የቀን፦ 16/04/2013 የእስክንድር ነጋ የችሎት ውሎ።

  • በእምነት ክህደት ቃል ተከሳሾች ወንጀሉን አለመፈፀማቸውን ለፍርድ ቤቱ ገልፀዋል

  • ምስክር ለመስማት ለመጋቢት 29፣20 2013 ጠቀጥሯል።

  • "አቃቤ ህግ የስርዓቱ ቡችላ ነው" ተከሳሾች

  • "ተከሳሾች ችሎት በመድፈር ይጡልኝ" አቃቤ ህግ

  • ምስክር ለመስማት ከ3 ወር 16 ቀን በላይ ተቀጥሯል

 

ሰዓት፦ 4፡20

 

ፍርድ ቤቱ አቃቤ ህግ አሻሽያለው ያለውን ክስ ለመመለክት ለዛሬ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቶ የነበረ ሲሆን ችሎቱ ከመጀመሩ በፊት አቶ እስክንድር ነጋ አቤቱታ አለኝ በማለት “ችሎት ታዳሚዎቻችን ላይ እንግልት እየደረሰ ነው፤ በባለፈው ችሎት በችሎት የታደሙ ደጋፊዎቻችን ታስረውብናል ስለሆነም ፍርድ ቤቱ አካሄዱ እንዲስተካክል ትእዛዝ እንዲሰጥልን” በማለት ጠይቀዋል። ፍርድ ቤቱም አቤቱታው በመቀበል ተጨማሪ አምስት ሰዎች ወደ ችሎት እንዲገቡና ችሎቱን እንዶታደሙ ፈቅዷል።

 

ፍርድ ቤቱ ዛሬ በዋለው ችሎት እነ እስክንድር ነጋ ከማክሰኞ 13/04/2013 የተዘዋወረው ተለዋጭ ቀጠሮ የተመለከተ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትእዛዝ መሰረት ሁለቱ ክሶች ማለትም የማህበራዊ ሚድያን በተመለከተ፤ ኦሮሚያ ሚድያና አማራ ሚድያ በሚል የፌስቡክ ገጽ እንዲሁም አራተኛ ተከሳሽ በተመለከተ እንዲጠቀስ የተጠየቀው ቦታ ‘አጠና ተራ ወደ ጦር ሃይሎች ታክሲ በሚያዝበት ፌርማታ አንድ ካፌ ውስጥ’ በሚል ክሱ ተሻሽሎ ቀርበዋል በሚል በችሎቱ ፊት ተነብበዋል።  

 

በመቀጠል የተከሳሾች የእምነት ክህደት ቃል እንደሚከተለው ተሰምተዋል።  በመጀመርያ ፍርድ ቤቱ አንደኛ ተከሳሽ አቶ እስክንድር ነጋን ወንጀሉን መፈጸማቸው እና አለመፈጸማቸው እንዲሁም ጥፋተኛ መሆናቸውና አለመሆናቸው ሲጠይቃቸው “አልፈጸምኩም፤ ጥፋተኛም አይደለሁም” በማለት የምሰጠውን ማብራርያ ቃለ በቃል ይያዝልኝ ሲሉ ጠይቀዋል። በዚህም መሰረት “ከሁሉ በፊት ሁሉም በሚያየው በሚሰማው እግዘብሄር ፊት እኔና ጓደኞቼ ጥፋተኞች አይደለንም፤ ሁሉንም በማታዩትና በማትሰሙት የኢትዮጵያ ህዝብ እና ችሎቱ ፊት ከክሱ አንድም መሰመር እውነት የለውም። እውነት ነጻ ታወጣለች”። ፍርድ ቤቱ ሀሳቡን በማሻሻል “እኔ እና ጓደኞቼ” የሚለው ሐረግ እርሶ ራስዎን ብቻ ስለሚወክሉ “እኔ ጥፋተኛ አይደለሁም፥ እውነቱ እያደር ይወጣል” በሚል አሻሽሎ ይዞታል። ዐቃቤ ህግ ጣልቃ በመግባት አቤቱታ አለኝ በማለት “በህዝቡ ፊት ተከሳሽ ክሱን የፖለቲካ ጉዳይ እንዲመስል እያደረገው ነው፤ እንዲሁም ተከሳሽ የሚያቀርበው ሀሳብ ከክሱ ጭብጥ ጋር በተያያዘ ብቻ እንዲሆን” ሲል ለችሎቱ ጠይቀዋል። በዚህ መሀል የተከሳሽ ጠበቆች “ዐቃቤ ህግ በእምነት ክህደት ቃል ላይ ጣልቃ መግባት አይችልም፣ ግዜ እየፈጁብን ነው፤ በተከሳሽ የሚቀርበው ሀሳብ ፖለቲካዊ ይዘት ይኑረው አይኑረው መወሰን የሚችለው ፍርድ ቤቱ ነው፣ ዐቃቤ ህግ በዛቻ መልክ ተከሳሶችን ማሰፈራራትና ማሸማቀቅ የለበትም” በማለት የመከራከርያ ነጥብ አንስተዋል። ፍርድ ቤቱ ችሎቱ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህግ መሰረት እንደሚመራ በመግለጽ የዐቃቤ ህግ አቤቱታ አልተቀበለውም።

 

 በሁለተኛ ደረጃ ፍርድ ቤቱ ሁለተኛ ተከሳሽ አቶ ስንታየሁ ቸኮልን ወንጀሉን መፈጸማቸው እና አለመፈጸማቸው እንዲሁም ጥፋተኛ መሆናቸውና አለመሆናቸው ሲጠይቃቸው “አልፈጸምኩም፤ ጥፋተኛም አይደለሁም” በማለት መልስ ሰጥተዋል። በመቀጠልም የሚከተለውን ማብራርያ ሰተዋል፦ “14 ሰዎች ገድላችዋል ተብሎ የቀረበብን ክሰ በተመለከተ እኛ አልገደልንም፤ ገድላችዋል ተብለን የቀረበብን ክስ ሆን ተብሎ ምርጫ እንዳንሳተፍ የቀረበ የሀሰት ውንጀላ ነው፣ ‘ብልጦች ከሰዋል ሞኞች ቀጥለዋል’። ስለዚህ የምትሰጡት ውሳኔ ለኛ ብቻ አይደለም ለኢትዮጵያ ሀዝብ በሙሉ ነው፤ የተዛባ የፍትህ ስርዓት እናንተ ከምታስቡት በላይ ነው ውጤቱ። ማንንም አልበደልንም፣ አላጠፋንም፣ አላታለልንምም፤ ዐቃቤ ህግ የከሰሰን በፖለቲካ ምክንያት ስለሆነ ፖለቲካዊ ምላሽ እንሰጣለን። ተረኝነት በተጠናወተው ስርዓት ተከሰን ቢሆንም እኛ ግን የህዝብ ድምጽ ሆነን ስልጣን የህዝብ እስኪሆን ትግላችን እንቅጥላለን”። በዚህ መሀል ዐቃቤ ህግ ፍርድ ቤቱ “የችሎቱን ስርዓት እያስከበረ አይደለም” በማለት አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን፤ በሌላ በኩል ደግሞ ጠበቆች የችሎትን አካሄድ በተመለከተ “ዐቃቤ ህግ ፍርድ ቤቱን ማዘዝ አይችልም” በማለት ተቋውመዋል። ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ህግ አቤቱታ በመቀበል የአቶ ስንታየሁን ንግግር በማቋረጥ “ከችሎቱ አሰራር ስርዓት እየወጣህ ስለሆነ በአካሄዱ መሰረት ተስተካከል” ሀሳብህ በህጉ መሰረት አቅርብ በማለት ሁሉም ተከሳሾች ችሎቱ ላይ አንዳንድ አላስፈላጊ ቃላት እንዳይጠቀሙ አቅጣጫ ሰጥተዋል።

 

በሶስተኛ ደረጃ ፍርድ ቤቱ ሶስተኛ ተከሳሽ ወንጀሉን መፈጸሟን እና አለመፈጸሟን እንዲሁም ጥፋተኛ መሆንዋና አለመሆንዋን ስትጠየቅ “አልፈጸምኩም፤ ጥፋተኛም አይደለሁም። በባለፈው ስርዓት ይሄን በመሰለ ችሎት ተከሰን ነበር፤ ነገር ግን ለነጻነት፣ ለፍትህ ፣ለሰባአዊነትና ለእኩልነት ስለነበረ አይቆጨኝም። የአሁኑን ክስ ዘርን መሰረት ያደረገ፣ ፍትህን የናቀ እምነትን የከዳ፣ ሰበዊነትን የሚጥስ እና ህዝብን የናቀ ክስ ነው። ዐቃቤ ህግ የስርዓቱን ቡችላ የሆነበትን ሁኔታ ተመልክቻለሁ...” ተናግራለች። ፍርድ ቤቱም ተከሳሽዋ ሀሳብዋን ሳትቋጭ በማቋረጥ “ቃላቶችን እየመረጥሽ ከስድብ ውጭ ሀሳብሽን ግለጪ” በማለት አርመዋል። በሌላ በኩል ዐቃቤ ህግ “ችሎት በመድፈር ሶስተኛ ተከሳሽ ላይ ውሳኔ ይሰጥልኝ ሲል” ጠይቀዋል። በዚህ መሀል የተቀሩት ሶስት ተከሳሾች (አንደኛ፣ ሁለተኛ እና አራተኛ) በህብረት አንድ ላይ “ዐቃቤ ህግ የስርዓቱን ቡችላ ነው” የሚለው ሁላችንም የተነጋገርንበትና የሁላችንም የጋራ ሀሳብ ነው በማለት ገልጸዋል። ከዚህ ምላሽ በኋላ ዐቃቤ ህግ አራቱንም ተከሳሾች ችሎትን በመድፈር እንዲጠየቅሉኝ ሲለ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። ፍርድ ቤቱም የዐቃቤ ህግ ክስን እንመለከተዋለን በማልት ሶስተኛ ተከሳሽን ሀሳብዋን እንድትቀጥል እድል ሰጥተዋል። “. . . ዳኞች ከስርዓቱ ተጽኖ ነጻ ሆናቹ እንድትዳኙን በኢትዮጵያ ህዝብ ስም እለምናለሁ” በማለት ሶስተኛ ተከሳሽ ሀሳብዋን ቋጭታለች።

 

በአራተኛ ደረጃ ፍርድ ቤቱ አራተኛ ተከሳሽ ወንጀሉን መፈጸሟን እና አለመፈጸሟን እንዲሁም ጥፋተኛ መሆንዋን አለመሆንዋን ስትጠየቅ “አልፈጸምኩም፤ ጥፋተኛም አይደለሁም” በማለት ለጥያቄው መልስ ከሰጠች በሁሏ የሚከተለውን ተጨማሪ ማብራርያ ሰጥታለች። “ሶስት ግዜ እግታ ተደርጎብኛል፣በጥቅማ ጥቅም ኮነዶሚንየም ይሰጥሻል በማልት ተለምኛለሁ፣ የመንግስት ስራ እየሰራሽ መንግስት ደመውዝ እየከፈለሽ ተቃዋሚ ፓርቲ አትደግፊ በማለት በስልክም ጭምር ተጠይቄለሁ፣ የተከሰስኩበትን ክስ የአማራና የደቡብ ህዝብ ለማጋጨት የሚለው የፍትህ ስርዓቱን እና ተዋዶ የኖረውን ህዝብ የሚያዋርድ ነው፣. . . ፍትህ ወዴት ናት? በቶሎ መዳኘት አለብን” በማለት ሀሳብዋን ገልጻለች።

 

የእምነት ክህደት ቃል ከተሰማ በሁላ ዐቃቤ ህግ “ማስረጃ አሰማም በተመለከተ ፍርድ ቤቱ በይግባኝ ይመልከትልኝ ካልሆነ ምስክሮችን በችሎቱ ማቅረብ እና ማሰማት ይዳግተኛል ”በማለት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል። በዚህ መሀል አቶ እስክንድር “እያንዳዱ ቀን ዋጋ እያስከፈለን ነው፣ ፍርድ ቤቱ በሂደት መሰማት አለበት፣ ዐቃቤ ህግ በቃል ብቻ ስለሆነ ያቀረበው በጽሁፍ እስኪያቀርብ በፍርድ ቤቱ ሂደት መሰረት ይታይልን፤ ወይስ ምርጫ እንዲያልፈን ነው የሚጓተተው፣ አጭር ቀጠሮ ተሰጥቶን በየዕለቱ ይታይልን ወይም ፍርድ ቤቱ judicial notice ይውሰድልን። ፍርድ ቤቱ በቀጥታም ባይሆን በትዘዋዋሪ ከምርጫ እንድንወጣ ዐቃቤ ህግን እየደገፈ ነው ”በማለት ተቃውሞ አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱ “እንደሱ አይንት ዓላማ የለንም፣ ክፍት ባለን ቦታ መሰረት እናያለን፤ የዐቃቤ ህግ የይግባኝ ጥያቄ በሚመለከት አያገባንም” በማለት መልስ ሰተዋል። በሌላ በኩል ጠበቆች “ዐቃቤ ህግ ምስክር ማቅረብ ካልቻለ ቀጠሮ ለምን ይሰጣል” በማለት ጠይቀዋል፤ ዐቃቤ ህግ ደግሞ “ማቅረብ አልችልም አላልኩም” በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

 

በመጨረሻም ፍርድ ቤቱ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፈዋል። በዐቃቤ ህግ ያቀረበው ችሎትን የመድፍር ክስ ባለማወቅና ስሜታዊ በመሆን የተሰነዘረ ቃል ስለሆነ በማለት በማስጠንቀቅያ ታልፈዋል። እንዲሁም ቀጣዩን ቀነ ቀጠሮ ለመጋቢት 29-30፣ ሚያዝያ 13፣14፣18፣19፣20፣21፣26 እና 28፤ 2013 እንዲሆን ተወስኗል።

 

ከዚህ ቀደም የነበረውን ችሎት ለማየት ይህን የጫኑ

 

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.