የተመረጡ የወንጀል የፍርድ ቤት ጉዳዮች ትንታኔ፦ ከክስ እስከ ምስክር መሰማት ጅማሮ

ቅድመ መግቢያ

 

የመብቶች እና ዴሞክራሲ ዕድገት ማዕከል (ሴንተር ፎር አድቫንስመንት ኦፍ ራይትስ ኤንድ ዴሞክራሲ /ካርድ/) ቦርድ-መር፣ ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች አዋጅ 113/2011 መሠረት፣ በመዝገብ ቁጥር 4307፣ ሐምሌ 17፣ 2011 ሕጋዊ ሰውነት ያገኘ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት ነው። ካርድ ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ተፈጥራ ማየትን ራዕይ አድርጎ ሰንቆ፣ የዴሞክራሲ መርሖዎችን በማስተጋባት ዴሞክራሲ በኢትየጵያ ብቸኛው የጫወታ ሕግ የማድረግ ተልዕኮ ይዞ እየሠራ የሚገኝ ድርጅት ነው።

 

ከካርድ ዓላማዎች መካከል “ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበራቸውን ለማረጋገጥ የፖሊስ ማቆያዎችን፣ የማረሚያ ቤቶችን አያያዝ እና የፍርድ ቤቶችን ሒደት መከታተል እና መገምገም” አንዱ ነው። በዚህም መሠረት የተለያዩ የፍርድ ችሎቶችን በመከታተል ዘገባውን ለተደራሲያኑ ያቀርባል[1]። በተጨማሪም በየወቅቱ የተለያዩ ሕጋዊ ትንታኔዎችን በማድረግ የፍርድ ሒደቶች አካሔድ ላይ የተስተዋሉ ችግሮችን ነቅሶ ለማሳየት ይጥራል።

 

ካርድ ከሚከታተላቸው እና የፖለቲካ አመራሮች ከታሰሩባቸው የክስ መዝገቦች መካከል በባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀ መንበር እስክንድር ነጋ እና በአሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አመራር አባል ጃዋር መሐመድ ሥም የሚጠሩት መዝገቦች ይገኙበታል። ከዚህ ቀደም በሁለቱ መዝገቦች ሥር የተጠረጠሩት ተከሳሾች ያለፉበትን የቅድመ ክስ ሒደት የሕግ ትንታኔ[2] ማቅረባችን ይታወሳል። በዚህ እና የቀደመው የሕግ ትንታኔ ተከታይ በሆነው ትንታኔ ሁለቱ መዝገቦች ላይ ምስክር መደመጥ ከመጀመሩ በፊት ያለፉበትን የሕግ ክርክር ሒደቶች ከሕግ አግባብ አንፃር ተገምግሟል። ግምገማውን ያሰናዱልን ሚኪያስ በቀለ[3] ናቸው።

 

የዚህን ትንታኔ ፒዲኤፍ እዚህ ክሊክ በማድረግ ዳውንሎድ ማድረግ ወይም ከታች ማንበብ ይቻላል።

 

 

 

I. መግቢያ

 

1. ይህ የፍርድ ቤት ጉዳዮች ትንታኔ ሁለት የወንጀል መዝገቦችን አካትቷል። የተካተቱት መዝገቦች - 1) እስክንድር ነጋ፣ ስንታየሁ ቸኮል፣ ቀለብ ስዩም፣ ጌትነት በቀለ፣ አስካል ደምለ፣ አሸናፊ አወቀ፣ እና ፍተዊ ገ/መድህን የተካተቱበት፣ ከዚህ በኋላ "የእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ" እየተባለ የሚጠቀስ እና 2) ጃዋር ሲራጅ መሐመድ፣ በቀለ ገርባ ዳኮ፣ ሀምዛ አዳነ ታዬ፣ ጉቱ ሙሊሳ ደጋፋ፣ ደጀኔ ጣፋ ገለታ፣ መስተዋርድ ተማም አደም፣ እረፋት አቡበከር ከድር፣ አማን ቃሉ ባቲ፣ ዓለማየሁ ገለታ ዋቀሳ፣ ኦሮሚያ ሚዲያ ኔትዎርክ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ ደጀኔ ጉተማ፣ መለሰ ዲሪብሳ ፋርጋሳ፣ ሸምሰዲን ጠሀ መሐመድ፣ ብርሃነ መስቀል አበበ ሰኚ፣ ፀጋዬ ረጋሳ አራርሳ፣ ቦና ቲቢሌ ኮሮ፣ ያለምወርቅ አሰፋ መንግሥቱ፣ ጌቱ ተረፈ ሰርቤሳ፣ ታምራት ሁሴን ሙዳ፣ በሽር ሁሴን ቦራ፣ ሰቦቃ ቃቆ ገላልቻ፣ ኬኔ ዱሜቻ ባዩ፣ ዳዊት አብደታ ጫሊ እና ቦጋለ ድሪብሳ ኦዲ የተከታቱበት፤ ከዚህ በኋላ "የእነ ጃዋር መሐመድ መዝገብ" እየተባለ የሚጠቀሰው ናቸው።

 

2.. ይህ ትንታኔ ክስ ከተመሰረተበት እስከ የ ዐቃቤ ሕግ ምስክር መሰማት ጅማሮ ድረስ ያለውን የፍርድ ቤት ሒደት ለመተንተን ጥረት ያደርጋል። በዚህም የክስ ማመልከቻ፣ የቀረቡ አቤቱታዎች እና መልሶች፣ ብሎም የፍርድ ቤት ትእዛዞች እና አካሔዶች፤ ኢትዮጵያ አባል ከሆነችባቸው የዓለም ዐቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሥምምነቶች፣ የዓለም ዐቀፍ እና ቀጠናዊ የሰብዓዊ መብቶች ተቋማት ለሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ከሰጧቸው ትርጉሞች እና መመሪያዎች፣ ከኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት፣ የወንጅል ሕግ እና ሒደቱ የሚተዳደርበት የሥነ ስርዓት ሕግ እና ሌሎች ተገቢነት ያላቸው የሕግ ማዕቀፎች አንፃር ለመመርመር ጥረት ተደርጓል። ክስ ከመመሥረቱ በፊት የነበሩ የጊዜ ቀጠሮ እና የቅድመ-ምርመራ ሒደቶች ከዚህ በፊት በተሠራ ትንታኔ ላይ ተካትተዋል።[4]

 

II. ዋስትና

 

3. ማንኛውም ሰው የነጻነት መብት (Right to Liberty) አለው። ይህ የነጻነት መብት ሊገደብ የሚችለው በሕግ በግልጽ በተቀመጠ ሁኔታ ብቻ መሆን እንዳበት ኢትዮጵያ አባል የሆነችባቸው የዓለም ዐቀፍ ሥምምነቶች ይደነግጋሉ።[5] የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም "በሕግ ከተደነገገው ሥርዓት ውጪ ማንኛውም ሰው ወንድም ሆነ ሴት ነጻነቱን/ቷም አያጣም/አታጣም [...] ክስ ሳይቀርብበት ወይም ሳይፈረድበት ሊታሰር አይችልም" በሚል ይደነግጋል።[6] ተጠርጥረው ወይም ተከሰው ያሉ ግለሰቦች የዋስትና መብት ሊከለከል የሚገባው - ተጠርጣሪው/ተከሳሹ ሊጠፋ፣ ምስክሮችን ሊደልል እና ለሌሎች ግልጽ እና ከባድ የሆነ አደገኝነት አለው ተብሎ የሚታሰብ ከሆነ፤ ይህም በበቂ ማስረጃ ሲረጋገጥ መሆን እንዳለበት የአፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች ቻርተርን የተረጎመው የአፍሪካ የሰብዓዊና ሕዝቦች መብት ኮሚሽን ያስረዳል።[7] የኢትዮጵያ የወንጀል ሒደት በሚተዳደርበት ሕግ መሠረት በሞት ወይም ከ15 ዓመት በላይ የሚያስቀጣ ብሎም በወንጀሉ ምክንያት ተበዳዩ የሚሞት ከሆነ ፍ/ቤቶች የዋስትና መብት ሊከለክሉ እና የዜጎችን የነጻነት መብት ሊገድቡ ይችላሉ።[8] የወንጀል ሥነ ስርዓት ሕጉ አክሎም፤ ግለሰቡ ለዋስትና እንዲያሟላ ፍ/ቤቱ የሚጠይቀውን ማሟላት የማይችል ከሆነ፣ ከእስር ከወጣ ሌላ ወንጀል ይፈፅማል ተብሎ የሚታመን ከሆነ ብሎም ምስክሮችን ሊያባብል እና ማስረጃ ሊያጠፋ ይችላል ተብሎ ከታመነ የዋስትና መብት ሊከለከል እንደሚችል ይደነግጋል።[9] የዋስትና መብት እንዲከበር የሚቀርብ ጥያቄ - የሚጠየቅበትን ምክንያት እና ለዋስትና ሊሟላ የሚችለውን ማስያዣ አካትቶ - በማንኛውም ጊዜ፣ በየትኛውም የፍርድ ሒደት ደረጃ እና በየትኛውም ፍርድ ቤት - ሊቀርብ ይችላል።[10]

 

4. በዚህ ትንታኔ ላይ በተካተቱት ሁለቱም መዝገቦች ላይ የቀረቡ ክሶች የዋስትና መብት የሚያስከለክሉ በመሆናቸው በዋስትና ጥያቄ የተደረገ የጠለቀ ክርክር አልነበረም። በሌላ ችሎት የተያዘ ጉዳይ እልባት ከማግኘቱ በፊት ጉዳዩ መቀጠል ባለመቻሉ ምክንያት ሲራዘም የዋስትና ጥያቄ ቀርቦ የተከለከበት አጋጣሚ ነበር። ጥር 26፣ 2013 በነበረው የእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ ችሎት ላይ የ ዐቃቤ ሕግ ምስክሮች አሰማምን የሚመለከት ይግባኝ ቀርቦ ሒደቱ ለጊዜው መታገዱን ተከትሎ የዋስትና መብት ጥያቄ ቢቀርብም ፍርድ ቤቱ ጥያቄያቸውን ሳይቀበላቸው ቀርቷል።

 

III. የተፋጠነ ፍትሕ

 

5. የፍርድ ሒደቶች ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ መከወን አለባቸው። የዜጎች ባልተገባ የፍርድ መዘግየት የመዳኘት መብት የሰብዓዊ መብት ነው። “የመጨረሻው ጊዜ መች ሊሆን እንደሚችል ላይገመት (uncertainity about faith) የሚችል ረዥም የፍርድ ሒደት መኖር የለበትም።[11] በተለይ የዋስትና መብታቸውን ተከልክለው በእስር ላይ ለሚገኙ ተከሳሾች ከጉዳዩ እና ለትክክለኛ ፍትሕ ለመስጠት ከሚያስፈልገው አንፃር ታይቶ እስሩ ከሚያስፈልገው ጊዜ በላይ መሆን የለበትም - የፍርድ ሒደቱም በተቻለ መጠን በፍጥነት መጠናቀቅ አለበት።[12] ለፍርድ ሒደት የሚያስፈልገው ጊዜ ምክንያታዊነት የሚታየው ከእንያንዳንዱ ጉዳይ አንፃር ሲሆን፥ የጉዳዩ ውስብስብነት፣ ተከሳሹ ፈፀመው ከተባለው ድርጊት እና ጉዳዩ በፍርድ ቤት እና አስተዳደርያዊ ተቋማት ከተያዘበት አካሔድ አንፃር እየታየ መወሰን አለበት።[13] የኢትዮጵያ የወንጀል ሥነ ስርዓት የወንጀል ጉዳይ ቀጠሮዎች ሊሰጡ የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች በዝርዝር አስቀምጧል።[14]

 

6. በዚህ ትንታኔ ላይ በታዩት ሁለቱም መዝገቦች ከዋናው የክስ ሒደት በተጨማሪ የተለያዩ ለፍርድ ቤት የሚቀርቡ አቤቱታች ነበሩ። እንደ ፍርድ ቤቱ ከማረሚያ ቤቶች ጋር የሚገናኝበት "ፕላዝማ ተበላሽቷል" ዓይነት የማረሚያ ቤቶች አስተዳደራዊ ሁኔታዎች፣ እና ፖለሲ የተሰጠውን ትዕዛዝ በጊዜ መፈፀም ባለመቻሉ ምክንያት ከሚኖሩ ያለአግባብ ቀጠሮዎች በስተቀር - ቀጠሮዎች በበቂ ምክንያት - ትዕዛዞችን ለመስጠት፣ የተሰጡ ትዕዛዞችም ውጤት ለመጠባበቅ፣ በበላይ ፍርድ ቤቶች በሚመጡ የእግድ ትዕዛዞች፣ የተከሳሾችን መቅረት ተከትሎ፣ ለተከራካሪዎች የዝግጅት ጊዜ ለመስጠት እና በመሳሰሉት ምክንያቶች ሲሰጡ ተስተውለዋል።

 

IV. ግልጽ ችሎት

 

7. የፍርድ ቤት ሒደቶች በግልጽ መካሔድ አለባቸው። የተከሳሾች በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብት በተለያዩ የዓለም ዐቀፍ ሥምምነቶች ብሎም በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም ላይ የተደነገገ ነው። ይህ መርሖ የተከሳሾች ተገቢ የፍትሕ ሒደት የማግኘት መብት (fair trial) አንዱ ምሰሦ ነው። ችሎቶች ግልጽ መሆን ያለባቸው ለተለዩ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆን ለአጠቃላይ ማኅበረሰቡ ብሎም ለሚዲያዎች ነው። የፍርድ ቤት ሒደቶች በግልጽ ችሎት መካሔዳቸው የሒደቱን ግልጽነት ስለሚያረጋግጥ፣ የፍትሕ ስርዓቱ በተጠያቂነት መንፈስ እንዲሠራ ምክንያት ይሆናል፤ በዚህም ምክንያት የግለሰቦች ብሎም የአጠቃላይ ማኅበረሰቡ ጥቅም እንዲጠበቅ ያግዛል።[15] ይህ ብቻ ሳይሆን ችሎቶች በግልጽ መካሔዳቸው በተከሳሽ እና በተበዳይ መካከል እርቅ (Restorative Justice) ለመፍጠር ምክንያት ይሆናል ተብሎ ይታመናል።

 

8. የፍርድ ቤት ሒደቶች ግልጽ መሆን አለባቸው ሲባል ችሎቶች ስለሚካሔዱት ጊዜ እና ቦታ በግልጽ ለማኅበረሱ ማሳወቅ፣ ብሎም ከጉዳዩ አንጻር ሒደቱን ለመከታተል ካለው ተነሻሽነት እና ከጉዳዩ ርዝመት አንጻር ታይቶ በቂ የሚባል አዳራሽ ሊኖር ያሻል እንደማለት ነው።[16] የችሎቶች ግልጽነት የሚዲያ ተወካዮች ተገኝነተው ሒደቱን መዘገብ እንዲችሉ መፍቀድን ያካትታል።[17] ነገር ግን በችሎት ሒደት ጊዜ ካሜራ መጠቀም ላይ ክልከላ ሊደረግ ይችላል።[18]

 

9. ችሎቶች ዝግ የሚሆኑባቸው አጋጣሚዎች የተለዩ ናቸው። የዓለም ዐቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃል ኪዳን ዝግ ችሎቶች፣ ማለትም ሚዲያ እና አጠቃላይ ማኅበረሰቡ ችሎቶችን ከመታደም ሊከለከል የሚገባው ከሞራል አኳያ፣ የማኅበረሰቡን ደኅነንት ለማስጠበቅ፣ የተከራካሪዎች የግል ሕይወት አደጋ ላይ እንዳይወድቅ፣ ብሎም ችሎቱ ክፍት መሆኑ ትክክለኛ የፍትሕ አሰጣጥን አደጋ ውስጥ ይከታል ተብሎ የሚታመን ከሆነ ብቻ መሆኑን ይገልጻል።[19] የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መመሪያ በበኩሉ፤ ሕፃናትን እና ምስክሮችን ለመጠበቅ፣ የወሲባዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ግለሰቦችን ማንነት ለመደበቅ፣ ብሎም የማኅበረሰቡን እና የአገርን ሰላም እና ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚል በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብት ሊገደብ እንደሚችል ይደንግጋል።[20] የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 20(1) ላይ፤

 

"የተከሰሱ ሰዎች ክስ ከቀረበባቸው በኋላ [...] ለሕዝብ ግልጽ በሆነ ችሎት የመሰማት መብት አላቸው። ሆኖም የተከራካሪዎች የግል ህይወት፣ የሕዝብን የሞራል ሁኔታና የአገሪቱን ደኅንነት ለመጠበቅ ሲባል ብቻ ክርክሩ በዝግ ችሎት ሊሰማ ይችላል" በሚል ይደነግጋል።

 

10. በዚህ ትንታኔ ላይ በተካተቱ መዝገቦች አንዳንዴ ተገቢ በሆኑ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በቂ ባልሆኑ ምክንያቶች፣ በፍርድ ቤት ብሎም በችሎር አስከባሪ የፖሊስ አባላት ችሎቶችን ታዳሚዎች እንዳይከታተሉ ክልከላዎች ይደረጉ ነበር። ክልከላዎቹ ቤተሰቦች፣ ጋዜጠኞችን ብሎም ደጋፊዎችን ያካተተ ነበር። ክልከላዎቹ ለፍርድ ቤቱ ሙግት ምክንያትም ሲሆኑ ተስተውለዋል። በእነ እስክድር ነጋ መዝገብ ደጋፊዎች በለበሱት ልብስ ምክንያት ችሎቱን እንዳይታደሙ የተከለከሉበት አጋጣሚ የነበረ ሲሆን ይህም ለችሎቱ ቀርቦ ነበር። በታኅሣሥ 13፣ 2013 በነበረው ችሎት ደጋፊዎች በለበሱት ልብስ እና የፊት መሸፈኛ ምክንያት እንዳይገቡ እንደተከለከሉ ተከሳሾች አቤቱታ አቅርበዋል። ይህ አቤቱታም በሚቀጥለው - በታኅሣሥ 16፣ 2013 ቀጠሮ ላይ በድጋሚ፥ በታዳሚዎች ላይ እንግልት እየተፈጠረ ነው በሚል በችሎት ተነስቷል። ፍ/ቤቱም በዚህ ቀጠሮ ላይ ተጨማሪ አምስት ሰዎች እንዲገቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

 

11. በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገብም በተመሳሳይ የቤተሰብ፣ የሚዲያ እና የደጋፊዎች የችሎት ላይ ተሳትፎ ክልከላ ተስተውሎ ነበር። ጥር 19፣ 2013 በዋለው የእነ ጃዋር መሐመድ ችሎት ተከሳሾቹ፥ ቤተሰቦች እና ደጋፊዎች በለበሱት ልብስ እና በሚናገሩት ቋንቋ እየተለዩ ወደ ችሎቱ እንዳይገቡ፣ ብሎም እንዲታሰሩ ሆነዋል በሚል አቤቱታ አቅርበዋል። በቂ የችሎት ታዳሚ በሌለበት የእምነት ክህደት ቃላችንን ለመስጠት እንቸገራለንም ብለው አመልክተዋል።

 

ፍ/ቤቱ የታዳሚዎች ልብስ ከተከሳሾች ለመለየት አስቸጋሪ መሆን እንደሌለበት፣ በብሔር እየለዩ መከልከል ግን ተገቢ አለመሆኑን በመግለጽ፣ ግልጽ ችሎቶች ሒደቱ ፍትሐዊ እና ገለልተኛ እንዲሆን እንጂ ለድጋፍ እና ተቃውሞ አይደለም በሚል ተገቢ ማብራሪያ ሰጥቷል። ፍ/ቤቱ አክሎም በጥር 19፣ 2013 በዋለው ችሎት በቂ ታዳሚ ባለመኖሩ የተከሳሾችን የእምነት ክህደት ቃል ሳይቀበል ቀርቷል።

 

ችሎት የተከለከሉት ታዳሚዎች ቢጫ ልብስ በመልበሳቸው፣ ተከሳሾች በማረሚያ ቤት ከሚለብሱት ልብስ ጋር ተመሳሳይነት ሊኖረው ስለሚችል፣ ብሎም በችሎቶች ውስጥ ሊኖሩ የሚችሉ ድጋፍ እና ተቃውሞዎች በፍርድ ቤቱ ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥሩ ስለሚችሉ ከላይ በተገለጹት የዓለም ዐቀፍ ሥምምነቶች መሠረት፣ ፍትሕ ሊዛባ የሚችልበት አጋጣሚ ሊፈጥሩ ስለሚችሉ ገደቡ ተገቢ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። እነ ጃዋር መሐመድ የእምነት ክህደት ሊሰጡ በተቀጠረበት የሚቀጥለው ቀጠሮ - በጥር 27፣ 2013 - ችሎቱ ከመጀመሩ ከጥቂት ደቂቃዎች አስቀድሞ ጋዜጠኞች ችሎቱ ወደ ሚታይበት አዳራሽ እንዳይገቡ የተከለከሉ ሲሆን፣ የገቡም እንዲወጡ ተደርጎ ነበር። ተከሳሾች ይህንን፣ የሚዲያ አካላት በችሎቱ ላይ እንዳይታደሙ መደረጋቸውን ለፍ/ቤቱ አሳውቀዋል። በዚህኛው ችሎት የተሰተዋለው የችሎት አስከባሪዎች የፀጥታ አካላት መብቱን ለመገደብ በቂ ምክንያት በሌለበት ሁኔታ የተደረገ የተከሳሾችን በግልጽ ችሎት የመዳኘት መብት የሚጋፋ ነው ተብሎ ሊወሰድ ይችላል።

 

V. የመከላከል መብት

 

ሀ) የክስ ማመልከቻ ግልጽነት

 

12.ክስ በተቻለ መጠን ለተከሳሹ ራሱን መከላከል የሚችልበትን ግልጽ መረጃ መስጠት አለበት። የዓለም ዓቀፍ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን ማንኛውም ዜጋ የቀረበበትን ክስ ወዲያውኑ የማወቅ መብት እንዳለው፣ የክሱን ባህሪ እና ምክንያት (nature and cause) ማወቅ በሚያስቸለው መልኩ በሚገባው ቋንቋ በዝርዝር ሊቀርብለት እንደሚገባ ይደነግጋል።[21] የአፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን መመሪያም ተከሳሹ በሚገባው ቋንቋ እና በዝርዝር፣ ክሱ እንደቀረበ ወዲያውኑ፤ የክሱን ባሕሪ እና ምክንያት ሊገለጽለት እንደሚገባ፣ ብሎም መረጃው የተከሰሰበትን የሕግ ድንጋጌ ብሎም ክሱ የተመሠረተበትን ድርጊት (alleged fact) ማካተት እንዳለበት፣ ተከሳሹም እራሱን መከላከል እና ነጻ ሊሆን የሚችልበትን እርምጃዎች ሊወስድ የሚያስችለው መሆን እንዳለበት ይደነጋግል።[22] የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም በተመሳሳይ ዜጎች የሚቀርብባቸውን የወንጀል "[ክስ] በቂ በሆነ ዝርዝር እንዲነገራቸው እና ክሱን በጽሑፍ የማግኘት መብት አላቸው" በሚል ይደነግጋል።[23] የኢትዮጵያ የወንጀል ስነስርዓት ሕግ በበኩሉ ክስ በሚቀርብበት ጊዜ "[...] ወንጀሉ የተፈጸመበትን ጊዜና ስፍራ ተገቢ በሆነ ጊዜም የተበደለው ሰው ስም ወይም ወንጀሉ የተፈጸመበት ንብረት [...]" ሊያካትት እንደሚገባ ይደነግጋል።

 

13. በዚህ ትንታኔ ላይ በተካተቱ ሁለት መዝገቦች የቀረቡ የክስ ማመልከቻዎች ተከሳሾች ፈጸሙ የተባሏቸውን አንዳንድ ድርጊቶች ዝርዝር ማብራሪያ አላከተተም። በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ ላይ ተከሳሾቹ አመፅ እና ግጭት እንዲነሳሱ ትዕዛዝ ብሎም ገንዘብ መስጠታቸው ተገልጿል። ነገር ግን ተከሳሾች ለማን ትዕዛዝ እንደሰጡ፣ መቼ ትዕዛዝ እንደሰጡ፣ በምን ዓይነት የግንኙነት አካሔድ ትዕዛዙን እንደተሰጡ፣ ብሎም በእነ ማን መካከል ግጭት ለማነሳሳት ትዕዛዝ እንደሰጡ፣ እና የመሳሰሉት - ሳይገለጹ በደፈናው ተቀምጧል። በተመሳሳይ በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገብ - አቶ ጃዋር ሲራጅ (1ኛ ተከሳሽ) አመፅ እንዲፈፀም ጥሪ እንዳስተላለፉ ቢገለጽም መቼ፣ በየትኛው የግንኙነት/የሚዲያ አማራጭ እንዳስተላለፉ አልተገለጸም። የአቶ በቀለ ገርባ (2ኛ ተከሳሽ) ክስም ላይ ቄሮን እንዲነሳ ትእዛዝ እንደሰጡ የተገለጸ ሲሆን - የቄሮ ማንነት፣ ለማን ትዕዛዙ እንደተሰጠ፣ መቼ እንደተሰጠ፣ በየትኛው የግንኙነት አማራጭ ትዕዛዙ እንደተሰጠ አልተገለጸም። አቶ ጉቱ ሙሌሳ (4ኛ ተከሳሽ) የተባሉ ተከሳሽ በተመሳሳይ ተቃውሞ እንዲካሔድ፣ ግጭትም እንዲፈጠር ትዕዛዝ ማስተላለፋቸው ቢጠቀስም፤ ለማን ትዕዛዙን እንዳስተላለፉ፣ መች እና እንዴት እንዳስተላለፉ አልተጠቀሰም። ሀምዛ አዳነ (3ኛ ተከሳሽ)፣ መስተዋርድ ተማም (6ኛ ተከሳሽ)፣ አማን ቃሉ (8ኛ ተከሳሽ) እና ሸምሰዲን ጠሃ (13ኛ ተከሳሽ) የተባሉ ተከሳሾች ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ አመፅ እንዲነሳ እና ግጭት እንዲፈጠር ማድረጋቸው ቢገለጽም፤ በየትኛው የማኅበራዊ ሚዲያ መሆኑ፣ መቼ እንደሆነ፣ ይዘቱ ምን እንደሚል፣ የመሳሰሉት አልተጠቀሱም። አቶ ደጀኔ ጣፋ (5ኛ ተከሳሽ) የተባሉ ተከሳሽ ንብረት እንዲጠፋ ቅስቀሳ ማድረጋቸው ቢገለጽም መቼ እና በየትኛው አጋጣሚ ቅስቀሳ ስለማድረጋቸው፣ በየትኛው ንብረት ላይ ስለመሆኑ ሳይገለጽ ታልፏል።

 

14. የክስ ማመልከቻ ግልጽነት በሁለቱም መዝገቦች አከራከሮ ነበር። በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ ተከሳሾች ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ፣[24] ማለትም - ሞቱ ስለተባሉት 14 ሰዎች የተከሳሾች ተሳትፎ በግልጽ እንዲቀርብ በሚል እና የትኞቹን ብሔሮች በየትኛዎቹ እንዳነሳሱ፣ ተልዕኮ ለማን እንደሰጡ፣ በምን የሚዲያ አማራጭ እንዳነሳሱ በግልጽ አልተቀመጠም - የሚሉ መቃወሚያዎችን ተከትሎ ብሔርን ከብሔር ማጋጨት እና የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን በሚመለከት  ዐቃቤ ሕግ ክሱን እንዲያሻሽል ፍ/ቤቱ ሕዳር 29፣ 2013  በዋለው ችሎት አዝዞ ነበር። ይህንን ተከትሎ  ዐቃቤ ሕግ በታኅሣሥ 16፣ 2013 በዋለው ችሎት የማኅበራዊ ሚዲያ የተባለው የኦሮሚያ እና አማራ ሚዲያ መሆኑን፣ ለ4ኛ ተከሳሽ (ስንታየሁ ቸኮል) ያልተጠቀሰው ቦታ ደግሞ አጠና ተራ ታክሲ የሚያዝበት አካባቢ በሚል ይሰተካከል በሚል ክሱን አሻሽሏል። በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገብ በጥር 4፣ 2013 በዋለው ችሎት ተከሳሾች ያቀረቡትን የክስ መቃወሚያ ተከትሎ ፍ/ቤቱ - "ሸኔ" ቡድን ይሁን ግለሰብ እንዲገለጽ፣ የተጠቀሰው የጦር መሣሪያ መቆጣጠሪያ አዋጅ[25] ድርጊቱ ከተፈፀመ በኋላ የወጣ በመሆኑ እንዲስተካከል ወይም ክሱ እንዲተው ፍርድ ቤቱ ያዘዘ ሲሆን፣ ወንጀል ተብሎ ያልተገለጸ ተግባር የቴሌኮም ወንጀል ተብሎ መቅረቡ፣ "ነፍጠኛ" ማለት ወንጀል ባልሆነበት መገለጹ እና ተከሳሾች ተለይተው ይቀረቡ በሚል የቀረቡትን ደግሞ ውድቅ አድርጓል። ይህንን ተከትሎ በጥር 14፣ 2013  በነበረው ቀጠሮ  ዐቃቤ ሕግ - "ሸኔ" ቡድን መሆኑን እና ለ3ኛ ተከሳሽ በተለየ በምን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የተባለውን በፌስቡክ እና ኦኤምኤን ላይ መሆኑን በመግለጽ ክሱን የተሻሻለ ሲሆን፣ በጦር መሣሪያ መቆጣጠሪ አዋጅ የቀረቡ ክሶች ከአዋጁ በፊት ለነበሩ ድርጊቶች በመሆናቸው ውድቅ ሆነዋል።[26]

 

ለ) የማስረጃ ግልጽነት - የምሰክሮች አሰማም

 

15. በዚህ ትናታኔ ላይ የተከታተቱት ሁለት መዝገቦች የ ዐቃቤ ሕግ ምስክር አሰማም አከራካሪ ሆኖ ነበር። የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 20(4) እንደሚደነግገው፤

 

[ተከሳሾች] የቀረበባቸውን ማናቸውንም ማስረጃ የመመልከት፣ የቀረቡባቸውን ምስክሮች የመጠየቅ፣ ለመከላከል የሚያስችላቸውን ማስረጃ የማቅረብ ወይም የማስቀረብ እንዲሁም ምስክሮቻቸውን ቀርበው እንዲሰሙላቸው የመጠየቅ መብት አላቸው።

 

የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን ተከሳሽ መከላከል እንዲያሰችለው የተሟላ ነገሮች (adequate facilities) ሊደርሰው እንደሚገባ ሲደነግግ፣ እነዚህም  ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ማቅረብ ያሰባቸውን የሰነድ ብሎም ሌሎች ማስረጃዎችን በሙሉ ያካትታል።[27] የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት መመሪያም በተመሳሳይ ተከሳሾችን ለቀረበባቸውን ክርክር እና ማስረጃ ተዘጋጅተው መመለስ እንዲችሉ ተገቢው ዕድል ሊሰጣቸው እንደሚገባ ያትታል።[28]

 

16. ምስክሮች በድብቅ ሊሰሙ የሚችሉበት አንዱ አጋጣሚ - ለደኅንነታቸው ጥበቃ እንዲረግላቸው የሚል ነው። የአፍሪካ ቻርተር ለመተርጎም ኮሚሽኑ ባወጣው መመሪያ የምስክሮች ደኅንነት አደጋ ላይ ይወድቃል የሚባል ከሆነ፣ ፍርድ ቤቶች የምስክሮች ማንነት እንዲደበቅ ሊፈቅዱ እንደሚችሉ ይደንግጋል።[29] የምስክሮች ማንነት ሊደበቅ የሚገባው የወንጀሉን ባሕሪ እና ሁኔታ በማየት፣ የምስክሩን ደኅንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ (አስፈላጊነቱ በማስረጃ ሲረጋገጥ) እና ትክክለኛ ፍትሕ ለመስጠት ተገቢ መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ ነው።[30] ነገር ግን ዳኛም ሆነ ተከላካዩ አካል ላያውቁት የሚችሉት ምስክር አይፈቀድም።[31] ኢትዮጵያም ራሱን የቻለ የጠቋሚ እና የምስክሮች ጥበቃ የሚደረግበት ሒደት የሚተዳደርበት ሕግ አላት።[32]

 

17. በዚህ ትንታኔ ላይ በተካተቱት ሁለት መዝገቦች የምስክሮች አሰማም ሒደት ዋናው ጉዳይ ከሚታይበት የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እስከ ይግባኝ ሰሚ እና የሰበር ሰሚ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ድረስ ክርክር ተደርጎበታል። በእነ ጃዋር መዝገብ  ዐቃቤ ሕግ ዋናው ጉዳይ በሚታይበት የፌደራል የከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ 146 ምስክሮች ማንታቸው እንዲደበቅ እና ከመጋረጃ ጀርባ እንዲሰሙ የጠየቀ ሲሆን፣ ፍ/ቤቱ የአደጋ ስጋት ስለመኖሩ በቂ ማስረጃ አልቀረበበትም ብሎም በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 20(4) ላይ የተደነገገውን የተከሳሾች የሰብዓዊ መብት ለመጠበቅ በሚል፣ የምስክሮች ሥም ዝርዝር ሳይቀርብ በግልጽ ችሎት እንዲመሰክሩ ብይን ሰጥቷል። ይህንን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ - የምስክሮች ጥበቃ በ ዐቃቤ ሕግ መወሰን ያለበት ነው፣ ከመጋረጃ ጀርባ ምስክሮቹ ቢሰሙም ተከሳሾች መጠየቅ (መስቀለኛ ጥያቄ) ስለሚችሉ መብታቸውን አይጋፋም እንዲሁም አቶ ጃዋር "ጠባቂዎቼ ተነሱ" ማለታቸውን ተከትሎ የተፈጠረው ኩነት[33] ምስክሮቹ ለደኅንነታቸው አደጋ እንዳለባቸው አመላካች ነው - የሚሉ መከራከሪያዎች በማቅረብ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ አቅርቧል። ተከሳሾች በበኩላቸው ምስክሮቹ በቅድመ ምርመራ ጊዜ በግልጽ ችሎት መስክረው ምንም አደጋ ስላልደረሰባቸው አሁንም አይደርስባቸውም በሚል ተከራክረዋል። የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤትም ጉዳዩን ወደ ሥር ፍ/ቤት - የከፍተኛ ፍርድ ቤት - በመመለስ ዐቃቤ ሕግ ለምስክሮቼ ስጋት ያለውን ዝርዝር አቅርቦ ክርክር እንዲደረግ አዝዟል። ይህንንም ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ለምስክሮቼ ደኅንነት ስጋት ነው ያለው ጥያቄ ውድቅ መደረጉን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ጉዳዩን ወደ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የወሰደው ሲሆን የሰበር ሰሚ ችሎቱም የቀረበውን የሰበር ቅሬታ ውድቅ በማድረግ ምስክሮች በግልጽ ችሎት እንዲሰሙ የሚለውን ውሳኔ አጽድቆታል።

 

18. በተመሳሳይ በእነ እስክንድር መዝገብ ዐቃቤ ሕግ ዋናው ጉዳይ በሚሰማበት የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ምስክሮቼ ከተከሳሾች ጋር ስለሚተዋወቁ ብሎም ማስፈራሪያም ስለደረሳቸው ከመጋረጃ ጀርባ እንዲሰሙልኝ በሚል የምሰክሮች ጥበቃ አዋጅ ድንጋጌዎችን በመጥቀስ አቤቱታ ያቀረበ ሲሆን የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ በሕዳር 29፣ 2013 በዋለው አቤቱታው በማስረጃ የተደገፈ አይደለም በሚል ውድቅ አድርጎታል። ዐቃቤ ሕግ ምስክሮች በሚሰሙበት ጊዜ፣ በድጋሚ ምስክሮቹ ከዚህ በፊት ዛቻና ማስፈራራት ስለደረሰባቸው የሥም ዝርዝራቸውን ማቅረብ የለብኝም ቢልም፣ የተከሳሽ ጠበቆች ጉዳዩ ከዚህ በፊት ተነስቶ ውድቅ የተደረገ ስለሆነ፣ ለዝግጅት እንዲረዳን የሥም ዝርዝራቸው ቀድሞ ይሰጠን በሚል አቅርበዋል። ይህንን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ጉዳዩን ወደ ፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በይግባኝ በመውሰድ፣ የምስክር አሰማሙ ሒደት እንዲታገድ አድርጓል። በጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤትም ዐቃቤ ሕግ፤ ምስክሮቹ በቅድመ ምርመራ ጊዜ ዛቻ እና ማስፈራራት ስለገጠማቸው ብሎም፣ ተከሳሾች መስቀለኛ ጥያቄ መጠየቅ ስለሚችሉ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(4) የተደነገገውን መብታቸውን አይጋፋም በሚል - 16 ምስክሮች በዝግ ችሎት፣ 5 ምሰክሮች ደግሞ ከመጋረጃ ጀርባ እንዲሰሙ ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን፤ የተከሳሽ ጠበቆች በምስክሮቹ ላይ አደጋ ስለመኖሩ በቂ ማስረጃ ስላልቀረበ ብሎም ምስክሮቹን ለመጠበቅ ሌላ - እንደ መኖሪያ አድራሻ የመቀየር እና የጦር መሳሪያ የማስጣጠቅ አይነት አማራጮች ስላሉ ይግባኙ ውድቅ እንዲደረግ ጠይቀዋል። የጠቅላይ ፍርድ ቤቱም ምስክሮች ላይ አደጋ የተባለው ቀረቦ ክርክር እንዲደረግበት ጉዳዩን ወደ ሥር ፍርድ ቤት፣ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መልሶታል። የከፍተኛው ፍርድ ቤትም በጉዳዩ የአከራከረ ሲሆን - ዐቃቤ ሕግ ክሱ ላይ ልዩ ሥልጠና በመውሰድ በግለሰቦች ላይ ጥቃት የማድረሰ ድርጊት በመሆኑ ብሎም ምስክሮቹ ላይ ጥቃት ለማድረስ እንደተሞከረባቸው በመግለጽ ያመለከተ ሲሆን፣ የተከሳሽ ጠበቆች በበኩላቸው በጽሑፍ ብቻ ስለቀረበ ምስክሮቹ ስጋት አለባቸው ማለት አይቻልም፣ በዝርዝር እና ከምክንያታዊ ጥርጣሬ ውጪ ባልቀረበበት የተከሳሾችን የመከላከል መብት መጣበብ የለበትም በሚል ተከራክረዋል። ፍ/ቤቱም ምስክሮቹ በግልጽ ችሎት እንዲሰሙ የወሰነ ሲሆን፣ ዐቃቤ ሕግ ይህንን በመቃወም የሰበር አቤቱታ አቅርቧል። የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎቱም በሰኔ 10፣ 2013 በዋለው ችሎት የዐቃቤ ሕግን ቅሬታ ውድቅ አድርጎታል።

 

ሐ) በአካል በችሎት ክርክር ማቅረብ - በሌሉበት እንዲታይ

 

19. በእነ ጃዋር መዝገብ የሚገኙ ተከሳሾች የደኅንነት ስጋትን፣ ብሎም በፍርድ ሒደቱ ላይ እምነት የለንም የሚሉ ምክንያቶችን በመጥቀስ በተለያዩ ጊዜያት ወደ ችሎት አንቀርብም ሲሉ ተስተውለዋል። ከ1ኛ እስከ 4ኛ ያሉ ተከሳሾች ለደኅንታችን ስለምንሰጋ ወደ ምንገኝበት ማረፊያ ቤት ቅርብ በሆነ ችሎት ጉዳያቸን እንዲታይ በሚል ቢያመለክቱም ፍርድ ቤቱ በታኅሣሥ 8፣ 2013 በዋለው ችሎት ጥያቄው በማስረጃ ያልተደገፈ ነው በሚል ውደቅ አድርጎታል፤ ተከሳሾቹ ተገደው እንዲቀርቡም ትዕዛዝ ሰጥቷል። ይህንን ተከትሎ በነበረው የጥር 4፣ 2013 ቀጠሮ ተከሳሾች ሳይገደዱ በራሳቸው ፍቃድ የቀረቡ ሲሆን፣ ፍ/ቤቱ ደኅንታቸውን ለማስጠበቅ ከሚመለከትው መንግሥታዊ አካል ጋር በጋራ እንደሚሠራ አሳውቋቸዋል። ሰኔ 21፣ 2013 በዋለው ችሎት 4ቱ ተከሳሾች በፍትሕ ስርዓቱ ላይ እምነት ስለሌለን ብሎም የፍርድ ቤት ትዕዛዞች በአስፈፃሚው አካል ስለማይተገበሩ ከዚህ በኋላ ወደ ችሎት አንቀርብም በሚል ለፍርድ ቤቱ በጽሑፍ አሳውቀዋል። ፍርድ ቤቱም መጥሪያ ደርሷቸው እስከ ሐምሌ 21፣ 2013 ድረስ እንዲቀርቡ በሚል ዕድል ሰጥቷል። በሐምሌ 21፣ 2013 ችሎት ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾች ተገደው እንዲቀርቡ ጥያቄ ቢያቀርብም፥ ተከሳሾች በፍትሕ ስርዓቱ እምነት የለንም በሚል ያቀረቡት ተቀባይነት እንደሌለው በመግለጽ፣ ተከሳሾች "የመከላከል መብታውን በፍቃዳቸው ስለተዉ" በሚል ጉዳዩ በሌሉበት እንዲታይ ብሏል። ይህንን ተከትሎ ተከሳሾቹ ያቀረብነው ምክንያት (የፍርድ ቤት ትዕዛዝ በአስፈፃሚው ስላለፈፀሙ) በአግባቡ ያልመረመረ በመሆኑ፣ ተከሳሾችን በሕግ አስገድዶ ማስቀረብ በሚችልበት፣ በሌሉበት እንዲታዩ የሚለው ትዕዛዝ ቀድሞ በሰነድ ለተሳሾች ባለመቅረቡ፣ ትዕዛዙ ለየትኛው ክርክር እንደሆነ ግልጽ ስላለሆነ፣ እና ተከሳሾቹ በእስር በሚገኙበት ሁኔታ በሌሉበት ሊባል ስለማይገባ፤ የሚሉ ምክንያቶችን በማቅረብ ለፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ይግባኝ ያቀረቡ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ አቤቱታቸውን ተቀብሎ ዐቃቤ ሕግ ምላሽ እንዲያቀርብበት እና ክርክር እንዲደረግ ጉዳዩን ያስቀርባል ያለ ሲሆን - ይህ ትንታኔ እስከሚታተምበት ጊዜ ጉዳዩ በዚህ ላይ ይገኛል።

 

20. ሒደቱ በአትዮጵያ የወንጀል ስርዓት ከነበሩት ሒደቶች ለየት ያለ ሆኖአል።

 

በተለምዶ ተከሳሾች በሌሉበት እንዲታዩ የሚደረጉ ጉዳዮች በማረሚያ ቤት ለሚገኙ ሳይሆን በውጪ ሆነው ሊገኙ ላልቻሉ ተከሳሾች ነበር። በኢትዮጵያ የወንጀል ሥነ ስርዓት ሕግ በሌሉበት ሊታዩ የሚችሉት ከ12 ዓመት ፅኑ እስራት በታች ለማያሰቀጡ ወንጀሎች እና፣ በፅኑ እስራት ወይም ከ5,000 ብር በላይ ለሚያስቀጡ በአገር ላይ የሚፈፀሙ የኢኮኖሚ ወንጀሎች ለተከሰሱ ተከሳሾች ሲሆን፥ ተከሳሹ ያለበቂ ምክንያት ሳይቀርብ ሲቀር እንዲታሰር ትእዛዝ ወጥቶ ለመያዝ የማይቻል ከሆነ፣ እና በጋዜጣ ወይ በሌላ አማራጭ በግልጽ የማይቀርብ ከሆነ በሌለበት ጉዳዩ እንደሚታይ የሚገልጽ ጥሪ ከተደረገለት በኋላ ነው።[34]

 

የወንጀል ተከሳሽ በየችሎቶች ላይ ራሱ የመቅረብ መብት ያለው ቢሆንም ይህንን መብቱ ሊተው ይችላል - ይህም መሆን ያለበት በግልጽ (unequivocally) እና ከተቻለውም በጽሑፍ (preferably in written) የመቅረብ መብቱን መተዉን ሲገለጽ ብቻ ነው።[35] በዚህ ጉዳይ ላይ ለተከሳሾች የተደረገው ጥሪ በግልጽ - መቅረታቸው በሌሉበት እንዲታይ የሚለውን ውጤት እንደሚያመጣ ካለመግለጹ ባሻገር፣ ተከሳሾቹ በጽሑፍ ያቀረቡት እና "የፍርድ ቤት ትእዛዞች በአስፈፃሚው ስለማይፈፀሙ አንቀርብም" የሚለው አቀራረብ በአካል ቀርበው የመከራከር መብታቸውን በፍላጎታቸው በግልጽ ትተዋል ለማለት አያስችልም።

 

VI. የእስረኛ አያያዝ

 

21. በቁጥጥር ሥር የሚገኝ ማንኛውም እስረኛ በአግባቡ፣ ሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ መያዝ አለበት። ማሰቃየት፣ ወይም ያለፍቃድ ታሳሪው የሕክምና ሙከራ ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ በየትኛውም ሁኔታ የተከለከለ ሲሆን፣ በተለያዩ የዓለም ዐቀፍ ሥምምነቶች ላይ ተካትቷል።[36] የመንቀሳቀስ መብታቸው ተገድቦ በእስር ላይ የሚገኙ ግለሰቦች ሰብዓዊ በሆነ፣ ለሰው ልጆች በሚገባቸው ክብር ልክ ሊያዙ ይገባል።[37]

 

ሀ) ሕክምና እና የሃይማኖት ነጻነት

 

22. በማረሚያ ቤት የሚገኙ ታሳሪዎች በማረሚያ ቤቱ በሚገኝ እና በማንኛውም ጊዜ፣ በነጻ፣ የሙያው ሥነ ምግባር በሚፈቅደው መሠረት ሕክምና የማግኘት መብት አላቸው።[38] የፌደራል ማረሚያ ቤቶች የራሳቸው የሕክምና ቦታ አኑረው እስረኞችን የማሳከም ኃላፊነት ሲኖርባቸው፣ ሕክምናው በማረሚያ ቤት ውስጥ ከሚገኝ አቅም በላይ ከሆነ አና በሐኪም ከተረጋገጠ "[ማረሚያ ቤቱ] ተገቢውን ጥበቃ በመመደብ እስረኛው ያስፈለገውን የሕክምና አገልግሎት ሊሰጥ ወደሚችል የመንግሥት ሆስፒታል የመውሰድ [...]" ኃላፊነት አለበት።[39] እንዲሁም እስረኛ ከግል ሐኪሙ ጋር በጽሑፍ ወይም በአካል የመገናኘት መብቱ አለው።[40]

 

23. በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገብ 4ኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ ጉቱ ሙሊሳ በግንቦት 12፣ 2013 በዋለው ችሎት የሕክምና ቀጠሮ ቢኖራቸውም ማረሚያ ቤቱ አጃቢ ስለሌለ በሚል ሳይወስዳቸው እንደቀረ አመልክተዋል። ክስ ከመቀርቡ በፊት በግል ሐኪሞቻቸው እንዲታከሙ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ የተሰጠላቸውን በእነ ጃዋር መሐመድ መዝገብ የሚገኙ ተከሳሾች በበኩላቸው ማረሚያ ቤቱ ትዕዛዙን ማስፈፀም መቆሙን ለፍርድ ቤቱ ያሳወቁ ሲሆን፣ የማረሚያ ቤቱ ተወካይም ምከንያቱን እንዲያስረዱ መጠራታቸውን ተከትሎ በካቲት 22፣ 2013 በመቅረብ በጉዳዩ ላይ ይግባኝ ስለተባለ በመሆኑ ነው በሚል አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱም ትዕዛዙ ተፈፃሚነቱን እንዲቀጥል አሳስቧል። በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ የሚገኙ 2ኛ ተከሳሽ - አቶ ስንታየሁ ቸኮል በጥቅምት 4፣2013፣ እና 3ኛ ተከሳሽ - ወ/ሮ አስቴር ሥዩም ደግሞ በታኅሣሥ 12፣ 2013 በግል ሐኪሞቻቸው እንዲታከሙ ለፍርድ ቤቱ አመልክተዋል።

 

24. በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ የሚገኙት 2ኛ ተከሳሽ - አቶ ስንታየሁ ቸኮል ፀበል እንዲገባላቸው በጠየቁት መሠረት ፍ/ቤቱ በግንቦት 9፣ 2013 በዋለው ችሎት ለማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝ ቢሰጥላቸውም፣ ተከሳሹ በሰኔ 22፣ 2013 በነበረው ቀጠሮ ትዕዛዙ እንዳልተፈፀመላቸው ለፍርድ ቤቱ አሳውቀዋል። ማረሚያ ቤቱም ሐምሌ 8፣ 2013 በዋለው ችሎት ለፍርድ ቤቱ እንዳስረዳው ከዚህ በፊት ያልነበረ አሠራር በመሆኑ ፀበል ለማስገባት እንቸገራለን በሚል ቢያሳውቅም፣ ፍርድ ቤቱ እንደ ሌላው ማንኛውም መድኃኒት እንዲገባ በሚል አዟል። በኢትዮጵያ የፌደራል ማረሚያ ቤቶች ሕግ መሠረት እስረኞች የራሳቸውን ሃይማኖት እና እምነት የሌላውን ሳያውኩ እና ክብር ሳይነኩ ማራመድ እንደሚችሉ ይደነግጋል።[41]

 

ለ) ከውጪ መገናኘት

 

25. በእነ ጃዋር መዝገብ 12ኛ ተከሳሽ የሆኑት አቶ ሸምሰዲን ጠሃ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በስልክ መገናኘት እንደችሚሉ ፍርድ ቤቱ ቢያዝላቸውም፣ ማረሚያ ቤቱ ትዕዛዙን አለመፈፀሙን በግንቦት 12፣ 2013 በነበረው ችሎት የገለጹ ሲሆን፣ ፍ/ቤቱም ማረሚያ ቤቱ እንዲፈፅም አና መፈፀሙን በጽሑፍ እንዲያሳውቅ አዝዟል። እስረኞች ከትዳር አጋር፣ ከዘመድ፣ ጓደኛ፣ የሃይማኖት አባት ብሎም የሕግ አማካሪ ጋር በአካል ወይም በጽሑፍ የመገናኘት መብት አላቸው።[42]

 

VII. ማጠቃለያ

 

26. በእነ ጃዋር መሐመድ ብሎም የእነ እስክንድር ነጋ መዝገቦች ክስ ከተመሠረተበት ጀምሮ እስከ ዐቃቤ ሕግ ምስክር መስማት ጅማሮ ድረስ በነበሩ የፍርድ ቤት ሒደቶች በየደረጃው የነበሩ ፍርድ ቤቶች ጉዳዮቹን በሕግ እና በገለልተኝነት ሲሠሩ ተስተውለዋል። ክርክሩቹ ብዙ አቤቱታዎችን ያካተቱና እና የይግባኝ ክርክሮችም የተካሔደባቸው እንደመሆናቸው ረዘም ያለ ጊዜያት ፈጅተዋል። ነገር ግን ፍርድ ቤቶቹ ቀጠሮዎች የሚሰጡባቸው ምክንያቶች ብሎም የቀጠሮ ጊዜዎቹ በአብዛኛው ምክንያታዊ በመሆናቸው የተፈጠረ ፍትሕ የማግኘት መብት ተገድቧል ለማለት አይቻልም። ታዳሚዎች ግልጽ ችሎቶችን - አንዳንዴም አግባብነት ባላቸው ምክንያቶች፣ ሌላ ጊዜም ያለ በቂ ምክንያት - እንዳይሳተፉ ሲከለከሉ ተስተውሏል። የክስ ማመልከቻዎቹ ያካተቷቸው የወንጀል ድርጊቶች ውስብስብነት እና ድርጊቶቹ በግልጽ ተለይተው አለመቀመጣቸው የተከሳሾችን የመከላከል አቅም አደጋ ውስጥ ይከታል ተብሎ ሊወሰድ ይችላል። የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ለደኅንነታቸው ስጋት እንዳለባቸው በማስረጃ መረጋገጥ ስላልቻለ፣ ዐቃቤ ሕግ ምስክሮቼ በዝግ ችሎት እና ከመጋረጃ ጀርባ ይሰሙልኝ በሚል ያቀረበው አቤቱታው በተደጋጋሚ ውጤታ አልባ ሆኗል - ፍ/ቤቶች የተከሳሾች የመከላከል መብት ላለመገደብ የሔዱበት ርቀትም ሊደነቅ የሚገባው ነው። በአካል ቀርቦ የመከራከር መብት የተነፈገበት ሒደትም አጠያያቂ ሲሆን፣ ጉዳዩ ይሄ ትንታኔ እስከታተመበት ጊዜ ድረስ በሒደት ላይ ይገኛል። ማረሚያ ቤቶች ለእስረኛዎቹ የሕክምና ብሎም ከእምነት ነጻነት ጋር የተያያዙ መብቶችን ለመፈፀም የፍርድ ቤት ትዕዛዝን የመጠበቅ፣ ብሎም ትዕዛዝ ከተሰጠም በኋላ ያለመፈፀም አዝማሚያ ያሳዩባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ።

 

[1]https://www.cardeth.org/am/section/%e1%8b%9c%e1%8a%93/%e1%8b%a8%e1%89%bd%e1%88%8e%e1%89%b5-%e1%8b%8d%e1%88%8e/

 

[2] https://www.cardeth.org/pre-trial-proceedings-of-post-hachalu-detentions-legal-analysis-of-selected-cases/

 

[3] ሚኪያስ በቀለ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር እና ጠበቃ ናቸው። ሚኪያስ ይህንን የሕግ ትንታኔ ያዘጋጁት በካርድ ጥያቄ ነው።

 

[4] https://www.cardeth.org/pre-trial-proceedings-of-post-hachalu-detentions-legal-analysis-of-selected-cases/ (Accessed on December 2021)

 

[5] International Covenant on Civil and Political Rights (ICPR), Adopted by the General Assembly of the United Nations on 19, December 1966. Article 9(1), Ethiopia accede the ICCPR on June 11, 1993. See https://treaties.un.org/  (accessed on October, 2020), (ከዚህ በኋላ "የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶቸ ቃል ኪዳን" እየተባለ የሚጠቀስ)

 

African Charter on Human and Peoples' Rights (ACHPR), Adopted on 27 June 1981, Entered into force on 21 October 1986, Article 6 Ethiopia ratified the ACHPR on June 15, 1998 and deposited on June 22, 1998. See https://au.int/en/treaties/african-charter-human-and-peoples-rights (accessed on October, 2020) ከዚህ በኋለ "የአፍሪካ የሰብዓዊ መብቶች ቻርተር " እየተባለ የሚጠቀስ)

 

[6] የኢትዮጲያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲየዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት፣ አዋጅ ቁጥር 1/1987፣ የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ፣ አንደኛ አመት ቁጥር 1፣ (ነሃሴ፣ 1987 ዓ.ም) (ከዚህ በኋላ "የአትዮጲያ ሕገ መንግሥት" እየተባለ የሚጠቀስ)፣ አንቀጽ 17(1)(2) ፡፡

 

[7] Principle and Guidline on the Right of Fair Trial and Legal Assistance in Africa, African Commision on Human and Peoples' Rights (ከዚህ በኋላ "የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መመሪያ" እየተባለ የሚጠቀስ)፣ አንቀጽ M(1)(E)፡፡

 

[8] የወንጀለኛ መቀጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ፣ የነጋሪት ጋዜጣ፣ ቁጥር 1፣ በተለየ የወጣ፣ (ጥቅምት፣ 1954) (ከዚህ በኃላ "የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ" እየተባለ የሚጠቀስ)፣ አንቀጽ 93፡፡

 

[9] የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ፣ አንቀጽ 57፡፡

 

[10] የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ፣ አንቀጽ 64፡፡

 

[11] የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን፣ አንቀጽ 14(3)(c) General Comment 32, Article 14፣ Right to equality before Courts and tribunals and to fair trial, Human Rights Committee (August 23, 2007)፣ (ከዚህ በኋላ "የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ አስተያየት ቁጥር 32" እየተባለ የሚጠቀስ)፣ አንቀጽ 35፡፡

 

[12] ዝኒ ከማሁ

 

[13] ዝኒ ከማሁ

 

[14] ፍርድ ቤቶች በወንጀል ክርክር ጊዜ ቀጠሮ ሊሰጡ የሚችሉት - የተከራካሪዎች በበቂ ምክንያት መቅረት፣ የምስክሮች መቅረት፣ ለምርመራ ጊዜ ለመስጠት በሚል፣ ተጨማሪ ማስረጃ እንዲቀርብ፣ አዲስ ማስረጃ በድንገት መገኘቱ፣ የክስ ማመልከቻ ተሻሽሎ ለዝግጅት ጊዜ ሲያስፈልግ፣ ለዝግጅት በቂ ጊዜ ካልተሰጠ፣ ክሱ ከመጀመሩ በፊት የሚያስፈልግ ፍቃድ ካለ፣ ለተያዘው ጉዳይ በሌላ ፍርድ ቤቱ እልባት ማግኘት ያለበት ጉዳይ ካለ፣ የተከሳሽ አእምሮ ሁኔታ መታየት ካለበት፣ አካለ መጠን ላልደረሰ ተከሳሽ ጠባቂ የሚያስፈልገው ሲሆን እና የጉዳዩ መሠማት በአንድ ቀን ማጠቃለል የማይቻል ከሆነ ነው፡፡  የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ፣ አንቀጽ 94(2) ይመለከቷል፡፡

 

[15] የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን፣ አንቀጽ 14(1)፣ አጠቃላይ አስተያየት 32፣ አንቀጽ 28፡፡

 

[16] ዝኒ ከማሁ፡፡

 

[17] የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መመሪያ፣ አንቀጽ A(3)(e)፡፡

 

[18] ዝኒ ከማሁ፡፡

 

[19] የሲቪል እና ፖለቲካ መብቶቸ ቃል ኪዳን፣ አንቀጽ 14(1)፣ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ አስተያየት ቁጥር 32፣ አንቀጽ፣ 29፡፡

 

[20] የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መመሪያ፣ አንቀጽ A(3)(f)፡፡

 

[21] የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶቸ ቃል ኪዳን፣ አንቀጽ 9(2) እና 3(ሀ)፡፡

 

[22] የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መመሪያ፣ አንቀጽ N(1)፡፡

 

[23] የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት፣ አንቀጽ 20(2)፡፡

 

[24] የክስ መቃወሚያ ወደ ክርክር ከመግባቱ በፊት በተከሳሽ የሚቀርብ ሲሆን ምክንያቶቹ -  ክሱ ሟሟላት የሚገባውን ቅድመ ሁኔታ አለሟሟላቱ፣ ጉዳዩ በሌላ ፍርድ ቤት እየታየ መሆኑ፣ በተመሳሳይ ክስ ከዚህ በፊት ተከሶ ነጻ ወይም ጥፋተኛ የተባለ ከሆነ፣ ጉዳዩ በይርጋ የታገደ ከሆነ፣ ምህረት የተሰጠ ከሆነ፣ ክሱ ኬሎች ወንጀሎኝ ጋር በጋራ መከሰሰ ጥቅሙን የሚጎዳ ከሆነ፣ በሌላ ችሎት የቀረበ ክስ ሳይፈጸም የተያዘው ጉዳይ መታየት የሌለበት ከሆነ እና ፈጸመ ለተባለው ድርጊቶች ተከሳሹ ኃላፊነት የሌለበት መሆኑ - ሊሆኑ ይችላል፡፡ የወ/መ/ሥ/ሥ/፣ አንቀጽ 119 እና ተከታዮቹ፣ አንቀጽ 130፡፡

 

[25] የኢትዮጲያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ፣ አዋጅ ቁጥር 1117/2011፣ የፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ (መጋቢት፣ 2011 ዓ.ም)፡፡

 

[26] የወንጀል ሕግ ወደ ኋላ ተመልሶ አይሰራም (Non-retroactivity of Criminal Law) የሚለው መሠረታዊ የወንጀል ሕግ መርሆ ነው፡፡  የኢትዮጲያ ሕገ መንግስሥት፣ አንቀጽ 23፣ የኢትዮጲያ የወንጀል ሕግ፣ አንቀጽ 5 እና የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ፣ አንቀጽ 2"ን" ይመለከቷል፡፡

 

[27] የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን፣ አንቀጽ 14(3)(b)፣ የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ አጠቃላይ አስተያየት 32፣ አንቀጽ 33፡፡

 

[28] የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መመሪያ፣ አንቀጽ A(2)(e)፡፡

 

[29] የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መመሪያ፣ አንቀጽ A(3)(e)፡፡

 

[30] የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መመሪያ፣ አንቀጽ N(6)(f)፡፡

 

[31] የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መመሪያ፣ አንቀጽ A(3)(i)፡፡

 

[32] ስለወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ የወጣ አዋጅ፣ አዋጅ ቁጥር 699/2013፣ የነጋሪት ጋዜጣ፣ (የካቲት፣ 2003 ዓ.ም) (ከዚህ በኋላ "የምስክሮች ጥበቃ አዋጅ" እየተባለ የሚጠቀስ)፡፡

 

የምስክሮች ጥበቃ የሚደረገው ከ10 ዓመት በማያንስ መቀጮ ለሚያሰቅጡ ወንጀሎች ምስክርነት ወይም መረጃ ለሰጡ፣ በምስክሩ ወይም ቤተሰቡ አካል/ንብረት ላይ አደጋ ይደርሳል ተብሎ ሲታመን እና ደህንነቱ በጥበቃ ብቻ ይረጋገጣል ተብሎ ሲታሰብ ነው፡፡ የምስክሮች ጥበቃ ከሚደረግባቸው አጋጣሚዎች ውስጥ የወንጀል ጉዳዮች ምሰክር ማንነትን መደበቅ፣ በዝግ ችሎት እንዲካሄድ፣ ብሎም በአካል ሳይታዩ ከመጋረጃ ጀርባ ቃል እንዲሰጡ የሚደረጉባቸው አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ጥበቃ የሚደረገብት አካሄድ የሚወሰነው ሊደርስ የሚችለው አደጋ፣ እና ጥበቃው በሌላ ሰው መብት ላይ በሚያመጣው ተጽህኖ አንጻር ይሆናል፡፡ ጥበቃው እንዲደረግ የሚወሰነው በፍትሕ ሚንስትር ሲሆን እራሱ ጥበቃው እንዲደረግለት የሚፈልገው ግለሰብ፣ እሱ ካልቻለ በመርማሪ ወይም በዓቃቢ ሕግ ብሎም ጉዳዩ ያገባኛል በሚሉ አካላት ጥያቄው ሊቀርብ ይችላል፡፡ ጥበቃው የሚደረገው በጥበቃው ተጠቃሚ እና በፍትሕ ሚንስትር መካከል በሚደረግ ስምምነት ይሆናል፡፡ የምስክሮች ጥበቃ አዋጅ አንቀጽ 3፣ 4፣ 5፣ 6፣ 7 እና 10ን ይመለከቷል፡፡

 

[33] አቶ ጀዋር ሲራጅ መሃመድ በጥቅምት 1፣ 2012 ዓ.ም ጠባቂዎቼ በእኩለ ለሊት በመንግሥት እንዲነሱ ታዘዋል፣ ይህም ለሕይወቴ አደጋ ነው በሚል በማህበራዊ ሚዲያ መግለጻቸውን ተከትሎ በተለያዩ በሀገሪቷ ክፍሎች በደጋፊዎቻቸው በተነሳ አመጽ ከ80 በላይ ሰዎች ሕይወት እንዲጠፋ እና ንብረት እንዲወድም ሆኖአል፡፡

 

[34] የወ/መ/ሥ/ሥ/ሕ፣ አንቀጽ 160 እና ተከታዮቹ፡፡

 

[35] የአፍሪካ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን መመሪያ፣ አንቀጽ N(6)(c)፡፡

 

[36] የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን፣ አንቀጽ 7፡፡

 

[37] የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት፣ አንቀጽ 21(1)፣ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ቃልኪዳን፣ አንቀጽ 10(1)፣ እንዲሁም የፌደራል ማረሚያ ቤት አዋጅ፣ አዋጅ ቁጥር 1174/2012፣ የነጋሪት ጋዜጣ (የካቲት፣ 2012 ዓ.ም)፣ አንቀጽ 23፣ (ከዚህ በኋላ "የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አዋጅ" እየተባለ የሚጠቀስ) ይመለከቷል፡፡

 

የፌደራል ማረሚያ ቤት አዋጅ በፌደራል ማረሚያ ቤቶች ውስጥ ፍርድ ተፈርዶባቸው የሚገኙ ታራሚዎችን፣ ዋስትና መብታቸው ተከልከለው በእስር ላይ የሚገኙ ታሳሪዎችን፣  ብሎም ከፍትኃ ብሔር ጉዳይ ጋር ተያይዞ የታሰሩ ታሳሪዎችን ጨምሮ ስላለው የእስረኞች አያያዝ ይተዳደርበታል፡፡ የፌደራል ማረሚያ ቤት አዋጅ አንቀጽ 2(7) ይመለከቷል፡፡

 

[38] የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አዋጅ፣ አንቀጽ 37፡፡

 

[39] የፌደራል ማረሚያ ቤት አዋጅ፣ አንቀጽ 37 በተለየ ንኤስ አንቀጽ 9፡፡

 

[40] የፌደራል ማረሚያ ቤት አዋጅ፣ 40(1)፡፡

 

[41] የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አዋጅ፣ አንቀጽ 38፡፡

 

[42] የፌደራል ማረሚያ ቤት አዋጅ፣ አንቀጽ 40(1)፡፡

 

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.