ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የምርጫ ጊዜ መዛወርን ተከትሎ በቀረቡ የመፍትሔ አማራጮች ዙሪያ የቀረበ አቤቱታ

ግንቦት 25፣ 2012

አዲስ አበባ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል እና ሴንተር ፎር አድቫንስመንት ኦፍ ራይትስ ኤንድ ዴሞክራሲ (ካርድ) በቀን ግንቦት 13፣ 2012 ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራስያዊ ሪፑብሊክ፣ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በተጻፈ ደብዳቤ የምርጫ ጊዜ መዛወርን በሚመለከት በከሳሽነት ወይም በጣልቃ ገብነት ለመሟገት የቀረበ ማመልከቻ በጉዳዩ የመሳተፍ መብታችንን በማስረዳት አግባብነት ያላቸውን የሕገ መንግሥት ስርዓቱን ያጠናክራሉ ያልናቸውን የስልታዊ ሙግት (Strategic Litigation) መከራከርያዎች አቅርበን ነበር። (ማመልከቻችንን እዚህ ዳውንሎድ ያድርጉ።) ይሁንና አጣሪ ጉባዔው ለማመልከቻችን ምንም ምላሽ ያልሰጠን ከመሆኑም ባሻገር፥ ለኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 21፣ 2012 ምላሸ መስጠቱን አሳውቋል። በዚም መሠረት  ምክር ቤቱ በዚህ ሳምንት ምላሹ ላይ ተወያይቶ ውሳኔውን ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ይሁንና አመልካች ድርጅቶች ውሳኔው ይፋ ከመሆኑ አስቀድመን ያቀረብነው ማመልከቻ ምላሽ እንዲያገኝ በማሰብ በግልጽ ጋዜጣዊ መግለጫ መልክ በድጋሚ ይፋ እንዲሆን ወስነናል።

በማመልከቻችን፣

1ኛ. በጉዳዩ የመሳተፍ መብት በአንድ የጥናት መስክ ሦስተኛ ዲግሪ ያላቸውን ዜጎች ብቻ የሚመለከት ስላለሆነ እና እኛም ሕጋዊ ሰውነት እንዳላቸው ድርጅቶች አማራጭ የማቅረብ እና የመደመጥ መብት ያለን መሆኑን፣

2ኛ. የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤው የሕገ መንግሥት ትርጉም የማስተናገድ ሥልጣን የሌለው መሆኑን እና ምክረ ሐሳብ ለመስጠትም ከፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ እስኪቀርብለት መጠበቅ ያለበት መሆኑን፣

3ኛ.  የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤው ከፊል አባላት የገዢው ፓርቲ አባላት በመሆናቸው እና ይህም የገለልተኝነት እና ነጻ ዳኝነት ጥያቄ የሚያስነሳ በመሆኑ አባላቱ በገዛ ፈቃዳቸው ወይም በጉባኤው ትዕዛዝ መልቀቅ ያለባቸው መሆኑን፣

4ኛ. ኢትዮጵያ ያደሩ የፖለቲካ ቅራኔዎች እና ጥያቄዎች ያሏት አገረ መንግሥት እንደመሆኗ ለሕዝቦች እንድነት እና ለፖለቲካ ኀይሎች መሠረታዊ ሥምምነት ሲባል የባለድርሻ አካላት በውሳኔ አሰጣጡ ሒደት ውስጥ የምክክር ዕድል ሊሰጣቸው የሚገባ መሆኑን ገልጸናል።

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔው በከሳሽነት ወይም በጣልቃ ገብነት ለመሟገት ያቀረብነውን ማመልከቻ በሚመለከት ጭብጥ አስይዞ ካለማከራከሩም በላይ፣ ለማመልከቻው የደረሰኝ ቁጥር ወይም ሌላ ማረጋገጫ አልሰጠንም። ይህ ሁኔታ ፍትሕ የማግኘት መብታችንን ከመገደብ ወይም ከመጣስ አልፎ ፍትሕ የመጠየቅ ዕድል የነፈገን ከመሆኑ አንጻር የሚመለከታቸው አካላት ውሳኔያቸውን ይፋ ከማድረጋቸው በፊት ጊዜ ወስደው ምላሽ እንዲሰጡ በማለት አቤቱታችንን እናቀርባለን። የማመልከቻችንን ዝርዝር ከዚህ መግለጫ ጋር አያይዘናል።

ከሠላምታ ጋር፣

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶችና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል፣

ሴንተር ፎር አድቫንስመንት ኦፍ ራይትስ ኤንድ ዴሞክራሲ

Center for Advancement of Rights and Democracy (CARD)

Making Democracy the Only Rule of Game!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *