ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ እነ ጃዋር መሐመድ ላቀረቡት አቤቱታ ዐቃቤ ሕግ መልስ እንዲሰጥበት ቀጠሮ ሰጠ

ኅዳር 24፣ 2014 - የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት 2ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት የይግባኝ አቤቱታቸውን መርምሮ፣ የሥር ፍርድ ቤት ተከሳሾቹ በሌሉበት ጉዳያቸው ይታይ ሲል የሰጠውን ብይን “አግባብ አይደለም” ሲሉ ተከሳሾች ያቀረቡት የመቃወሚያ አቤቱታ ላይ ዐቃቤ ሕግ መልስ እንዲሰጥ፣ አቤቱታቸው ችሎት ያስቀርባል ሲል ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

ከዚህ በፊት ተከሳሾቹ ‘በፍርድ ቤት ነጻ የሚባሉ ግለሰቦች በአስፈፃሚ አካላት እየታሰሩ ነው’ ሲሉ ምክንያታቸውን ጠቅሰው፥ ጉዳያቸውን ለሚመለከተው መደበኛው ፍርድ ቤት ‘በገዛ ፍቃዳችን በችሎት አንቀርብም’ ማለታቸውን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ በሌሉበት ‘ምስክሮቼ ይሰሙልኝ’ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቆ ነበር።

በዚህም የሥር ፍርድ ቤቱ ተከሳሾቹ በሌሉበት ጉዳያቸው እንዲታይ ብይን መስጠቱ ይታወሳል።

ሆኖም የሥር ፍርድ ቤቱ የሰጠው ውሳኔን ተገቢነት የለውም ሲሉ ባለ 5 ነጥብ ምክንያቶች ጠቅሰው የጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሐምዛ አዳነ እና የደጀኔ ጣፋ ጠበቆች የይግባኝ አቤቱታቸውን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት በኅዳር 7 ቀን 2014 አስገብተው ነበር።

ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ በዛሬው ቀጠሮ አቤቱታቸውን መርምሮ መዝገቡ ያስቀርባል ሲል፣ በይግባኙ ላይ ዐቃቤ ሕግ መልስ እንዲሰጥበት ለታኅሣሥ 6 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በሌላ በኩል ዐቃቤ ሕግ ጃዋር መሐመድን ጨምሮ በሁሉም ተከሳሾች ላይ የሚሰሙ ምስክሮች ለደኅንነታቸው ከምስክር ጥበቃ አዋጁ አንጻር 10ሩ ምስክሮች በዝግ ችሎት፣ 136ቱ ምስክሮች ደግሞ ከማጋረጃ ጀርባ እንዲሰሙለት ያቀረበው አቤቱታ በሥር ፍርድ ቤት ውድቅ መደረጉን ተከትሎ፣ ምክንያቶቼ ሳይመዘኑ አቤቱታዬ ወድቅ መደረጉ አግባብነት የለውም ሲል በድጋሚ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ጠይቆ ነበር። የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ 2ኛ ይግባኝ ሰሚ ችሎት አቤቱታቸውን መርምሮ በምስክሮች ደኅንነት ላይ ሊደርስ የሚችል አደጋ በማሳያ አልቀረበም ሲል የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔ እንደማይቃወም በመግለጽ፥ የዐቃቤ ሕግ አቤቱታውን አያስቀርብም ሲል ውድቅ አድርጎታል።

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.