
በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት ጥር 14፤ 2013 በዋለው ችሎት በእነ ጃዋር መሐመድ የክስ መዝገብ ሥር ተሻሽለው የቀረቡትን ክሶች ተመልክቷል።
ፍርድ ቤቱ ጥር 4 በዋለው ችሎት በሰጠው ትዕዛዝ መሠረት ዐቃቤ ሕግ ያሻሻለውን የክስ ዝርዝር ለችሎቱ በጽሑፍ ያቀረበ ሲሆን፥ ከተራ ቁጥር 5 እስከ 10 ያሉ ክሶችን በሚመለከት ግን የቀደመው ችሎት እንዳቀረበው በአዋጅ 1177/2012 አግባብነት ያለው የሕግ መሠረት መሆኑን በመጥቀስ አሻሽሎ የሚያቀርበው ነገር እንደሌለ ለችሎቱ አሳውቋል። ችሎቱም ተሻሽሎ የቀረቡትን ክሶች እንደሚከተለው በመዘርዘር በቀረበው አቤቱታ ላይ ውሳኔ አሳልፋል።
በክስ 1 ሥር ሸኔ በሚል የቀረበው ቃል ግለሰብ ይሁን ቡድን ግልጽ አይደለም ተብሎ በቀረበው አቤቱታ መሠረት ቡድን በሚል ተሻሽሎ ቀርቧል። በሁለተኛ ደረጃ 3ኛ ተከሳሽን በሚመለከት በምን ሚዲያ ተጠቅመው ነው ቅስቀሳ ያደረጉት ለሚለው በፌስቡክ ድረገጽ እና በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ላይ በሚል ተሻሽሏል።
በሌላ በኩል ከተራ ቁጥር 5 እስከ 10 ያሉ ክሶች ባለመሻሻላቸው ውድቅ እንዲደረጉ ችሎቱ ወስኗል። እነዚህ ክሶች 1ኛ እና 2ኛ ተከሳሾችን ጨምሮ በአጠቃላይ 12 ተከሳሾችን የሚመለከቱ መሆናቸውን ያወሳው ችሎቱ ድርጊቱ የተፈፀመው አዋጅ 1177 ከመፅደቁ በፊት በመሆኑ አዋጁ ከመውጣቱ በፊት ለተፈፀሙ ድርጊቶች ተፈፃሚነት እንደማይኖረው ገልጿል። በመሆኑም የወንጀል ሕጉን አንቀጽ 2 እና ሕገ መንግሥቱን በመፃረር መሠረታዊ የሕግ ስህተት እንዳይፈጠር ክሶቹ ካልተሻሻሉ በስተቀር እንዲቋረጡ በማለት ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ችሎቱ ከዚህ ትዕዛዝ በኋላ ወደ እምነት ክህደት ቃል እንዲገቡ ቢጠይቅም የተከሳሾች ጠበቆች ክሱ መሻሻሉን በሚመለከት ጊዜ ሰጥተን ከደንበኞቻችን ጋር ያላየን እና ያልመከርንበት ስለሆነ በወንጀል ሥነ ስርዓት ሕጉ አንቀፅ 120/3 መሠረት አጭር ቀጠሮ ይሰጠን በማለት አቤቱታ አቅርበዋል። በተጨማሪም ተከሳሾቹ ከተራ ቁጥር 5-10 ባሉና በችሎቱ ውድቅ ከተደረጉ ክሶች ጋር በተያያዘ አቤቱታ አሰምተዋል።
በዚህም መሠረት ጃዋር መሐመድ የተያዙት ጦር መሣሪያዎች በመንግሥት የተሰጣቸው እና በሕጉ መሠረት የተመዘገቡ እንደመሆናቸው ወንጀል ያለመሆኑ እየታወቀ ዐቃቤ ሕግ ግን ሆን ብሎ ያቀረበው ክስ ነው ብለዋል። አያይዘውም የተቀሩትም ክሶች ቢሆኑ የውሸት እና ጭብጥ የሌላቸው መሆናቸውን በማውሳት ዐቃቤ ሕግ የፍርድ ቤቱን ጊዜ ብሎም የተከሳሾቹን በመጭው አገራዊ ምርጫ ተሳትፎ ባያስተጓጉል ሲሉ አቤቱታቸውን አሰምተዋል። ደጀኔ ጣፋም ተመሳሳይ ሐሳብና አቤቱታ አቅርበዋል።
ችሎቱ የቀረቡትን አቤቱታዎች በማዳመጥ ተከሳሾቹ ከጠበቆቻቸው ጋር የተገናኙበት ጊዜ አጭር መሆኑን እንዲሁም የእምነት ክህደት ቃል መስጠት ከባድና ዝግጅት የሚጠይቅ ነው በማለት ለጥር 19፤ 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።