ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው የቀረበበት የሽብር ክስ ተነስቶ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ የተመለከተውን አንቀጽ 257 (ሀ) መተላለፍ እንዲከላከል ብይን ተሰጠ::

getachew-shiferaw

በማህበራዊ ሚዲያ በተለይም ፌስቡክ እንዲሁም በስልክ መገናኛ ዘዴዎች ግንቦት ሰባት ከተባለው አሸባሪ ቡድን አመራሮች ጋር ግንኙነት አድርገሃል በሚል የጸረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 7(1) የተመለከተውን በመተላለፍ የሽብር ክስ ተመስርቶበት ጉዳዩ በፍርድ ቤት ሲታይ የከረመው የነገረ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው የቀረበበት የሽብር ክስ ተነስቶ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ አንቀጽ 257(ሀ) የተመለከተውን የወንጀል ድርጊት መተላለፍ እንዲከላከል ከፍተኛ ፍ/ቤት ብይን ሰጥቷል፡፡
ታህሳስ 13/2009 ዓ.ም የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት የአቃቤ ህግ ማስረጃን መርምሮ ተከሳሹ መከላከል ይገባዋል ወይስ መከላከል ሳያስፈልገው በነጻ ይሰናበት በሚለው ላይ ብይኑን ያሰማ ሲሆን፣ አቃቤ ህግ ያቀረበው የሰነድ ማስረጃ ተከሳሹን በሽብር የሚያስጠይቀው እንዳልሆነ በመግለጽ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

የፌደራል አቃቤ ህግ በጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው ላይ ለመሰረተው ክስ ያቀረበው ማስረጃ ከማህበራዊ ሚዲያ ፌስቡክና ከስልክ ግንኙነት ከብሄራዊ መረጃና ደህንነት የተገኘ የሰነድ ማስረጃ ብቻ ነው፡፡ ፍ/ቤቱ ብይኑን የሰጠው ይኸንኑ አቃቤ ህግ ተከሳሹ ከሽብር ቡድን አመራሮች ጋር ግንኙነት ስለማድረጉ ያስረዳልኛል በሚል ያቀረበውን የሰነድ ማስረጃ ሲሆን፣ በማስረጃ ምዘና ወቅት ተከሳሹ የሽብር ወንጀል ስለመፈጸሙም ሆነ ከሽብር ቡድን ጋር ግንኙነት ስለመኖሩ የቀረበው ማስረጃ አያመለክትም በማለት ተከሳሹን ከሽብር ወንጀል ነጻ ብሎታል፡፡

ሆኖም ተከሳሹ በማህበራዊ ሚዲያ አማካኝነት ከተለዋወጣቸው መልዕክቶች መካከል በሌላ መዝገብ በሌለበት የሽብር ክስ ቀርቦበት ጥፋተኛ ከተባለው አበበ ገላው ጋር ያደረገው የመልዕክት ልውውጥ ግዙፍ ያልሆነ የወንጀል መሰናዳትና መገፋፋት ድርጊትን እንደሚያመለክት በመግለጽ ክሱ ወደ መደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ተቀይሮ አንቀጽ 257 (ሀ) ላይ የተመለከተውን እንዲከላከል ሲል ብይን ሰጥቷል፡፡

በዚህ መሰረት ተከሳሹ መከላከያ ማስረጃ ካለው የማስረጃ ዝርዝሩን እንዲያስመዘግብ፣ እንዲሁም በእለቱ የተከሳሽ ጠበቃ በህመም ምክንያት ባለመቅረባቸው ተከሳሹ ከጠበቃው ጋር ተመካክሮ ዋስትና መብቱ እንዲከበርለት ለመጠየቅ ባመለከተው መሰረት፣ የዋስትና ጥያቄንና የማስረጃ ዝርዝር መግልጽን ለመጠባበቅ ለታህሳስ 19/2009 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡ ተከሳሹ ተከላከል የተባለበት የህግ አንቀጽ የዋስትና መብትን ይፈቅዳል፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው በሽብር ተጠርጥረሃል በሚል ለእስር ከተዳረገ አንድ አመት አስቆጥሯል፡፡

Reported on December 26/2016

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *