ፍርድ ቤቱ የእነ ጃዋር መሐመድን የእምነት ክህደትን ቃል ተቀበለ

  • ጃዋር መሐመድ፤ ‘አባቴ ሙስሊም፣ እናቴ ኦርቶዶክስ ናቸው። ባለቤቴ ፕሮቴስታንት ናት። የሥራ ባልደረቦቼ ሙስሊሞችና ክርስቲያኖች ናቸው። በዚህ ሁኔታ እኔ የሃይማኖት ግጭት ባስብ እንኳን በዙሪያዬ ሊተባበሩኝ የሚችሉ ሰዎች የሉም።’
  • በቀለ ገርባ፤ ‘የኦሮሞን ሕዝብ የገደለው ነፍጠኛ ነው’ ማለታቸውን አምነው፥ ነፍጠኛ እና አማራ ይለያያል ብለዋል።
  • ሸምሰዲን ጠሀ፤ ‘የታሰርኩት ጋዜጠኛ ሳልሆን ነህ ተብዬ ነው፤ እንደታሰርኩ ስደበደብ ውያለሁ።’

መጋቢት 13፣ 2013 - ፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎቱ በቀደመው ችሎት ላይ በሐኪም ፍቃድ ያልቀረቡትን እና አስተርጓሚ የሚያስፈልጋቸውን ተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃል ለመቀበል የተሰየመ ሲሆን፣ ባለፈው ችሎት ላይ ተከሳሾች ያልቀረቡበትን ምክንያት በሚመለከት በተከላካይ ጠበቆች በኩል የሰነድ ማስረጃ ቀርቦለታል። ችሎቱ ማስረጃውን ተመልክቶ የሁለት ሳምንት እረፍት እና ተጨማሪ ምግብ ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል ለችሎቱ በማሳወቅ የፍቃዱን ሰነድ ብቻ ዐቃቤ ሕግ እንዲመለከቱ በማድግ ከዛ ዉጪ ያለውን ማስረጃ የተከሳሾቹን የሕክምና ምሥጢር ደኅንነት የሚነካ ስለሆነ በማለት ለተከላካይ ጠበቆቻቸው በመመለስ፣ ሦስቱን ተከሳሾች በሚመለከት ድካም ሊኖራቸው ስለሚችል በየተቀመጡበት የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንዲሰጡ ፈቅደዋል።

የመጀመሪያ ተከሳሽ ጃዋር ሞሐመድ ወንጀሉን ያለመፈፀማቸውን ለችሎቱ ቃላቸውን ከሰጡ በኋላ የቀረበባቸው ሦስት ክሶች ላይ ማብራሪያ አክለዋል። የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ላይ ጥቃት እንዲደርስ እና የሃይማኖት አባቶች እንዲገደሉ አድርገዋል ለተባሉት የወንጀል ክስ ከሙስሊም አባት እና ከኦርቶዶክስ እናት ተወልደው፣ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ባለቤት እንዳለቻቸው፣ አስተዳደጋቸው እና የሥራ ባልደረቦቻቸው ጭምር ገሚሱ ሙስሊም፣ ገሚሱ ደሞ ክርስቲያን በሆኑበት ሁኔታ ላይ ይህን ነገር ለመፈፀም ቢያስቡ እንኳን ሊተባበራቸው የሚችል እንደሌለ፤ እንዲሁም ከማንነታቸው እና ከአስተዳደጋቸው ጋር ፍፁም የሚቃረን መሆኑን በማውሳት፣ ይህን ድርጊት መፈፀም የራስን ግማሽ አካል ቆርጦ እንደመጣል ጭምር እንደሆነ ለችሎቱ አሰረግጠው አስረድተዋል።

ብሔር ብሔረሰቦች እርስ በርስ እንዲጋጩ አድርገዋል በማለት ለቀረበባቸው ክስ "የአማራና የኦሮሞ ሕዝብ በአገሪቷ ውስጥ ካላቸው የሕዝብ ቁጥር ብዛት ሁለቱ ብሔሮች ለአገሪቱ የተያያዙ ትልልቅ ግንድ እንደመሆናቸው፣ ሁለቱ ቢጋጩ ጥሩ እንዳልሆነ አንድ ቢሆኑ ደሞ ትልቅ ኃይል መሆን አንደሚችሉ ስላመንኩበት ባሕር ዳር ድረስ በመሔድ ሁለቱ ሕዝቦች አንድ እንዲሆኑ ብዙ ሠርቻለሁ። ኦሮማራ ለሚያቀነቅኑ ብዙ ድጋፍ አድርጊያለሁ" በማለት ብዙ ያወሱ ሲሆን መንግስትን በኃይል ለመገልበጥ ሞክረዋል ተብሎ ለቀረበባቸው ክስ "አገር ሳይፈራርስ ተምሬ ባገኘሁት ዕውቀት መሠረት ከቄሮ ጋር በኅብረት በመሆን ሰላማዊ ትግል በማድረግ ለውጥን በማምጣት አሁን ላይ ላለው ደረጃ አድርሻለሁ። ይህ የትላንት ትውስታ እንደመሆኑ መጠን ከሳሾቼም የማይክዱት እውነታ ነው፤ ይህ ክስ በእኔ አና በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ትልቅ የሥም ማጠልሸት ነው" ብለዋል።  በተጨማሪም በሕዝብ ዘንድ ትልቅ ተቀባይነት ስላላቸው እና በምርጫ ቢሳተፉም ገዢው ፓርቲ ተቀባይነት እንደማያገኙ ስጋት ስላለባቸው እና የኦሮሞ ሕዝብ እና ኦፌኮን ከምርጫ ለማስወገድ የተደረገ ክስ እንደሆነ፣ ዓላማ በዚህ ችሎት የተሳካ ይመሥላል። እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ የሐሰት ክስ ሰለባ ነን ብለዋል።

ሁለተኛ ተከሳሽ በቀለ ገርባ ለችሎቱ ወንጀለኛ ያለመሆናቸውን የቀረበባቸውም ክስ ከአስተዳደጋቸው እና ከሚከተሉት የፖለቲካ አመለካከት ጋር አብሮ የማይሔድ መሆኑን፤ በዲሞክራሲና ሐሳብን በመግለጽ ነጻነት እንደሚያምኑ የማርቲን ሉተር ኪንግ እና የማሕተመ ጋንዲ የትግል ስልት እንደሚከተሉ በማከልም፣ በኦሮሞና እና በቤንሻንጉል ሕዝቦች መሐል ባሉ ያለመግባባቶች ከአጋሮቻቸው ጋር በመሆን ሰላም አንዲፈጠር እንዳደረጉ፤ ይህን መንግሥት በሚመለከት ግን "በመጀመሪያ የነበረኝን ድጋፋ ያቆምኩት የለውጡ ሀዲድ መሥመሩን በመሳቱ እና ትምህርት ቤቶች ማዕከላዊ በመሆናቸው፣ በየአካባቢው እናቶች ማልቀስ በመጀመራቸው፣ ዲያስፖራዎች መሬት በየቦታው እየተቀራመቱ ስለሆነ እንደገና መንግሥትን በመቃወም ሕዝብ ጥያቄ እንዲያቀርብ እና ሕዝቡ በምርጫ ድምፅ እንዲቀጣቸው ለማድረግ ሰላማዊ ትግል እያደረግኩ ነው” ብለዋል። ይሄን ማድረግም መብታቸው እንደሆነ ገልጸዋል። በሁለተኛነት ለቀረበባቸው ክስ መስከረም 30 የመንግሥት የግዜ ቆይታ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ስለሚያልቅ ሕጋዊ መንግሥት የለም ማለታቸው በሕገ መንግሥቱ ተንተርሰው መሆኑን አሳውቀዋል።

በቀለ ገርባ ‘የኦሮሞን ሕዝብ የገደለው ነፍጠኛ ነው’ ብለዋል ተብሎ የቀረበባቸው ክስ እውነት መሆኑንና በታሪክ ምሁራንም በግልጽ በጽሑፍ የቀረበ ስለመሆኑ፣ ከአስተዳደጋቸው ጀምሮ እስከ አሁንም የዓይን እማኝ መሆናቸውን፣ ይህንን መናገራቸውም ወንጀልነት የሌለው ነገር  መሆኑን ገልጸዋል። ነገር ግን አማራ እና ነፍጠኛ ልዩነት እንዳለው በእርሳቸው ዕሳቤ "ነፍጠኛ ማለት ጠመንጃ ይዞ ሰውን ከሰው ደረጃ አውጥቶ ቋንቋ እና ባሕሉን ጭኖበት፣ መሬቱን ቀምቶ፣ እኔ የሰው ውሃ ልክ ነኝ በማለት የኖረ ስርዓት ነው" በማለት የሐሰት ውንጀላ ነው የቀረበብኝ ሲሉ ተደምጠዋል።

ሦስተኛ ተከሳሽ ሀምዛ ቦረና ወንጀሉን እንዳልፈፀሙ፣ የተከሰሱትም ለመጀመሪያ ግዜ እንደሆነ፣ የቀረበባቸው ውንጀላ መሠረት እንደሌለው፣ ምክንያቱም "ስወለድ ራሴን ያገኘሁት ኦርቶዶክስ ሆኜ ነው፤ መላው ቤተሰቤም አሁን ላይኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች ናቸው። ስለዚህ እነርሱ እንዲጎዱ ቅስቀሳ ማድረግ ምን ማለት እንደሆነ ለፍርድ ቤቱ ትቼዋለሁ" በማለት መንግሥት ያሰረኝ የኦፌኮ አባል ስለሆንኩ ነው ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል።

ዘጠነኛ ተከሳሽ ዓለማየሁ ገለታ ወንጀሉን እንዳልፈፀሙ እና ጥፋተኛ እንዳልሆኑ ቃላቸውን ሰጥተዋል።

13ኛ ተከሳሽ ሸምሰዲን ጠሀ ወንጀለኛ እንዳልሆነ እና ምንም እንኳን ጋዜጠኛ ባይሆንም የታሰረው ግን ጋዜጠኛ ነህ ተብሎ እንደነበር፣ በታሰረበት ቀን ቀኑን ሙሉ ስደበደብ ውዬ ነበር የቀድሞ ዐቃቤ ሕግ መተው አይተውኛል። ሕክምናም ተደርጎልኛል። የታሰርኩትም ለምን እንደሆነ አላውቅም። በዚህ ቦታ እኔ ሳልሆን ከሳሾቼ ነበሩ መቆም የነበረባቸው" በማለት አክለዋል።

በተከላካይ ጠበቆች በኩል ከ 3-24 ያሉ ተከሳሾች ክሳቸው ዋስትና የማያስከለክላቸው ስለሆነ ዋስትና እንዲሰጣቸው የጠየቁ ሲሆን ችሎቱም መጋቢት 22 የማረሚያ ቤቶች ኃላፊ በሕክምናው ላይ በነበረው ችግር መልስ ለመመለስ ስለሚቀርቡ በዛኑ ዕለት ውሳኔ እንደሚሰጣቸው ተናግሯል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩላቸዉ በሚቀጥለው ችሎት ምስክር ከመጋረጃ ጀርባ ማቅረብ እንዲፈቀድላቸው የጠየቁ ሲሆን፣ ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ሕግን ጥያቄ በሚመለከት ውሳኔ ለመስጠት መጋቢት 28 የቀጠሩ ሲሆን መጋቢት 29 እና ተከታዮቹን ቀናቶች ደሞ የመጀመሪያ ዙር ምስክር የሚሰማበት ግዜ ነው ሲሉ ውሳኔ አሳልፈዋል።

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.