ፍርድ ቤቱ በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ የዐቃቤ ሕግ 4ተኛ ምስክር በ48 ሰዓት በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለው እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጠ

  • የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በታዘዘው መሠረት እስክንድር ነጋ ላይ የደረሰውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ማጣራት አለመጀመሩ ተነግሯል፤ ጉዳዩ ግን በወንጀል ተይዟል ተብሏል።

ታኅሣሥ 11፣ 2014 - የዝዋይ ማረሚያ ቤትን ከማደራጀት ሥራ ተያይዞ በአጃቢ እጥረት ምክንያት በባለፈው ሁለት ቀጠሮ ችሎት ሳይቀርቡ የቀሩት ተከሳሾች እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሁሉም ቀርበዋል። የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በእነ እስክንድር ነጋ ላይ ቀሪ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ለመስማት የተሰየመ ቢሆንም በባለፈው ቀጠሮ ችሎት ቀርቦ ማንነቱን አስመዝግቦ ለዚህኛው ቀጠሮ እንዲቀርብ ታዝዞ የነበረው ምስክር ሳይቀርብ ቀርቷል።

ዐቃቤ ሕግ ባድራሻቸው ተፈልገው ያልተገኙት 4ኛ ምስክር ታስሮ እንዲቀርብ ያመለከተ ሲሆን ሌላ አንድ ቀሪ ምስክር ደሞ በድጋሚ መጥሪያ እንዲደርሳቸው በድጋሚ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

በወቅታዊ ጉዳይ ከአዲስ አበባ ውጪ ናቸው ያላቸው 8ኛ ምስክር ጌትነት ተስፋዬን በተመለከተ ግን ምስክርነታቸው እንዲታለፍ ጠይቀዋል።

የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው ምስክሩ ከዚህ በፊት በነበሩት ቀጠሮዎች በኮቪድ ሕመምተኛ መሆናቸውን ተከትሎ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠኝ ብለው በተሰጣቸው ተለዋጭ ቀጠሮም መቅረብ አልቻሉም፤ ይህ ደግሞ ምስክሩ ቀርበው ለመመስከር ፍላጎት የላቸውም ወይም ፍቃደኛ አደሉም ማለት ነው፤ ስለዚህ ችሎቱ ተጨማሪ ቀጠሮ ሊሰጥ አይገባም ብለው ተከራክረዋል።

ፍርድ ቤቱም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ምስክሩን በ48 ሰዓት በቁጥጥር ሥር አውለው እንዲያቀርቡት ትዕዛዝ ሰጥቷል።

እስክንድር ነጋ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከአገር ውጪ የሚገኙ ቤተሰቤን በሳምንት አንድ ቀን ጌዜ በስልክ እንዳገኛቸው የታዘዘውን ትዕዛዝ አልፈፀመልኝም ሲሉ አቤቱታ አቅርበዋል።

ፍርድ ቤቱም ትዕዛዝ ለምን እንዳልተፈፀመ የማረሚያ ቤቱ የእስረኞች ኃላፊ ቀርበው እንዲያስረዱ አዟል።

እስክንድር ነጋ ከዚህ በፊት በሌላ ታራሚ ደረሰብኝ ባሉት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አጣርቶ ሪፖርት እንዲያደርግ በፍርድ ቤቱ መታዘዙ ይታወሳል። ይሁንና ፍርድ ቤቱ ኮሚሽኑ ማጣራት መጀመር አለመጀመሩን ለማረጋገጥ ባቀረበው ጥያቄ እስክንድር ነጋ ማንም አካል የማጣራት ሥራ አለመጀመሩን ተናግረዋል፤ በተጨማሪም ጉዳዩ በወንጀል መያዙን ገልጾ ኮሚሽኑ ባይለፋ ሲል እስክንድር አስተያየታቸውን አክለዋል።

ፍርድ ቤቱ ኮሚሽኑ በታዘዘው መሠረት የማጣራት ሥራውን ለምን እንዳልጀመረ እንዲያስረዳ አዘዋል። ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ለመስማት ለታኅሣሥ 15 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.