ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነሮችን ሥያሜ በተመለከተ

ጥር 5፣ 2014 – ሥማችን ከዚህ በታች የተዘረዘረው አገር በቀል የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቅርቡ ያፀደቀው የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን የሚያመቻቸው የምክክር ሒደት ሁሉን አካታች፣ ተዓማኒ እና ግልጽ መሆኑን ለመከታተል የበኩላችንን ለመወጣት ቅድመ ዝግጅት እያደረግን እንገኛለን።

በአዋጁ እንደተገለጸው፣ አገራዊ ምክክሩ ለዘመናት ሲንከባለሉ የመጡ ችግሮችን ሁሉን አካታች በሆነ ንግግር ለመፍታት እንዲቻል፣ የሒደቱ ግልጽነት በብዙኃን ዘንድ ለሚኖረው ተዓማኒነት እና ቅቡልነት ወሳኝ ሚና አለው። በመሆኑም ለኮሚሽኑ ተቋማዊ ግንባታም ይሁን ለኮሚሽነሮቹ ሥያሜ ያለው ሕዝባዊ ተሳትፎ ሰፊ እንዲሁም ግልጽነት የተላበሰ መሆን ይኖርበታል።

ስለሆነም፣ አገራዊ ምክክሩን የሚያመቻቸው ኮሚሽን ተዓማኒነቱ ጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለን እናምናለን። ለዚህም የኮሚሽነሮች ጥቆማ ከሕዝብ፣ ከሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፣ እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲዎች እየተሰበሰበ መሆኑ ሊደነቅ የሚገባው ቢሆንም፥ የተሰጠው ጊዜ ግን አጭር ሆኖ አግኝተነዋል። የኮሚሽነሮች የጥቆማ ጊዜ ማጠሩ ከመረጃው ተዳራሽነት፣ በተለያዩ የአገራችን ክፍሎች ካለው የመገናኛ ዘዴዎች ውሱንነት፣ ብሎም ለኮሚሽነርነት ብቁ የሆኑ ሰዎችን ለማሰብ ከሚወስደው ጊዜ አንፃር በቂ ጥቆማዎች እንዳይደረጉ እንቅፋት ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሮብናል።

በተጨማሪም፣ በሕዝብ ከተጠቆሙ ኮሚሽነሮች መካከል የመጨረሻ 14ቱ ዕጩዎች በአፈ ጉባዔው ተለይተው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርቡ የተገለጸ ሲሆን፥ ዕጩዎቹ ተለይተው የሚቀርቡበትን መመዘኛ ሁኔታ በተመለከተ የአሠራር ግልጽነት አለመኖሩን አስተውለናል። በሕዝብ የተጠቆሙት ዕጩዎች በምን መመዘኛ እንደተመረጡ ለብዙኃን ግልጽ ማድረግ የሚቻልበትን አሠራር መመሥረት ለኮሚሽኑ ተዓማኒነት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለን እናምናለን።

ስለሆነም፣ ኮሚሽነሮችን የመጠቆሚያ ጊዜው እንዲራዘም እንዲሁም የመጨረሻዎቹ ዕጩ ኮሚሽነሮች ከተጠቆሙት ሰዎች መሐከል ተለይተው የሚቀርቡበት መመዘኛ ግልጽነት እንዲኖረው እንጠይቃለን።

ጥያቄውን ያቀረብነው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች፦

 1. የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅቶች ህብረት (CEHRO)
 2. የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (CARD)
 3. ኢስት አፍሪካን ኢኒሺዬትቭ ፎር ቼንጅ (I4C)
 4. የሕግ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች (LHR)
 5. የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር (EWLA)
 6. የኢትዮጵያ አርታኢያን ማኅበር (EGE)
 7. ሴታዊት ንቅናቄ
 8. ስብስብ ለሰብዓዊ መብቶች በኢትዮጵያ (AHRE)
 9. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ተሟጋቾች ማዕከል (EHRDC)
 10. ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ፋውንዴሽን
 11. የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ)

Center for Advancement of Rights and Democracy (CARD)

Making Democracy the Only Rule of Game!

Leave a Reply

Your email address will not be published.

*

code