የእነ ጃዋር መሐመድ ጉዳይ በሌሉበት እንዲታይ ተወሰነ

ሐምሌ 21፣ 2013፤ ጃዋር መሐመድ፣ በቀለ ገርባ፣ ሃምዛ አዳነ እና ደጀኔ ጣፋ ዛሬም ለተከታታይ ሦስተኛ ጊዜ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ቀርተዋል።

የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥት ጉዳዮች ችሎት የእነ ጃዋር መሐመድ የክስ ሒደት አሰማም ሁኔታ ላይ ለማከራከር የያዘው ቀጠሮ ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባን ጨምሮ አራት ተከሳሾች ባለመቅረባቸው ለዛሬ እንዲቀርቡ ማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።

ፍርድ ቤቱ የዛሬው ችሎት የተያዘው ከዚህ ቀደም ከችሎቱ የቀሩ ተከሳሾች እንዲቀርቡ ለማረሚያ ቤት ትዕዛዝ መስጠቱን አስታውሶ፣ ይሁንና ዛሬም አራቱ ተከሳሾች ባለመቅረባቸው ብይን መስጠቱን አስታውቋል። በዚህም መሠረት ተከሳሾቹ ከዚህ ቀደም ከፍርድ ቤቱ ለመቅረታቸው የፍርድ ቤት ውሳኔዎች ላይ የአስፈፃሚ አካላት ጣልቃ ገብነትን በተግባር ማየታቸው በፍትሕ ሒደቱ ላይ ተስፋ እንዳስቆረጣቸውና ከዚህ በኋላ ፍርድ ቤት መቅረቡ የአገር ሀብት ከማባከንና ጊዜያቸውን ከመሻማት የዘለለ ፋይዳ እንደሌለው ቢያመለክቱም፣ ፍርድ ቤቱ ይህ በዚህ ችሎት ላይ ያልተስተዋሉ በመሆኑ ውድቅ አድርጌዋለሁ ብሏል።

የተጠቀሱት አራቱ ተከሳሾች ዛሬም ለፍርድ ቤት ያልቀረቡ በመሆኑ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 20 እና ኢትዮጵያ የፈረመቻቸው ሌሎች የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎች መሠረት ራሳቸውን የመከላከል መብታቸውን በፍላጎታቸው አለመጠቀማቸው ታውቆ ክርክሩ በሌሉበት እንዲቀጥል ፍርድ ቤቱ ወስኗል። ዐቃቤ ሕግ ተከሳሾቹ በማረሚያ ቤት በሕግ ጥላ ሥር የሚገኙ በመሆኑ ተገደው እንዲቀርቡ ሲል ያቀረበውን ሐሳብ ግን ፍርድ ቤቱ ውድቅ አድርጎታል።

በሌላ በኩል ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት ሌሎች ተከሳሾች በሕግ ቁጥጥር ሥር ሲውሉ የተያዘባቸው ንብረቶችን ጨምሮ የባንክ ሒሳባቸው እንዲለቀቅላቸው ጠይቀው፣ ፍርድ ቤቱም አንድ ላይ በማመልከቻ በጠበቆች በኩል እንዲቀርብ አዝዟል።  

ሸምሰዲን ጠሃ በግላቸው በድሬደዋ ማረሚያ ቤት ጫት እንደሚፈቀድ በመጥቀስ በተመሳሳይ መልኩ ይሄም የፌዴራል ከተማ እንደመሆኑ መጠን ጫት እንዲገባላቸው እና ሚስቶቻችን ማግኘት ደግሞ አንዱ የሰብዓዊ መብት አካል ስለሆነ እንድንገናኝ ሊፈቀድልን ይገባል በማለት አቤቱታ አቅርበዋል። ፍርድ ቤቱ በምስክር አሰማም ሒደቱ ዐቃቤ ሕግ ያሻሻለው አቤቱታ ላይ የተከሳሾች ጠበቆች መልስ እንዲያቀርቡ እና ሌሎች የተከሳሾቹን አቤቱታ ለማየት ለሐምሌ 30 ቀን 2013 ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.