Photo Credit - Addis Standard

ፍርድ ቤቱ የእነ አቶ ጃዋር መሀመድን የእምነት ክደት ቃል ለመስማት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጠ፤(ጥር 19፤ 2013 ዓ.ም)

(ጥር 19፤ 2013 ዓ.ም)

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ ሽብር እና ህገ መንግስታዊ ጉዳዮች ችሎት ጥር 19፤ 2013 ዓ.ም የእነ ጃዋር መሀመድን የእምነት ክደት ቃል ለመስማት ተሰይሞ የነበረ ሲሆን ተከሳሾችና ጠበቆቻቸው ባሰሙት አቤቱታ ምክንያት ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

የቀረበው አቤቱታ፤

ችሎቱ ከመጀመሩ በፊት ተከሳሾችና ጠበቆቻቸው የሚያሰሙት አቤቱታ እንዳላቸው ገልጸው የተፈቀደላቸው ሲሆን ሃሳባቸዉንም አቅርበዋል። በዚህም መሰረት አቶ ጃዋር መሀመድ ደጋፊዎቻቸው በለበሱት ልብስ ቀለም ምክንያት እንዲሁም ኦሮምኛ ተናጋሪ የሆኑ እየተለዩ ወደ ችሎት አንዳይገቡ ብሎም እየታሰሩ መሆኑን ጠቅሰው የታሰሩት እንዲፈቱ፤ ወደ ችሎት እንዳይገቡ የታገዱትም መግባት እንዲፈቀድላቸው በማለት አቤቱታ አሰምተዋል፡፡

በመቀጠልም አቶ በቀለ ገርባ ችሎቱ ለታዳሚያን ክፍት ሆኖ ሳለ ቤተሰቦቻቸው ግን በለበሱት ቢጫ ልብስ ምክንያት ወደ ችሎት እንዳይገቡ ብሎም እስራት እና እንግልት እየደረሰባቸዉ መሆኑን ጠቅሰው ሁኔታው ፍትህ የማፈን ስራ እንደሆነ በመግለጽ ፍርድ ቤቱ ቤተሰቦቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ወደ ችሎቱ እንዲገቡ እንዲፈቅድ ካልሆነ ተከሳሾችን እንደሸኛቸው ጠይቀዋል፡፡ አቶ ደጀኔ ጣፋ በበኩላቸዉ አንድን ችሎት ሙሉ ነው የሚያሰኘው ከዳኞችና ተከሳሾች በተጨማሪ የታዳሚዎች መኖር መሆኑን አስረድተው ችሎቱ ባልተሟላበት ሁኔታ ሂደቱን መቀጥል አግባቢ ስላልሆነ ችግሩ እንዲፈታ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ እንዲሰጥ በማለት አቤቱታቸዉን ያሰሙ ሲሆን አቶ ሃምዛም በተመሳሳይ መልኩ አቤቱታቸዉን አሰምተዋል። በተያያዘ መልኩ የተከሳሾች ጠበቆችም ደንበኞቻችው በተፈጠረዉ ሁኔታ መረበሻቸውን ግልጸው ለእምነት ክደት ቃል አጭር ቀጥሮ እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

የፍርድ ቤቱ ውሳኔ፤

ፍርድ ቤቱም የተከሳሾችን ቅሬታ ካዳመጠ በኋላ ማብራሪያ ሰጥቷል፡፡ ብሄር ተኮር አድሎዎች ተፈጽመው ከሆነ ስህተት መሆን እና የእርማት እርምጃዎችም እንደሚወሰዱ ገልጸዋል፡፡ ልብስን በሚመለከት በመሰረታዊነት በችሎቱ ላይ የሚያመጣው ነገር ባይኖርም የችሎቱን ነጻነት የሚጋፋ እንዲሁም ታዳሚውን ከተከሳሾች ለመለየት አዳጋች ሁኔታ የሚጥፈጥር መሆን እንደሌለበት በመግለጽ የመብት ጥሰትን በሚመለከት ግን ለሚመለከተዉ አካል ትዕዛዝ እንደሚሰጥ አብራርቷል፡፡ በተጨማሪም ተከሳሾቹና ጠበቆቻቸው ኃላፈነታቸውን እንዲወጡና እኛ ያልነዉ ብቻ ይሁን ከማለት እንዲታረሙ ችሎቱ አስገንዝቧል፡፡

ዕቃቤ ህግ በበኩሉ ቢጫ ልብስ በቤተሰቦቻቸዉና በደጋፊዎቻቸው መለበሱ ከተከሳሾች ጋር የመመሳሰል ነገር ስለሚያመጣ ለጥበቃ አዳጋች ሊሆን እንደሚችል፤ ችሎቱ ክፍት መደረጉ ፍታዊ እና ገለልተኛ ሂደት እንዲኖር እንጂ ድጋፍ እና ተቃዉሞ የሚሰማበት ሁኔታ ለመፍጠር እንዳልሆነ ጠቅሷል፡፡ በመሆኑም በየምክንያቱ ቀጠሮ የሚቀየር ከሆነ ለተከሳሾቹም ቢሆን የፍትህ መጓተትን የሚያመጣ ነው በማለት የእምነት ክደት ቃል መስማት ሂደቱ ቢቀጥል ሲል ሃሳቡን አጋርቷል። 

ፍርድ ቤቱም ለጥር 19 የቀጠረው የእምነት ክደት ቃል ለማዳመጥ ቢሆንም ችሎቱ ሙሉ አይደለም የሚለዉን ስላመነበት ቀጣይ ቀጠሮ ለጥር 27፤ 2013 ዓ.ም ሰጥቷል።

Center for Advancement of Rights and Democracy (CARD)

Making Democracy the Only Rule of Game!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *