Photo Credit - Addis Standard

የእነ ጃዋር መሓመድ መዝገብ፤ የጥር 04/2013 የፍርድ ቤት ውሎ።

ታህሳስ 8 ባስቻለው ችሎት በእነ ጃዋር መሓመድ መዝገብ ስር የተከሰሱ ተከሳሾች ጠበቆች በፍርድ ቤቱ ስልጣን እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ያቀረቡትን ተቃውሞ በተመለከተ የአቃቤ-ህግን ዝርዝር የጽሁፍ ምላሽ ያዳመጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት የቀረቡ መቃወምያዎችን በተመለከተ ጥር 4፤2013 ዓ.ም ብይን ሰጥቷል፡፡ በችሎቱ አቶ ጃዋር መሓመድ እና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ ሁሉም ተከሳሾች ቀርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ በዋነኛነት የተሰየመው በተከሳሾች ጠበቆች በተነሱ መቃወምያዎች ላይ ብይን ለመስጠት ቢሆንም ከክስ ሂዴቱ ጋር የተያያዙ የአካሄድ ጉዳዮችንም ተመልክተል፡፡

የተነሱ የአካሄድ/ ስነ-ስርአታዊ ጉዮች፤

በችሎቱ የፍርድ ቤቱ ውሳኔ ከመነበቡ በፊት ከተከሳሾች መሀል ተርጓሚ የሚስፈልገው ተከሳሽ ካለ የተጠየቀ ሲሆን አንዳንድ አማርኛ ቋንቋ የማይችሉ ቢኖሩም እርስ በራሳቸን መረዳዳት እንችላለን በማለት አስተርጓሚ እንደማያስፈልጋቸዉ ተከሳሾቹ መልስ ሰጥተዋል፡፡ በተጨማሪም ተከሳሾቹ በጠበቆቻቸው በኩል ችሎት ለመቅርብ ወደ ፍርድ ቤት ከሚጓዙበት ሁኔታ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ሀሳብ ለማስረዳት ፍቃድ ጠይቀው ተፈቅዶላቸው ሀሳባቸውን አቅርበዋል፡፡

በዚህም መሰረት አቶ በቀለ ገርባ ፍርድ ቤቱ በባለፈው ችሎት ተከሳሾች በቀጣይ ችሎት አስፈላጊ ከሆነ በፖሊስ አስገዳጅነት ጨምር እንዲቀርቡ የሰጠው ትእዛዝ ተከሳሾቹ ችሎቱን ንቀው ሳይሆን በአቤቱታ መልክ ያቀረቡትን ምክንያት ከግምት ያላስገባ፤ የዳኞችን ገለልተኛነት እንዲሁም የፍትህ ስርዓቱን እንድንጠራጠር አርጎናል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ከማረሚያ ቤት ወደ ፍርድ ቤት የሚያደርጉት ምልልስ ካለው እርቀት አኳያ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰው የተሰጠው ትእዛዝ ግን ፍርድ ቤቱ ብሎም መንግሥት የተከሳሾችን ደህንነት በተመለከተ ኃላፊነት መውሰዳቸውን የሚያመለክት መሆኑን በአጽኖት ገልጸዋል፡፡

አቶ ጃዋር በበኩላቸው በአገሪቱ ካለው የፖለትካ ሁኔታ አንጻር በተከሳሾች ላይ ጉዳት ብደርስ ሊከሰት የሚችለውን ቀውስ ከግምት በማስገባት የጽሁፍ አቤቱታ አቅርበው ሳለ በቀጣይ ችሎት በኃይል እንዲቀርቡ ትእዛዝ መሰጠቱ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም ወደ ፍርድ ቤት ከሚያደርጉት ምልልስ ጋር ተያይዞ በተከሳሾች ደህንነት ብሎም በአገሪቱ ሰላም ላይ ለሚደርስ የትኛውም ችግር የችሎቱ ዳኞች እና መንግስት ተጠያቂ መሆናቸውን አስረግጠው ሁኔታውን በሸኔ፤ ወያኔ ወይም ሻቢያ ማሳበብ አይቻልም ብለዋል፡፡

የተከሳሾቹን ቅሬታ ካዳመጠ በኃላ ፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን እንደሚረዳ፤ በተሰጠው ትእዛዝ ላይ በግዳጅ ይቅረቡ የሚለው በአማራጭነት የተሰጠ እና የሚፈጠረውን የችሎት መስተጓጎል ለማስቀረት ያለመ መሆኑን ማብራርያ ሰጥተዋል፡፡ በተጨማሪም የተከሳሾቹን ደህንነት በተመለከተ በተቻለ መጠን ክትትል እንደሚያደርግ፤ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራና ትእዛዝም እንደሚሰጥ ችሎቱ ለተከሳሾች ገልጸዋል፡፡

በተነሱ መቃወምያዎች ላይ የተሰጠው ብይን፤

ከአካሄድ/ስነ-ስርአታዊ ጉዳዮችበመቀጠል ፍርድ ቤቱ በተከሳሾች ጠበቆች በቀረቡት መቃወምያዎች ላይ ብይን ሰጥተዋል፡፡ አንደኛ፤ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን የማየት ስልጣን የለውም በማለት ለቀረበው መቃወምያ ችሎቱ በህግ በተደነገገው መሰረት የዳኝነት ስልጣን እንዳለው ብይን ሰጥተዋል፡፡ ሁለተኛ፤ ጉዳዩን ወደ ኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ማዘዋወር ከግዜ አኳያ ፍትህ ለመስጠት የተፋጠነ እንዳልሆነ፤ በቂ አማርኛ ተናጋሪና አስተርጋሚ በመኖሩ እና ጉዳያችን ይዘወርልን የተባለበት የኦሮሚያ ጠቅላይ ፍርድ ቤት አዲስ አበባ ከተማ የሚገኝ እንደመሆኑ የቦታ ለዉጥ የማይኖር መሆኑን በመጥቀስ ፍርድ ቤቱ መቃወሚያዉን ዉድቅ አድርግታል፡፡

ሶስተኛ፤ የጦር መሳርያዎችን በሚመለከት ለቀረበው ክስ አዋጁ የጸደቀው ከታህሳስ 30፤ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ስለሆነ እና ተፈጸመ የተባለው ድርጊት ከዛ በፊት ስለሆነ የወንጀል ድርጊት ተብሎ ሊቀርብ አይችልም፣ ህጋዊ መርህም የሚጣረስ ነው በሚል የቀረበው መቃወምያ ችሎቱ በከፊል ተቀብሎ ውሳኔ ሰጥቶበታል፡፡ በዚህ መሰረት አቃቤ ህግ በመደበኛ ወንጀለኛ ህግ ወይም በሌላ አግባብ ባለዉ ህግ እንዲከስና ክሱን አሻሽሎ እንዲያቀርብ ችሎቱ አዝዘዋል፡፡ አራተኛ፤ ከአምስተኛ እስከ አስረኛ ያሉ ክሶች በአንድ ላይ መቅረብ የሚችሉ ሰለሆኑ በአንድ ላይ ይጠቃለሉ በሚል የቀረበዉንም አቤቱታ ችሎቱ ዉድቅ አድርጓል፡፡ ቴሌኮም ማጭበርበር ከሚለው ክስ ጋር በተያያዘ አዋጅ 761/2004 በግለሰብ ደረጃ መያዝ ያለበትና የሌለበት ብሎ በግልጽ እንዳላስቀመጠ እና በግልጽ ወንጀል ነዉ ተብሎ ባልተደነገገበት ሁኔታ መጠየቅ አይገባም በሚል ለቀረበዉ አቤቱታ ችሎቱ በህጉ መሰረት በክስ መዝገቡ የተጠቀሱትን መሳሪያዎች ይዞ የመገኘት መብት የኢትዮ-ቴሌኮም ብቻ በመሆኑ አቤቱታዉ ተገቢነት እንደለለው ተገልጾ በፍርድ ቤቱ ውድቅ ተደርገዋል፡፡ በተጨማሪም “ነፍጠኛ” የሚለው ወንጀል ነዉ ተብሎ ባልተቀመጠበት ሁኔታ ከሆነም ብዙ ሰዉ ከኛ ጋር መጠየቅ አለበት በሚል ለቀረበዉ አቤቱታ ጉዳዩ እንደወንጀል የተቀመጠ ነው በማለት ችሎቱ መቃወሚያዉን ዉድቅ አድርጎታል፡፡

ክሱ የወንጀለኛ መቅጫ ሰነ-ስርዓቱን ያልጠበቀ ነው የሚለውን አቤቱታ ውድቅ ያደረገው ችሎቱ ክስ አንድ እና ሶስት ተነጥሎው መቅረቡ ተገቢ አይደለም እንዲሁም ከሁለተኛ እስከ ዘጠነኛ እና አስራሶስተኛ፣ አስራአራተኛ እና አስራሰባተኛ ክሶች ላይ ወንጀሉ ተለይቶ አልቀረበም የሚሉት መቃወምያዎችንም ውድቅ አድርጓል፡፡

በአጠቃላይ ችሎቱ የቀረቡ መቃወምያዎች አብዛኛዎቹ የህግ መሰረት የሌላቸው ናቸዉ በማለት ውድቅ አድረጓል:: በሌላ በኩል አቃቤ ህግ በአንደኛ ተከሳሽ ላይ ያቀረበውን ሶስተኛ ክስ አሻሽሎ እንዲያቀርብ ችለቱ ያዘዘ ሲሀን “ሸኔ” የሚለው ቃል ቡድን ይሁን ግለሰብ እንደሚያመለክት በግልጽ እንዲቀርብ ችሎቱ አዝዋል፡፡ ቀጣይ ቀጠሮን በተመለከተ ተሻሽሎ እንዲቀርብ የተባለው ክስ ብዙ መሆኑን እና ክሱን ያዘጋጁት ባለሙያዎች በስራ ጉዳይ ሌላ ሃገር መሆናቸውን በመጥቀስ አቃቤ-ህግ የአንድ ወር ግዜ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡ ተከሳሾች እና ጠበቆቻቸዉ በበኩላቸው ቀጠሮዉ ከሳምንት ጊዜ ያልበለጠ እንዲሆንላቸዉ ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ከጥምቀት በዓል ጋር ተያይዞ ወደ ፍርድ የሚደረግ ጉዞ አስቸጋሪ ሊሆን አንደሚችል በማውሳት አቃቤ ህግ የመንግስት አካል ስለሆነ እና በተሰጠው ግዜ ክሱን አሻሽሎ ለማቅረብ የሚችል መሆኑን በመጥቀስ ለጥር 14፤ 2013 ዓ.ም ቀጥረዋል፡፡

Center for Advancement of Rights and Democracy (CARD)

Making Democracy the Only Rule of Game!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *