አሳሳቢ የጥላቻ ገለጻዎች በአሜሪካ በሚገኙ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት

ካርድ በሕዳር 2012 አክቲቪስት እና የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ጃዋር መሐመድ የአሜሪካ ጉብኝት ሲያደርግ የገጠሙትን የተቃውሞና ድጋፍ ሰልፎችን የሚያሳዩ ዘጠኝ የዩቱዩብ ቪዲዮዎችን በጥንቃቄ ተመልክቷል። ቪዲዮዎቹ በስድስት የአሜሪካ ከተሞች ማለትም ዋሽንግተን ዲሲ፣ ሲያትል፣ አትላንታ፣ ሚኒያፖሊስ፣ ላስ ቬጋስ እና ዴንቨር የተካሔዱ ሰልፎችን የሚያሳዩ ናቸው። ጃዋር መሐመድን ሊቃወሙ ሰልፍ የወጡ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ጃዋርን ሊደግፉ ከወጡ የኢትዮጵያ ዳያስፖራዎች ጋር ፊት ለፊት የተጋፈጡ ሲሆን፥ እርስ በርስ እና ምናልባትም የመጡበትን ብሔር የሚፈርጁ የጥላቻ ገለጻዎችን ሲጠቀሙ ተስተውለዋል።

የሰልፎቹ መነሻ

ጥቅምት 12፣ 2012 - ጃዋር መሐመድ በፌስቡክ ገጹ የመንግሥት ኀላፊዎች የመደቡለትን የጥበቃ ጓዶች በሌሊት ሊያነሷቸው እና ለደቦ ፍርድ ሊያጋልጡት አንደሆነ ከገለጸ በኋላ፥ በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች አመፅ ተቀስቅሶ ነበር። ለቀናት በዘለቀው በዚህ አመፅ 86 ያህል ሰዎች እንደተገደሉ መንግሥት ይፋ አድርጓል። የበይነመረብ መብት አክቲቪስቶች ጃዋር በፌስቡክ ያሰፈረው ጽሑፍ እና ከዚያም በኋላ በሚመራው የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ ያስተላለፋቸው መልዕክቶች ለአመፁ እና ለንፁኀን ዜጎች መገደል ተጠያቂ ነው በሚል ይወቅሱታል። ይህንን ተከትሎ የአሜሪካ ዜግነት ያለው ጃዋር መሐመድ ወደ አሜሪካ ተጎዞ በቀጣዩ የኢትየጵያ ምርጫ እንደሚሳተፍ አሳውቋል። በአሜሪካ ከተሞች እየተዘዋወረ ደጋፊዎቹን በማነጋገር ላይም ነው። የጃዋር መሐመድ ተቃዋሚዎችም በበኩላቸው ጃዋር በሚንቀሳቀስባቸው ከተሞች በመገኘት ሰልፎችን ያደረጉ ሲሆን “በዘር ማጥፋትም” ወቅሰውታል። የጃዋር ተቃዋሚዎች ከጃዋር ደጋፊዎች ጋር ፊት ለፊት የተፋጠጡ ሲሆን እርስ በርስ የጥላቻ ገለጻዎች የተሞሉ ምልልሶችን ሲያደርጉ እንደነበርም ቪዲዮዎቹ ያሳያሉ።

የጥላቻ ገለጻዎቹ ስርጭት

ምንም እንኳን ሰልፎቹ ባብዛኛው ፖለቲካዊ አንደምታ ብቻ ባላቸው መፈክሮች የተሞሉ ቢሆኑም ሁሉም ሰልፎች ላይ ሊባል በሚችል መልኩ የተወሰኑ ቡድኖች የጥላቻ ገለጻዎችን የተጠቀሙ ከመሆኑም ባሻገር፣ እነዚህ ገለጻዎች የተለየ ተመልካች አግኝተው በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሲዘዋወሩ ነበር። አንዳንዶቹ እስከ 400 ሺሕ ተመልካች አግኝተዋል። በተመሳሳይ የጃዋር መሐመድ ደጋፊዎች ለጃዋር ተቃዋሚዎች ሰልፎችን አድርገዋል። በሁለቱም ወገን የተሰለፉት ውስጥ ያሉ ቡድኖች እንደ “ጋላ” እና “ነፍጠኛ” ያሉ አስነዋሪ እና ፖለቲካዊ መልዕክት ያላቸው ቃላቶችን ኦሮሞ ናቸው ብለው ያመኗቸው የጃዋር ደጋፊዎች እና አማራ ናቸው ብለው ያመኗቸው የጃዋር ተቃዋሚዎች ላይ ሲወራወሩ ነበር። ከነዚህ ቃላት በተጨማሪም “መንጋ”፣ “አሸባሪ”፣ “ዘር ጨፍጫፊ” የመሳሰሉ እና ቄሮ የሚባሉት የኦሮሞ ወጣቶችን እና የኦሮሞ ተወላጆችን በጥቅሉ ዒላማ ያደረጉ ፍረጃዎች በሰልፎቹ ላይ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል። ቪዲዮዎቹ እና ተቆርጠው ከመሐላቸው የወጡ አጫጭር ክሊፖች በፌስቡክ እና ዩቱዩብ ላይ አንዳንዴ በውግዘት ሌላ ጊዜ ደግሞ በማበረታታት ሲጋሩ ተስተውሏል።

አስፈላጊ ጥንቃቄዎች!

ካርድ - እንደዚህ ያሉ የጥላቻ ገለጻዎች በሚሰራጩበት ጊዜ አገር ውስጥ በአጭር ይሁን በረዥም ጊዜ ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ ግጭት ሊቀሰቅሱ እንደሚችሉ ይረዳል። በመሆኑም፣ ለወደፊት እንዲህ ዓይነት የተቃውሞም ይሁን የድጋፍ ሰልፎችን የሚያዘጋጁ ሰልፈኞች መፈክሮቻቸውን በጥንቃቄ እንዲቀርፁ እና የጥላቻ ገለጻዎችን የሚጠቀሙ ሰልፈኞች ሲገኙ አስተባባሪዎቹ በአስቸኳይ እንዲያስቆሟቸው ይመክራል። በተጨማሪም፣ የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች የጥላቻ ገለጻዎችን ከማጋራት እንዲቆጠቡ ያሳስባል።

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.