ኦሮሚያ፦ በ12-12-12 ምን ተፈፀመ?

በውብሸት ታዬ (ለካርድ)

ሰኔ 21 ቀን 2012 የአፋን ኦሮሞ ሙዚቃ አቀንቃኝና በአድናቂዎቹ እንደ ታጋይ የሚቆጠረው አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ምሽት 3፡00 አካባቢ አዲስ አበባ ውስጥ በጥይት ተመቶ ተገደለ። ይህን ተከትሎም ከቀጣዩ ቀን ጀምሮ በመላው ኦሮሚያ በተቀሰቀሰው ነውጥ የዜጎች ሕይወት መቀጠፍና ከፍተኛ የንብረት ውድመትና ደርሷል። በምላሹ በመንግሥት በኩል በርካታ የተቃዋሚ አመራሮች፣ ወጣቶች፣ ጋዜጠኞች እና የፀጥታ አካላትም ጭምር ለእስር ተዳርገዋል።

በዚህም ከ9000 ሺሕ በላይ ተጠርጣሪዎች ታስረዋል በሚባልበት ጉዳይ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ጋዜጠኞች፣ አክቲቪስቶችና በሌሎች ዘርፎች ውስጥ የሚሰሩ ዜጎች የሚገኙበት ሲሆን በተለይ የኦፌኮ አመራር አባል የሆኑት ጃዋር መሐመድ ደጋፊዎች መሪያቸው በአስቸኳይ እንዲፈታ ሲጠይቁ ቆይተዋል።

ከ12/12/2012 - 20/12/2012

ከቀኑ መገጣጠም ጋር እንዲያያዝ በሚመስል መልኩ በኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ከነሐሴ 12 ቀን 2012 እስከ ነሐሴ 20/2012 የሚቆይ አጠቃላይ የተቃውሞ ጥሪ “የኦሮሚያ ቄሮ ጠርቷል” በሚል በመላው ኦሮሚያ የተቃውሞ ሰልፍ እንዲደረግ በውጭ የሚገኙ ዕውቅ ሰዎች በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ (OMN) በኩል ጥሪ አስተላልፈዋል።

የተቃውሞው መግለጫው ይዘት

ይህ በ“ኦሮሚያ ቄሮ” ተላልፏል በሚል የተሰጠው መግለጫ ይዘት ከ12/12/2012 ጀምሮ ለስምንት ቀናት በተከታታይ የሚቆይ በመላው ኦሮሚያ የሚደረግ ተቃውሞና በተለይ ወደ ዋና  ከተማዋ የሚገቡ መንገዶችን በመዝጋት የትራስፖርትና መሰል እንቅስቃሴዎችን ማቆም የሚሉ ነበሩ።

የመንግሥት ግብረ መልስ

ይህን በኦሮሚያ ቄሮ ተጠራ የተባለውን አጠቃላይ የተቃውሞ ጥሪ ተከትሎ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ በተባለው ቀን የተፈቀደ ምንም ዓይነት ሕጋዊ ሰልፍ ባለመኖሩ ማኅበረሰቡ መደበኛ ተግባሩን እንዲያከናውን ካሳሰበ በኋላ፣ ይህን ተላልፈው በሚገኙ አካላት ላይ አስፈላጊውን የሕግ ማስከበር እርምጃ እንደሚወስድ ገለጸ። የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ በኦሮሚያ ቄሮ ሥም ጥሪውን ያደረጉት የራሳቸው ድብቅ አጀንዳ ያላቸው ቡድኖች በመሆናቸው በድርጊቱ ማንም እንዳይሳተፍ ሲል አስጠነቀቀ።

በ12/12/2012 የተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች

በኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክና በተለያዩ የማኅበራዊ ትሥሥር ገጾች አማካይነት የተላለፈውን ጥሪ ተከትሎ በበርካታ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የተቃውሞ ሰልፎች ተካሂደዋል። በተለይ የጃዋር መሐመድ እና የኦፌኮ ደጋፊዎች በስፋት ይገኙባቸዋል በሚባሉት ሁለቱ የሐረርጌ ዞኖች (ምሥራቅና ምዕራብ ሀረርጌ)፣ ምዕራብ አርሲ (በተለይም ገደብ አሳሳ፣ ዶዶላ፣ አዳባ፣ ዋቤ፣ ኮፈሌና፣ ሻሸመኔ)፣ ምዕራብ ወለጋና በሌሎች አንዳንድ ቦታዎች የተለያየ መጠን ያላቸው የተቃውሞ ሰልፎች ተደርገዋል።

የተቃውሞ ሰልፍ ዓላማ ምን ነበር?

ከተጠቀሰው ቀን ጀምሮ እንዲካሔድ በሚል የተጠራው ሰልፍ ዓላማ ምን እንደነበር ጥሪው ከተላለፈባቸው ሚዲያዎችና የመረጃ ምንጮች ለማረጋገጥ እንደተቻለው የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ ለእስር የተዳረጉት ጀዋር መሐመድና የትግል አጋሮቻቸው እንዲፈቱ፣ በተመሳሳይ በመላው ኦሮሚያ በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት የታሰሩ የኦሮሞ ተወላጆች በአስቸኳይ ይፈቱ የሚል ነበር።

የደረሱ ጉዳቶች ዓይነትና መጠን

እንደ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና መሰል የሰብአዊ መብት ተሟጋች ተቋማት ሪፖርት በዕለቱ የተቃውሞ ሰልፍ ከተደረገባቸው የኦሮሚያ አካባቢዎች በአንዳንዶቹ መንግሥት በወሰደው ከመጠን ያለፈ ኃይል፤ የሰዎች ሕይወት ያለፈ ሲሆን እስርና ድብደባ ስለመፈፀሙ ተገልጧል። ከሰብኣዊ መብት ተቋማት በተጨማሪ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የማኅበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶችም ስለጉዳቱ በስፋት ገልጸዋል። የደረሰውን የሕይወት መጥፋት መጠን አስመልክቶ ለተሰጠው ሪፖርት በምላሹ በኦሮሚያ ክልል የአስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ጅብሪል መሐመድ የሰብአዊ መብት ተቋማቱ መግለጫ የተሳሳተ እንደሆነ ጠቅሰው መንግሥት የወሰደው እርምጃ ተመጣጣኝ ነው ሲሉ አስተባብለዋል።

ዝርዝር መረጃዎች

ከላይ የተጠቀሱትን መረጃዎችና ጥቆማዎች መነሻ በማድረግ ችግሩ ተከስቶባቸዋል በተባሉባቸው አካባቢዎች የሚገኙ የተለያዩ ግለሰቦችን በማነጋገር ቀጥሎ ያለውን ዘገባ ለማቀናጀት ሞክረናል።

ሀ) ሁለቱ የሐረርጌ ዞኖች

ሥራቅ ሐረርጌ

አወዳይ

በምሥራቅ ሐረርጌ የአወዳይ ከተማ ነዋሪና በንግድ ሥራ እንደሚተዳደሩ የገለጹልን ዑስማን ሰይድ ሐጅ አደም “12/12/12 በሚል ለተሰየመው የተቃውሞ ጥሪ ምክንያት የሆነው የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በሺሕ የሚቆጠሩ ቄሮ እና ቀሬዎች (ወጣት የኦሮሞ ወንድና ሴቶች) እንዲሁም የኦፌኮ አባልና የፖለቲካ ተንታኝ የሆኑት ጃዋር መሐመድና የትግል አጋሮቹ ስለታሠሩ እንዲፈቱ ለመጠየቅ ነበር” ካሉ በኋላ በአወዳይ ከተማ ሰልፉን ያካሔድነው ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ነበር ብለዋል።

ዑስማን ሰልፉ በሰላማዊ መንገድ መካሔድ እንደጀመረ ከክልሉ ፖሊስ በተጨማሪ የመከላከያ ሠራዊትና ከፍተኛ መጠን ያለው የኦሮሚያ ልዩ ኃይል በመጣመር በሰልፈኛው ላይ ተኩስ ከፈቱ ሲሉ ይገልጻሉ።

በተኩሱም በወቅቱ ስድስት ሰዎች መገደላቸውንና ሦስቱ ደግሞ ሆስፒታል ከደረሱ በኋላ በሁለት ቀን ልዩነት ሕይወታቸው ማለፉን ገልጸዋል። የመቁሰል ጉዳት የደረሰባቸውን ሰልፈኞች በተመለከተም ታናሽ ወንድማቸው ወጣት ከድር ሰይድ ሐጅ አደምን ጨምሮ ቁጥራቸውን የማያውቁት በርካታ ሰልፈኞች ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል። ሌላው ዑስማን ያነሱት ነጥብ በዕለቱ በሰልፍ ያልተሳተፉና በመንገድ ላይ የተገኙ ሰላማዊ መንገደኞች ሳይቀሩ የዘፈቀደ ድብደባና ማሸማቀቅ ተፈፅሞባቸዋል፤ እንዲሁም በርካቶች በትምህርት ቤት ክፍሎች ውስጥ በተጨናነቀ ሁኔታ ታጉረው ታስረዋል ብለዋል።

ሐረማያ

ሌላው የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የሐረማያ ከተማ ነዋሪ የሆኑትና ዕድሜያቸው 65 እንደሆነ የገለጹልን ሼሕ አብዱረሐማን ኢብራሂም በ12/12/12 ተፈፀመ ያሉትን የሰብአዊ መብት ጥሰት የገለጹት “በዘመነ ወያኔ እንኳ ገጥሞን የማያውቅ” በሚል ሲሆን የኦሮሚያ ልዩ ኃይልና መከላከያ ሠራዊት በሰላማዊ ሰልፈኛው ላይ በከፈቱት ተኩስ የሞቱና የቆሰሉ እንዳሉ አውቃለሁ ብለዋል።

ሼህ አብዱረሕማን በወቅቱ በሰልፉ ለመሳተፍ በከተማዋ ዙርያ ከሚገኙ የተለያዩ ቦታዎች ከመጡት ሰልፈኞች ውስጥ በከተማዋ ሰባት ሰዎች መገደላቸውን መስማታቸውን ጠቁመው እሳቸው ግን በከተማዋ እንደሚኖሩ የሚያውቋቸው ሦስት ሰዎች ስለመገደላቸው እንደሚያውቁ ገልጸዋል። ቁጥሩ የማይታወቅ የከተማዋ ወጣት መታሰሩና እስካሁን ቤተሰብ ምግብና ውሃ እንኳ ማቀበል እንዳልቻለም ተናግረዋል።

ድሬዳዋ

የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪ የሆኑትና የመጀመርያ ሥማቸውን ማለትም “ኒማ” ይበቃል ያሉን የዓይን ምስክር ደግሞ የተቃውሞ ሰልፉ ከተጠራ በኋላ በርካታ መጠን ያለው የመከላከያ ሠራዊት የከተማዋ መግቢያ በሆነው “ሀይስኩል” ተብሎ የሚጠራው አካባቢ እንደሰፈረና ሰልፉ ከመጀመሩ ጥቂት ቀደም ብሎ ጀምሮ ወታደሮቹ የሚጠራጠሯቸውን ወጣቶች ያለምንም ጥያቄ ክፉኛ መደብደብ በመጀመራቸው አስቀድሞ ለተቃውሞ የተዘጋጀው ሕዝብ ወደባሰ ቁጣ ገብቷል ያሉ ሲሆን የመከላከያና የልዩ ኃይል አባላቱ አዲስ ከተማ፣ ለገሃሬ እና ሳቢያን አካባቢ ያገኟቸውን ወጣቶች በጅምላ እያፈሱ ‘ሀይስኩል’ ተብሎ በሚጠራው ሰፈር ባለው የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ክፍሎች ውስጥ ማጎር ጀመሩ ሲሉ አስታውሰዋል። እንደ ኒማ አባባል በዕለቱ ሁለት ወጣቶች የተቃውሞ ሰልፍ ሲደረግ የተገደሉ ሲሆን ሌላ አንድ ጎልማሳ ደግሞ በ15/12/2012 ምሽት 2፡30 ሰዓት ላይ ፖሊስ እንዲቆም ሲጠይቀው ትዕዛዝ አልተቀበለም በሚል ተተኩሶበት ታፋው ላይ ከተመታ በኋላ ሕክምና ባለማግኘቱ በቀጣዩ ቀን ረፋድ ላይ ማረፉን አውቃለሁ ብለዋል። ኒማ ጨምረውም ሐረር ከተማ ያለ ወንድማቸውን ዋቢ በማድረግ ሐረር ከተማ ውስጥ በዕለቱ በተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ሁለት ሰዎች መሞታቸውንና አራት የሚያውቋቸው ሰዎች በጥይት ተመተው የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ደርሶባቸዋል ብለዋል።

ቀርሳ

በምሥራቅ ሐረርጌ ቀርሳ ነዋሪ የሆኑና ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የ38 ዓመት ጎልማሳና የአንደኛ ደረጃ መምህር ደግሞ በከተማቸው የተደረገው ሰልፍ ሰላማዊ እና ከአርቲስት ሀጫሉ ግድያ ማግስት የታሰሩ የኦሮሞ ተወላጆችና እነ ጃዋር እንዲፈቱ መጠየቅ ቢሆንም ምንም መሳርያ በእጃቸው ያልያዙ ሰልፈኞች በተከፈተባቸው ተኩስ አንድ ባልና ሚስትን ጨምሮ ሁለት ወጣቶች (እድሜያቸው 18 እና 21 ናቸው ብለዋል) ተገድለዋል ያሉ ሲሆን፥ ከዚያ ዕለት ጀምሮ የዘፈቀደ እስርና የሰብአዊ መብት ጥሰት የተለመደ መሆኑ የነዋሪውን ማኅበራዊ ሰላም እንዳደፈረሰው ገልጸዋል።

ምዕራብ ሐረርጌ

በምዕራብ ሐረርጌ የተለያዩ ከተሞች ውስጥ በ12/12/2012 ከንጋቱ ጀምሮ የተቃውሞ ሰልፍ መደረጉንና ተቃውሞውን ተከትሎ በክልሉ ልዩ ኃይል እና በክልሉ ፖሊስ ቅንጅት በተቃዋሚዎቹ ላይ በተወሰደ እርምጃ የንጹሐን ሕይወት ማለፉንና የቆሰሉ እንዳሉም ያነጋገርናቸው የዓይን ምስክሮች ገልጸዋል።

ጭሮ

ነዋሪነታቸው በጭሮ ከተማ የሆኑትና የኦፌኮ አባል መሆናቸውን የነገሩን ሙሉጌታ ኤባ “በዕለቱ በጭሮ እንዲካሔድ ለታሰበው የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ የሚጠይቅ ሰልፍ ሰልፈኛው የሌሎችን ሰላም የሚያደፈርስ ምንም ዓይነት ድርጊት እንዳይፈጸም አስቀድሞ ተሰርቶ ነበር” ካሉ በኋላ በፀጥታ ኃይሎች የተወሰደው እርምጃ ግን በተቃራኒው ንጹኃንን ለሕልፈት ዳርጓል ብለዋል። በጸጥታ ኃይሎች በተከፈተው ተኩስም አንዲት እናት የተገደሉ ሲሆን ሰልፉ ውስጥ ያልነበረ ሌላ የ23 ዓመት ወጣትም በዕለቱ ተገድለዋል ብለዋል። ከሰላሳ የማያንሱ ሰልፈኞች ደግሞ በጥይት ተመተው የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ደርሶባቸዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ጡሎ

ሙሉጌታ በዕለቱ በቦታው ባይኖሩም ጡሎ ከተማ ውስጥ ይኖር የነበረና የሚያውቁት አሳንቲ አሊይ የተባለ ወዳጃቸው መገደሉ እንደተነገራቸውና ከቤተሰብ እንዳረጋገጡም ገልጸዋል።

ገለምሶ

ሌላው ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የገለዋሶ ከተማ ነዋሪ ናስር ኑሩ የሚባል የሚያውቁት ሰው በጥይት ተመቶ ከአካባቢው ነዋሪዎች ጋር በመሆን ወደ ሕክምና ሊወስዱት ቢሞክሩም ሕክምና ቦታ ከመድረሱ በፊት ሕይወቱ አልፏል ብለዋል።

ምዕራብ አርሲ ዞን

ገደብ አሳሳ

በምዕራብ አርሲ ገደብ አሳሳ ነዋሪ የሆኑትና የባንክ ሠራተኛ መሆናቸውን የገለጹልን ዋሬዋ ገልገሉ “በ12/12/2012 በዞኑ ውስጥ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር የተሳተፈበት የተቃውሞ ሰልፍ የተካሄደው በአሳሳ ከተማ ነበር” ካሉ በኋላ ስለሰልፉ ዓላማ ሲገልጹ “ፍፁም ሰላማዊና የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ የሚጠይቅ ቢሆንም በዕለቱ የክልሉ ልዩ ኃይል በሰልፈኞች ላይ በከፈተው ተኩስ በቅርብ የማውቃቸው ሦስት ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች የሆኑ ወጣቶች ተገድለዋል” ብለዋል። ዋሬዎ እንደሚሉት ከአሳሳ 10 ኪሎ ሜትር ላይ ርቃ በምትገኘው በባሌና በአርሲ ድንበር ላይ ባለችው ዋቤ ከተማም በተመሳሳይ ሁኔታ 20 ዓመት ያልሞላው አንድ ወጣት መገደሉን አውቃለሁ ብለዋል።

ሻሸመኔ

የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪ የሆነችና ማንነቷ እንዲገለጽ ያልፈለገች አንዲት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ በዕለቱ ስለሆነው ስትገልጽ “ከአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ የወንጀል ድርጊታቸው ሳይጣራ በርካታ ወጣቶች እየታፈሱ ይታሰሩ ስለነበር ያንን ለመቃወምና እነ ጃዋር መሐመድ እንዲፈቱ ለመጠየቅ ነበር የወጣነው” ካለች በኋላ በዕለቱ የመከላከያ ሠራዊት ዩኒፎርም የለበሱና የክልሉ ልዩ ኃይሎች በሰልፈኛው ላይ ከባድ ድብደባ ፈጽመዋል፤ በዚህም ሁለት ወጣቶች ቆስለዋል እንዲሁም አንድ ወጣት ተገድሏል ብላለች። በተቃውሞ የተዘጋው መንገድ በቀጣዩ ቀን ቢከፈትም እስርና ድብደባው ግን አሁንም መቀጠሉን ተናግራለች።

ምዕራብ ወለጋ

ቢላ

በ12/12/12 የተቃውሞ ሰልፍ ከተደረገባቸው የወለጋ ዞኖች አንዱ ምዕራብ ወለጋ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን አነስተኛ ከተማ በሆነችው ቢላ ከተማ ነዋሪ የሆኑና ማንነታቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ ጎልማሳ በአከባቢያቸው ቀደም ሲል ጀምሮ ፖለቲካዊ እስርና ያልታወቁ ግድያዎች እንደነበሩ አስታውሰው በተጠቀሰው ዕለት በተጠራው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ በተሳተፉ በርካታ ሰዎች ላይ ድብደባ፣ በጥይት መቁሰልና የገፍ እስር የተፈፀመ ሲሆን አንድ ሰውም ተገድሏል ብለዋል። የሰልፉ ዓላማ በእስር ላይ የሚገኙ የፖለቲካ አመራሮች እንዲፈቱ የሚጠይቅና በሰላማዊ መንገድ የተካሔደ እንደነበርም ጠቁመዋል።

ማጠቃለያ

በ12/12/2012 በመላው ኦሮሚያ ተጠርቶ የነበረውና ከአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ የታሰሩ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ጋዜጠኞችና አክቲቪስቶች እንዲሁም ሌሎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ታስረዋል የተባሉ ዜጎች እንዲፈቱ የሚጠይቅ የተቃውሞ ሰልፍ በተካሄደባቸው ከተሞች ውስጥ በአብዛኞቹ ግድያዎች፣ በጥይት ማቁሰልና ድብደባ እንዲሁም የዘፈቀደ የጅምላ እስር ስለመካሔዱ ያነጋገርናቸው ግለሰቦች ምስክርነት ያመለክታል።

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.