እነ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሀምዛ አዳነ እና ደጀኔ ጣፋ ፍርድ ቤት አንቀርብም ማለታቸውን ማረሚያ ቤቱ በጽሑፍ አሳወቀ

ሰኔ 29፣ 2013፤ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የፀረ ሽብር እና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ቀጠሮ የያዘው የምስክር አሰማም ሒደት ላይ የቃል ክርክር ለማድረግ ቢሆንም እንኳን ጃዋር መሐመድ እና ሌሎችም አራት ተከሳሾች በቀጠሮው ቀን አንቀርብም ማለታቸውን ማረሚያ ቤቱ በጽሑፍ ምላሽ ሰጥቷል።

 

የተቀሩት 8 ተከሳሾችን በተመለከተ ባለፈው ችሎት በሕክምና ምክንያት እንዳልቀረቡ ማረሚያ ቤቱ ምላሽ የሰጠ ቢሆንም፥ ፍርድ ቤቱ ለምን እንዳልቀረቡ ተከሳሾች በተናጥል የጠየቃቸው ሲሆን ሦስት ተከሳሾች ለሕክምና ቀጠሮ ስለነበረን እና የችሎቱ ቀጠሮ በማረሚያ ቤቱ ስላልተነገረን አልቀረብንም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

 

ሸምሰዲን ጠሀን ጨምሮ ሁለት ተከሳሾች ደግሞ  የቀጠሮ ሰዓት ካለፈ በኋላ ነው ማረሚያ ቤቱ እንድንወጣ የነገረን፤ በዕለቱም የሀጫሉ አንደኛ የሙት ዓመት እያከበርን በመሆኑ አልወጣንም ብለዋል።

 

ፍርድ ቤቱም ማረሚያ ቤቱ ተከታትሎ ቀጠሯቸውን ማሳወቅና ማቅረብ እንዳለበት አብራርቶ፥ ለሌላ ግዜ እንዳይደገም የቃል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል። በተጨማሪም ምክንያት ያቀረቡ ተከሳሾች የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማክበር እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

 

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ተከሳሾች በፍላጎታቸው የፍርድ ቤት ትዕዛዝን ሳይቀበሉ መቅረብ ባልፈለጉበት ሁኔታ በጠበቆቻቸው ተወክለው ምላሽ ሊሰጡ አይገባም ሥነ ስርዓታዊ አይደለም ሲል አቤቱታ አሰምቷል።

 

ተከላካይ ጠበቆች በበኩላቸው ተከሳሾችን ባናገርናቸው መሠረት ደንበኞቻችን ፍርድ ቤት የስርዓቱ አካል ነው፣ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በአስፈፃሚው አካል እየተጣሰ ስለሆነ ባለንበት በሰላም ብንቆይ ይሻለናል የሚል ምላሽ ሰተውናል ሲሉ ጠበቆቹ በቃል እና በጽሑፉ ምክንያታቸውን ለችሎቱ አቅርበዋል።

 

ጉቱ እና ቦና የተባሉት ተከሳሾች በበኩላቸው “የታሰርንበት ጉዳይ ፖለቲካዊ ነው፤ እዚህ መቅረባችን መፍትሔ አላስገኘም” በማለት አቤቱታ አሰምተዋል። ፍርድ ቤቱም እዚህ እየመጣችሁ ለሚዲያ ፍጆታ በሚል ያልተገቡ ንግግሮችን ባትናገሩ ተገቢ ነው ሲል ምላሽ ሰጥቷል። በተጨማሪም እነ ጃዋር ያቀረቡት ምክንያት ተቀባይነት እንደሌለው ፍርድ ቤቱ አክሎ ገልጿል።

 

ፍርድ ቤቱ “በተቻለ መጠን መብቶቻችሁን ለማስከበር ጥረት እያደረግን ነው። በዚህ ረገድ መፍትሔ ያላገኛችሁበት ጉዳይ አለ ብለን አናምንም። ቀጠሮ በተለያዩ ምክንያቶች እያጓተታችሁ ነው” በማለት ቀጣይ ቀጠሮ ለሐምሌ 21፣ 2013 ማረሚያ ቤቱ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሀምዛ አዳነ እና ደጀኔ ጣፋን እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ባለፈው ቀጠሮ እነጃዋር መሐመድ ለፍርድ ቤቱ የጻፉትን ደብዳቤ እዚህ ማተማችን ይታወሳል።

 

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.