ እነርሱን ማግኘት ነው የምፈልገው፡፡ እናታችሁ እኔ ነኝ ብዬ ልገልጽላቸው እፈልጋለሁ፤ ልስማቸው እፈልጋለሁ፡፡ ልጆቼ ይናፍቁኛል፡፡ ልጆቼ ያለፈቃዴ፣ በጉዲፈቻ ወደ ውጪ አገር የተወሰዱት ገና አንድ ዓመት እንኳ ሳይሞላቸው ነው፡፡ እነዚህ ልጆች የተፈጠሩት የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሳለሁ፣ ዳይሬክተሩ ወደ ቢሮ ይጠራኝና ቢሮውን ቆልፎ አስገድዶ ከደፈረኝ በኋላ ነው፡፡

ፅጌ መኮንን በመካኒሳ መስማት የተሳናቸው ተማሪዎች ትምህርት ቤት ተማሪ በነበሩበት ወቅት በዳይሬክተሩ ተደፈረው መንታ ልጆች ወልደው ነበር። መንታ ልጆቻቸው ያለፈቃዳቸው ለጉዲፈቻ ተሰጥተውባቸዋል። (ፎቶግራፍ በማሕሌት ተሾመ)

“ስድስተኛ ክፍል ደርሼ በመማር ላይ ሳለሁ ሚያዚያ አካባቢ ሆዴ ገፍቶ እርግዝናው ስላስታወቀብኝ እና የመውለጃ ጊዜዬም ስለደረሰ፤ ትምህርቴን አቋርጬ፣ መንታ ልጆቼን ወለድኳቸው፡፡ ያኔ ዳይሬክተሩ ጠርቶኝ ሲደፍረኝ፣ ተማሪዎቹ ሁሉም ያውቃሉ፡፡ መምህራንም ያውቃሉ፡፡ ዳይሬክተሩ ተማሪዎችን ቢሮ እያስገባ ምን እንደሚያደርግ ሁሉም ያውቃሉ፡፡ ግን ማንም አልተከላከለልኝም፡፡

“ተደፍሬ ስወጣም ልጆች ‹ምንድን ነው› ብለው ሲጠይቁኝ ምንም አይደለም ብዬ ዋሸኋቸው፡፡ ምክንያቱም ዳይሬክተሩ ቢሮ አስገብቶኝ ከደፈረኝ በኋላ፣ ‹ለማንም እንዳትናገሪ!› ብሎ አስፈራርቶኝ ነው የለቀቀኝ፡፡ በዚህ ላይ ‹ምንድን ነው ብለው ከጠየቁሽ፣ ቤተሰብ ፈልጎኝ ስልክ ስለተደወለልኝ መልዕክቱን ለማስተርጎም እንደረዳሁሽ ተናገሪ› ብሎ አስጠንቅቆና አስፈራርቶ ነው የለቀቀኝ፡፡

“ግን እዛ ትምህርት ቤት ያለን በሙሉ እርስ በእርስ ሁኔታውን እናውቃለን፡፡ እዛ ውስጥ እንዲህ ዓይነት የመደፈር ሁኔታ ያልገጠማት የለችም። [ወደ ሌላኛዋ ጓዳቸው እየጠቆሙ] እርሷ (ታደለች) ግን ከአንዴም ሁለት፣ ሦስት ጊዜ ታግላ አምልጣው ወጥታለች፤ ጠንካራ ነበረች። ለዚህ ነው ‹ጀግና ሴት ነኝ› የምትለው፡፡ የምትፎክረው፡፡

“መንታ ልጆቼን የወለድኩት ሐምሌ 16 ቀን 1987 እ.ኤ.አ ነበር፡፡ ያኔ የ14 ዓመት ልጅ ነበርኩ፡፡ ልጆቼ ሁለቱም ሴቶች ናቸው፤ ገና አንድ ዓመት ሳይሞላቸው ነው የተወሰዱብኝ፡፡ ልጆቼን በጉዲፈቻ የወሰዷቸው ፈረንጆች ናቸው፡፡ ልጆቼንም የሰጠኋቸው እኔ ፈቅጄ አይደለሁም፡፡ እኔ ሁለቱንም ልጆቼ በጣም ነው የምወዳቸው፡፡ እናቴ ናት የሰጠቻቸው፡፡ ለዚህ ሁሉ የዳረገን ድህነታችን ነው፡፡ ልጆቼ የተሰጡት በእናቴ ተሸንፌ ነው፤ ግን ስላላስቻለኝ በጣም እጨነቅ ነበረ፡፡ ድሀ ብንሆንም እናቴ ምንም ዓይነት ብርም ሆነ ቁሳቁስ ከፈረንጆቹ አልተቀበለችም፡፡

“በጉደፈቻ ከሄዱም በኋላ ስለነርሱ ሰምቼ አላውቅም፤ ግን የተለያዩ መረጃዎችን ቀበሌ ተቀምጠው ነበረ፡፡ እንዲሁም በተለያየ ጊዜ ደብዳቤ ይላክልን ነበር፡፡ እናም የመንትያ ልጆቼን ፎቶ ተልኮልኛል፡፡ የልጆቼ አሳዳጊ ፈረንጅ ልጆች ፎቶዎችም አብሮ አለ፡፡ ልጆቼ ሲወሰዱብኝ በጣም ተበሳጭቼ ስለነበር፣ አንጀቴ አልችል ስላለ ትቼ ሔጄ ነበር፤ ተመልሼ በምመጣበት ሰዓት፣ ይዘዋቸው ሲሔዱ አየሁ፤ ፈረንጆቹ ከመውሰዳቸው በፊትም ፎቶ አንስተዋቸዋል፡፡ ያንን ፎቶ እና ከወሰዷቸው በኋላ ያነሷቸውን ፎቶዎች አብረው ልከውልናል፡፡ የሔዱት ምን አልባት አሜሪካ ሊሆን ይችላል፤ ወይም አውሮፓ፡፡ ሰዎቹ ፈረንጅ ናቸው፡፡ በትክክል ሀገሩን አልነገሩኝም፤ ስለዚህ አላውቅም፡፡”

ፅጌ መንታ ልጆቻቸው በጉዲፈቻ ሲሰጡ፣ (በደርግ ጊዜ) ጉዲፈቻ የሰጠው ድርጅት ይኑር አይኑር ለጊዜው ባይታወቅም፤ ሙሉ የተሟላ መረጃ ባይሆንም ከፊል ሰነዶች ግን አሉ፡፡ ምርመራ ቢጀመር ጠቃሚ ፍንጮች አሉ ባይ ናቸው፡፡

ወጋየሁም እንደ ፅጌ “እኔም የምፈልገው ልጄን ማግኘት ነው፡፡ ልጄ በሕፃንነቱ ነው የተወሰደብኝ፡፡ ከዛ በኋላ ልጄን አይቼው አላውቅም” ይላሉ፡፡ ከወጋየሁ ገለጻ ለመረዳት እንደሚቻለው ልጃቸውን የወለዱበት ቦታ ዘውዲቱ ሆስፒታል ይመስላል፡፡ አጠገቡ ቤተክርስቲያን አለ፣ ጠበል አለ፤ በማለት ያስረዳሉ፡፡ (የእርሳቸው የምልክት ቋንቋ መደበኛው አይደለም፤ ልማዳዊው ነው፡፡ ጠበል የሚሉት ፍልውኃን ሊሆን ይችላል፡፡)

 

የወጋየሁ ታሪክ

አስተርጓሚው እንደተረከው “ትምህርቷን ያቋረጠችበት ምክንያትም ይኸው የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር በ13 ዓመቷ ደፍሯት በማርገዟ ነው፡፡ አፍራና ተሸማቃ ነው ከትምህርት ገበታዋ የቀረችው፡፡ መጀመሪያ ሰውየው ከትምህርት ቤት እንድትወጣና ወደ ሆነ ቦታ እንድትሔድ አደረጋት፡፡ ቦታውን ስትገልጽ ጫካ አለ፤ ቤተክርስቲያን አለ፤ ወደ አሮጌው ኤርፖርት አካባቢ ነው (አሁን ጦር ኃይሎች የሚባለው ሠፈር) ከትምህርት ቤት አስወጥቶ ወደዚህ ሥፍራ ወሰዳት፡፡ ከትምህርት ቤት እንድትወጣ የተደረገው በትዕዛዝ ነው፡፡ አንዲት ሴት መምህርት ናት ሒጂ ብላ ያስወጣቻትና የዚህ ሰውዬ መኪና ውስጥ ታስገባታለች፡፡

ወጋየሁ ወርቁ በመካኒሳ መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤት ተማሪ በነበሩበት ወቅት በዳይሬክተሩ ተደፍረው ልጅ ወልደው ነበር። ልጃቸው ያለፈቃዳቸው ለጉዲፈቻ ተሰጥቶባቸዋል። (ፎቶግራፍ በማሕሌት ተሾመ)

“በመኪና ወስዷት በወቅቱ ጫካ ወደ ነበረ ሥፍራ ወስዶ ከደፈራት በኋላ፣ የመመለሻ የትራንስፖርት ብር ሰጥቷት ይመለሳል፡፡ ከዛ ከወትሮው አምሽታ ወደ ቤት በመመለሷም ከቤተሰብ ጋር ትጋጫለች- የት አመሸሽ በሚል፡፡ በዚህ የተነሳም ከዚህ በኋላ ትምህርት ቤት አትሔጂም ተባለች፤ ለሕይወቷ የሚያስፈልጋትን መደበኛ የምልክት ቋንቋም ሳታውቅ ቀረች፡፡ ምክንያቱም ትኖር የነበረው ከአያቷ ጋር ስለነበር፣ ቤት ውስጥ ቀረች፡፡

“ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ይኸው የደፈራት ሰው በተመሳሳይ ቤት ይመጣና፣ ምንም እንደማያውቅ ሰው፣ ለምን ከትምህርት ቤት እንደቀረች ይጠይቅና ልጅ እንደተወለደ ይነገረዋል፡፡ ልጁ ጉዲፈቻ ለፈረንጅ እንዲሰጥ ሐሳብ አቅርቦ ተፈፃሚ ያስደርጋል፡፡ የእሷም ልጅ (ወደ አሜሪካ ይመስላታል) በጉደፈቻ ተሰጠ፡፡

“የሁለቱም ሴቶች ደፋሪ የተባለው፣ የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር የነበረ ነው፡፡ ልጇንም ወደ ውጪ በጉዲፈቻ የላከው ይኸው ሰው እና የእርሷ አያት ተስማምተው ነው፡፡ ይህ ሲሆን እርሷ አታውቅም፤ ፈቃደኛም አልነበረችም፡፡ ካደገ በኋላ የልጇ ፎቶ በአያቷ በኩል ደርሷታል፡፡ ፎቶ ይላክላቸው ነበር፡፡ የተለያዩ ሰነዶችም ይላካሉ፡፡ የልጇ ፎቶም የአንድ ዓመት፣ የሁለት ዓመት፣ የአራት ዓመት እያለ የተነሳቸውን ፎቶዎች ነው የተመለከተችው፡፡ ልጁ ሲወሰድ የነበረውን ትክክለኛ ዕድሜ አታውቅም ግን ‹ገና እያጠባሁ በነበረበት ወቅት ነው› ትላለች፡፡

“በዚህ ሒደት ውስጥ አያቴ ገንዘብ ስትቀበል አላየሁም፤ የማውቀውም ነገር የለም፤ እንዲህ ታደርጋለች ብዬ አላስብም፤ ‹እኔ ያየሁት ልጁን ወስደው ወደ መኪና ውስጥ ሲያስገቡት ነው፡፡ ያኔ አያቴ ልጁን ለፈረንጆች በጉዲፈቻ ለመስጠት ስትወስን፣ እኔ ተበሳጭቼ ስለነበር እየሮጥኩ ሸሽቼ ሔጄ ብቻዬን ሳለቅስ ነበር፣ በኋላ ስመለስ ነው ወደ መኪና ሲያስገቡት የተመለከትኩት፡፡ ከሔዱ በኋላ ምናልባት አያቴ በስልክ አግኝታ አነጋግራቸው ከሆነ አላውቅም እኔ ግን በግሌ ልጄን ማየት እፈልጋለሁ፤ ማግኘት እፈልጋለሁ፤ መሳም እፈልጋለሁ› ነው የምትለው” ይላል፡፡

 

የታደለች ታሪክ

በዚህ መስማት የተሳናቸው ዜጎች ትምህርት ቤት ውስጥ ከዳይሬክተሩ ብርቱ የብረት መዳፍ ከአንዴም ሁለትና ሦስት ጊዜ በልጅነታቸው በትግል ያመለጡት እና ገፍትረውን እንደተረፉ ጓደኞቻቸውም ጭምር የሚመሰክሩላቸው ታደለች ናቸው፡፡

ዛሬ በኑሯቸው ቢጎሳቆሉም ቁመታቸው ዘለግ ያለ፣ ሰውነታቸውም ደንዳና እንደ ነበር ያስታውቃል፡፡ “እኔ ሰውዬው ቀደም ብሎ ሌሎች ላይ የሚያደርገውን ስለምታዘብ፣ በጭራሽ አላምነውም፡፡ ሌሎቹን ባታለለበት ወጥመድ፣ ለምሳሌ የስልክ መልዕክት እንደመጣልንና እርሱ እያስተረጎመ ሊያግባባን እንደሆነ አድርጎ ወደ ቢሮ ሲጠራኝም በሩን ይዤ ነው የምቆመው፡፡ ወይም ወደ ሌላ ቦታም እንድሔድ ከፈለገ ሌሎች ተማሪዎችና ሰዎች ከሌሉ አልሔድም፡፡ ገፍቶ መጥቶም ከቢሮው በር አታሎ ወይም በጉልበት ሊያስገባኝ ሲል እኔም ያለ የሌለ ጉልበቴን ተጠቅሜ ታግዬው አመልጣለሁ፡፡ ሦስት ጊዜ አሸንፌው ወጥቻለሁ” ብለዋል።

ታደለች አረዳ በመካኒሳ መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤት ተማሪ በነበሩበት ወቅት በዳይሬክተሩ ተደጋጋሚ የመድፈር ሙከራ ተደርጎባቸው ከመደፈር ማምለጣቸውን ይናገራሉ። (ፎቶግራፍ በማሕሌት ተሾመ)

ታደለች እየሳቁ ሲቀጥሉ እነዚህ [የክፍል ጓደኞቿን] ደካሞች ነበሩ፡፡ ያምኑታል፡፡ እኔ ግን ጀግና ነኝ፤ እንደገና ጀግና ነኝ፤ እንደገና ጀግና ነኝ፤ ሦስት ጊዜ ጀግና ሆኜ አሸንፌው አልተደፈርኩም” ይላሉ።

መስማት የተሳናቸው ዜጎች ጉዳዮች ላይ በቅርበት የሚሠሩት አቶ መላከ ሙሉጌታ፣ ከስምንት ዓመታት በፊት መስማት ከተሳናቸው ዜጎች ጋር አዘውትረው በመገናኘት የተለያዩ ሥራዎችን ይሠሩ እንደ ነበር ገልጸዋል፡፡ በማስተርጎም፣ መስማት የተሳናቸው ዜጎች ትምህርት የሚያገኙበትን መንገድ በተመለከተ ዝግጅት በማድረግ ሠርተዋል፡፡ በዚህም መስማት ከተሳናቸው ማኅበረሰብ ጋር የቅርብ ትውውወቅ አላቸው፡፡

ሆኖም፣ “ይሄን ታሪክ ከሰማሁ ግን ሁለት ሳምንት አይሆነኝም›› ይላሉ፡፡ መጀመሪያ በሕግ ጉዳዩን መከታተል የሚችሉበትና፣ ልጆቻቸውን ማግኘት የሚችሉበት ጉዳይ ካለ በሚለው ጥረት አድርጌ ነበር፡፡ ግን ያው በአገሪቱ ሕግ መሠረት የይርጋ ጊዜ ስላለ ይሔንን ጉዳይ በዛ መንገድ ማሳካት እንደማይቻል ከሕግ ባለሙያዎች ስለተረዳሁ ነው ጉዳዩን ወደ እዚህ ያመጣሁት፡፡ ይሔ ጉዳይ የእነርሱ ብቻ ሳይሆን፣ የአገሪቱም ጉዳይ ሊሆን ይችላል በሚል ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ “መካኒሳ መስማት የተሳናቸው ት/ቤት” ከጥበቃ ሠራተኞች እስከ አስተዳደር ድረስ ተደራጅቶ በመንግሥት ዕይታ ውስጥ እየሠራ ነው፡፡ በእርግጥ የመንግሥት ድርጅት አይደለም፡፡ ግን በመንግሥት ቁጥጥር ሥር የሚሠራ ነው፡፡ አሁንም በዕርዳታ ድርጅቶች ነው የሚተዳደረው ይላሉ መላክነህ፡፡

መስማት በተሳናቸው ማኅበረሰብ አባላት ልማድ መረጃ እርስ በእርስ የሚለዋወጡ ቢሆንም፥ ወደ እኛ መስማት ወደ ምንችለው ማኅበረሰብ አይደርስም የሚሉት መላክነህ በዚህ በኩል መንገዱ ዝግ ስለሆነ ነው ብዙ ሰው ጉዳዩን ያልሰማው ይላሉ። ይህንን የመደፈር ታሪካቸውን ሳይቀር እንደቀላል እና የለት ተለት የሕይወት ገጠመኝ የሚቆጥሩትም ለዚያ ነው። “ምክንያቱም የእነርሱ ማኅበረሰብ ይሔን ነገር አይቶት፣ ሰምቶት በቃ ኖርማል ሆኖ ተላምደውታል፡፡ እንደ ተራ ታሪክ ነው የሚያወሩት፡፡ እነርሱ ሲያወሩት እንደ ቀልድ እየሳቁ ሊሆን ይችላል፤ ይሔ በእኛ እና በእነርሱ መካከል ያለው የተግባቦት ችግር የፈጠረው ይመስለኛል” ይላሉ አቶ መላክነህ።

የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ከተጠቂዎቹ ሴቶች ጠይቆ እንደተረዳው ሁለቱም የተደፈሩ ሴቶች ከዚያ በኋላ ትዳር አልመሠረቱም፤ ፅጌ ግን ከፈቀደችው ሰው አንድ ልጅ ወልደዋል። ለዚህም የዳረጋቸው በተደፈሩበት ጊዜያት የገጠማቸው የሥነልቦና ተፀዕኖ እንደሆነ ይገልጻሉ። ፅጌ “እኔ ማግባት አልፈልግም፣ የሥነልቦናው ጥቃት ከአእምሮዬና ከልቦናዬ አልጠፋም፡፡ ምክንያቱም በመጀመሪያ እነዚያ መንታ ልጆች እንዲወለዱ በፈቃዴ የተፈፀመ ግንኙነት አልነበረም፤ ሲቀጥል ልጆቼ ያለፈቃዴ ደግሞ ተወስደውብኛል፡፡ እና ይመጣሉ የሚል ተስፋ ነበረኝ – ብዙ ጊዜ፡፡ አሁንም እንደገና ባገባና ብወልድ፣ ያኛውን ታሪክ ስለሚያስታውሰኝ፣ እንደዛ ለማድረግ በፍፁም አስቤ አላውቅም” ብለውኛል።

ወጋየሁም በተመሳሳይ በታዳጊ ልጅነቷ እንዲህ ዓይነት ችግር ስለደረሰባት፣ የሥነ-ልቦና ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ በተጨማሪ ግን አያትዋ “በፍፁም ከወንድ ጋር እንዲህ ዓይነት ንክኪ እንዳታደርጊ!” በሚል እንዳስጠነቀቋቸው ይናገራሉ።

እነዚህ ሴቶች ዛሬም ድረስ ለደረሰባቸው በደል ፍትሕ ባይጠይቁም ልጆቻቸውን ለማየት ድምፅ አልባ ጩኸት እየጮኹ ይገኛሉ።

(የኢትዮጵያ ሰብኣዊ መብቶች ፕሮጀክት (ኢሰመፕ) የነዚህን ባለታሪኮች ቀጣይ ሁኔታ ተከታትሎ ለማቅረብ ይሞክራል።)

Leave a Reply

Your email address will not be published.