ካርድ በየቃቄ ውርድወት ሥም የሚጠራ የምርምር ሥራ ፌሎውሺፕ መርሐ ግብር ጀመረ

 

wfpየካርድ ውርድወት የምርምር ሥራ ፌሎውሺፕ መርሐ ግብር (ውርድወት ፌሌውሺፕ) ማኅበራዊ መበላለጦችን እንዲሁም በቁጥር አናሳ የሆኑ እና ለጥቃትና መድልዖ ተጋላጭ የሆኑ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የእኩል ዕድል እና የእኩልነት መብት ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችሉ አገር በቀል ዕውቀቶች እና ተሞክሮዎች ላይ ሴቶች እና ወጣቶች የምርምር ሥራ እንዲሠሩ ድጋፍ የሚያደርግ መርሐ ግብር ነው። መርሐ ግብሩ ለፌሎውሺፑ የሚመረጡ ሴቶች እና ወጣቶች የምርምር ሥራ ፍላጎታቸውን እንዲያሳኩም ተጨማሪ ዕድል ይሰጣል።

ካርድ ውርድወት የምርምር ሥራ ፌሎውሺፕ መርሐ ግብር ሥያሜውን ያገኘው ከየቃቄ ውርድወት ነው። የቃቄ ውርድወት የዛሬ 160 ዓመታት ገደማ የኖረች እና በጉራጌ ማኅበረሰብ ዘንድ ለእኩል የጋብቻ መብት የታገለች ባለታሪክ ነች።

ውርድወት በዛሬው የጉራጌ ዞን፣ ሞህር ቀበሌ የኖረች ሴት ናት። በጉራጌ ማኅበረሰቦች የቃል ታሪክ ውስጥ የቃቄ ውርድወት እየተባለች የምትታወስ ሲሆን ቃቄ የአባቷ ሥም መሆኑ ታውቋል። በ2007 ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ “እምቢታ” በሚል ርዕስ ባሳተመው ታሪካዊ ልቦለድ፣ ውርድወትን ለብዙ አንባቢዎች ያስተዋወቃት ሲሆን፥ ከዚያ በኋላ “የቃቄ ውርድወት” በሚል ርዕስ ተሠርቶ ለአራት ዓመታት ያህል መድረክ ላይ የቆየው ሙዚቃዊ ተውኔት የውርድወትን ገድል የበለጠ አስተዋውቆታል። የቃቄ ውርድወት ታሪክ ብዙዎችን ያነቃቃ እና የሴቶችን የመብቶች ትግል ለረዥም ጊዜ የኖረ እንደሆነ ያስተዋወቀ ነው።

የቃቄ ውርድወት ትግል በዋነኝነት የጋብቻ እኩል መብቶች ላይ ያጠነጥናል። በወቅቱ ትኖርበት የነበረው ማኅበረሰብ ባሕል ወንዶች ከአንድ ሴት በላይ የማግባት ትውፊታዊ መብት ቢኖራቸውም፣ ሴቶች ግን በዚህ ላይ የመወሰን መብት የላቸውም። የትዳር አጋሮቻቸውን መምረጥም ሆነ የፍቺ ጥያቄ ማቅረብ አልተፈቀደላቸውም። ውርድወት ግን ከሷ ውጪ ሁለት ሚስቶች ያገባውን ባለቤቷን ለመፍታት ትወስናለች። ሆኖም ይህ ውሳኔ ሴት በመሆኗ አንቂት የተባለ እርግማን ስለሚያስከትልባት፣ የጉራጌ ባሕላዊ ሸንጎ ወደ ሆነው የጆካ ጉዳዩን በመውሰድ ትሟገታለች። የቃቄ ውርድወት በሸንጎው ከመቅረቧ በፊት ለክርክር ይቀርቡ የነበሩት ወንዶች ነበሩ። ውርድወት ይህንን ዕድል ለማግኘት ብዙ ሴቶችን በማስተባበር አሳምፃለች። በስተመጨረሻም፣ የፍቺ መብቷ ያለ አንቂት ተረጋግጦላት እና ፍቺ ፈፅማ፣ የወደደችውን ሰው መርጣ ለማግባት የቻለች ሴት ነች።

ካርድ ይህንን የምርምር ሥራ ፌሎሺፕ ፕሮግራም በውርድወርት ሥም ለመጥራት ሲወስን፥ የቃቄ ውርድወርት ታሪክ አነቃቂ እንዲሁም አገር በቀል ችግሮችን በአገር በቀል መንገዶች እና አስተምህሮዎች ለመፍታት ሞዴል ይሆናል ብሎ በማመን ነው።

የውርድወት ፌሎዎች ለሰባት ወራት የሙሉ ሰዓት ምርምር እንዲያደርጉ የሚጠበቅ ሲሆን፣ ካርድ የሥራ ቦታ፣ አስፈላጊ ሲሆን አማካሪ መቅጠርና ተጓዳኝ ወጪዎችን የመሸፈን ኀላፊነት ይወስዳል። ተመራማሪዋ/ው ጥናታቸውን ሲያጠናቅቁ ሁለት የውይይት ወይም የምክክር መድረክ ማዘጋጀት ያለባቸው ሲሆን፣ የጥናት ውጤታቸውም ታትሞ ለሚመለከታቸው አካላት እንዲደርስ ይደረጋል።

የውርድወት ፌሎውሺፕ ዝርዝር የማመልከቻ መመሪያ እዚህ ይገኛል። የማመልከቻ ቀነ ገደቡ ሚያዝያ 22፣ 2012 ነው።

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.