በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች በድጋሚ ሳይቀርቡ ቀሩ

ታኅሣሥ 15፣ 2014 - የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በእነ እስክንድር ነጋ ላይ ቀሪ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ለመስማት የተሰየመ ቢሆንም ምስክሮች ሳይቀርቡ ቀርተዋል።

ይህን ተከትሎ ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ምስክር ፍፁም ከተማን በፖሊስ ጥሪ መቅረብ ስላልቻለ ታስረው እንዲቀርቡ ፍርድ ቤቱ በድጋሚ እንዲያዝላቸው እና አጭር ቀጠሮ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፤ ምስክር ተስፋዬ ይማምን በሚመለከት ግን በተደጋጋሚ ፈልጎ ለማቅረብ የተሞከረ ቢሆንም ሊገኙ ስላልቻሉ ከዚህ በኋላ ቢፈለጉም ይገኛሉ የሚል ግምት ስለሌለን ፍርድ ቤቱ ይህን ምስክር ይታለፍልን ብሏል።

ተከላካይ ጠበቆችም ዐቃቤ ሕግ ባቀረቡት ሐሳብ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ በችሎቱ በታዘዘው መመረት፥ በዐቃቤ ሕግ በኩል ይታለፍ የተባለው ምስክርን በሚመለከት የተለየ ሐሳብ እንደሌላቸው እና እንደሚስማሙ ነገር ግን ታስረው ይቅረብልን ባሉት ምስክር የፌዴራል ፖሊስ አስሮ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም ግን አላቀረባቸውም። ፖሊስ ዛሬ በደብዳቤ ለችሎቱ ባቀረቡት መልስ መሰረት ምስክሩ በሥራ ቦታቸው ላይ እንደሌሉ እና  አጎታቸው ሞቶ ክፍለ አገር እንደሔዱ ገልጸዋል። ምስክሩን ማቅረብ ቢፈልጉ ለቅሶ ሔደ ከተባለበት አስሮ ማቅረብ ይችሉ ነበር፤ ስለዚህ ዐቃቤ ሕግ እና ፖሊስ በመመሳጠር ሆን ብለው ያደረጉት ነገር ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ደንበኞቻችን እስከመቼ ይታሰሩ የሚለውን ግዜ ዐቃቤ ሕግ ያቀደበት ስለሆነ እስከዛ ድረስ በምክንያት ታስረው እንዲቆዩ እያደረገ ነው ሲሉ ችሎቱ ተለዋጭ ቀጠሮ ሊሰጥ አይገባም ብለዋል።

ዐቃቤ ሕግ በተነሳው ሐሳብ ላይ በራሳችን ምስክር ላይ ታስረው ይቅረቡ እያልን ትዕዛዝ እያሰጠን በተቻለ መጠን መዝገቡ እንዲፈጥን እያደረግን ነው። የቀረበው አቤቱታ ቅንነት የጎደለው ነው ሲሉ በጠበቆች በተነሳው ሐሳብ ላይ ምላሽ ሰተዋል።

በመዝገቡ ሦስተኛ ተከሳሽ የሆኑት ወ/ሮ ቀለብ ሥዩም በበኩላቸው በዚህ ጉዳይ ላይ እስከመቼ ቀጠሮ ይሰጣል? ከዚህ በኋላ ወደ ቀጣይ ሒደት ማለፍ አለብን፣ የተፋጠነ ፍትሕ ማግኘት እንፈልጋለን በማለት ለፍርድ ቤቱ አቤቱታ አቅርበዋል።

ባለፈው ችሎት እስክንድር ነጋ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ከአገር ውጪ የሚገኙ ቤተሰቦቼን በሳምንት አንድ ቀን ጌዜ በስልክ እንዳገኛቸው የታዘዘውን ትዕዛዝ አልፈፀመልኝም ሲሉ አቤቱታ አቅርበው እንደነበር ይታወሳል።

ፍርድ ቤቱም ትዕዛዝ ለምን እንዳልተፈፀመ የማረሚያ ቤቱ የእስረኞች ኃላፊ ቀርቦ እንዲያስረዱ አዘው ነበር።

በዛሬው ችሎት ምክትል ኮማንደር በለጠ ሞገስ በማረሚያ ቤት የቀጠሮ ታራሚዎች ፍትሕ አስተባባሪ በትላንትናው ዕለት የፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ተፈፃሚ እንደተደረገ ቀርበው ለችሎቱ ገልጸዋል።

እስክንድር ነጋ ከዚህ በፊት በሌላ ታራሚ ደረሰብኝ ያሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን አጣርቶ ሪፖርት እንዲያደርግ በፍርድ ቤቱ መታዘዙ ይታወሳል። ይህንን ተከትሎ ኮሚሽኑ አጣርቶ በዛሬው ችሎት ለፍርድ ቤቱ በደብዳቤ አቅርቧል። የግራ ቀኙን ክርክር የሰማው ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕግ ይታለፍ ያለውን ምስክር በዐቃቤ ሕግ ጥያቄ መሰረት መታለፉን እና ቀሪ ምስክርን በሚመለከት እንዲሁም ከኮሚሽኑ የመጣው ደብዳቤ ላይ ትዕዛዝ ለመስጠት ለታኅሣሥ 22፣ 2014 ቀጠሮ ሰጥተዋል።

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.