ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዐቃቤ ሕግ በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ ያሉ አምስት ምስክሮቼ ‘ከመጋረጃ ጀርባ ይደመጡልኝ’ ሲል ያቀረበውን የይግባኝ ክርክር አደመጠ

ሚያዝያ 15፣ 2013 - ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፌደራል ከፍተኛ  ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ ሽብር እና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ ምስክሮች  በግልጽ ችሎት ይታዩ ብሎ የሰጠውን ውሳኔ ተከትሎ  ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ማለቱ ይታወሳል። በዚህ ሥሚ፣ እስክንድር ነጋን ጨምሮ ሦስቱ ተከሳሾች በፕላዝማ ቀርበዋል።

ይህን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ 16 ምስክሮቹን በዝግ ችሎት፣ ቀሪ 5 ምስክሮቹን ደሞ ከማጋረጃ ጀርባ እንዲሰሙለት ጠይቋል።

ዐቃቤ ሕግ የምስክሮችን ማንነት መደበቅ የተፈለገበት ምክንያት በሁለት መልኩ ለችሎቱ አስረድተዋል፤ በቅድመ ምርመራ ወቅት ምስክርነት ሰጥተው የነበሩ ምስክሮች ላይ የግድያ ዛቻ ደርሶባቸው እንደነበረ እና አሁንም ተመሳሳይ ችግር ሊገጥም ይችላል ብለው ስጋት እንዳለባቸው፤ ምስክሮች በዝግ ችሎት እና ከማጋረጃ ጀርባ መመስከራቸው የተከሳሾችን መብት ይጋፋል ብለው እንደማያምኑ፣ በተጨማሪም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 20(4) መሠረት ተከሳሾች ማስረጃውን የመመልከት፣ ምስክርን ደሞ የመጠየቅ መብት ነው ያላቸው ብሏል።

ተከላካይ ጠበቆች በበኩላቸው የምስክሮችን ማንነት መደበቅ እውነተኛ ምስክርነትን ለማድመጥ አዳጋች እንደሚሆን፣ ምናልባትም ምስክሮቹ ከደንበኞቻቸው ጋር የግል ጠብ ይኑራቸው ወይንም ደግሞ ለፓርቲው ጥላቻ ስላለባቸው ይሆን የሚመሰክሩት ማወቅ አይቻልም። በተጨማሪም ዐቃቤ ሕግ በምስክሩ ላይ ደርሷል ስላሉት የግድያ ዛቻ ማስረጃ እንዳላቀረቡ ለችሎቱ አስታውሰዋል።

እስክንድር ነጋ በበኩላቸው፣ ይህ አሠራር በኢትዮጵያ ውስጥ ተግባራዊ የሚሆነው በሴቶችና እና በሕፃናት ላይ በሚደርስ ፆታዊ ጥቃት ነው ብለዋል።

ይሁንና ዐቃቤ ሕግ ይህ አሠራር በውጪ አገራት የተለመደ ነው ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

በዚህ መዝገብ ሁለተኛ ተከሳሽ የሆኑት ስንታየሁ ቸኮል "እኛ በመንግሥት ትዕዛዝ እንደታሰርን እናውቃለን። ምናልባትም ይህ ችሎት የታችኛውን ፍርድ ቤት ውሳኔ የሚሽር ከሆነ፣ የፍትህ ስርዓቱ ላይ ለውጥ አለ የሚባለው ሙሉ በሙሉ ውሸት ነው" ብለዋል።

ሦስተኛ ተከሳሽ ቀለብ ስዩም ምስክር በዝግ ችሎት መሆኑ መስካሪው እንዲዋሽ ዕድል ይሰጠዋል፣ ዳኞችም ሚዛናዊ የሆነ ውሳኔ ለመስጠት እንዲቸገሩ ያደርጋቸዋል፣ ከሰብዓዊ መብቶች አንፃር ደሞ የተከሳሾችን መብት የሚጥስ ነው በማለት የምስክሮችን የሥም ዝርዝር ጠይቃለች።

አራተኛ ተከሳሽ አስካል ሕዝቡ ሚዛናዊ ነው ብሎ መገምገም የሚችለው በግልጽ ችሎት ሲሆን ብቻ ነው ብለዋል።

ተከላካይ ጠበቆች በበኩላቸው የምስክሮችን ደህንነት አስጊ ነው ተብሎ ከታሰበ የመኖሪያ ቦታቸውን መቀየር አልያም መሣሪያ በማስታጠቅ ደኅንነታቸውን ማስጠበቅ እንደሚቻል ለችሎቱ ገልጸዋል።

ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ ምስክሮቹ የአዲስ አበባ ነዋሪ አና ሠራተኛ እንደመሆናቸው መጠን የእነሱን የመኖሪያ ቦታ መቀየር አዳጋች እንደሚሆን፣ መሣሪያ ማስታጠቁም አገሪቷ አሁን ካለችበት የደኅንነት ሁኔታ ለግለሰብ ማስታጠቁ ትክክል እንዳልሆነ አሳውቀዋል። ችሎቱ ግራ ቀኙን ካደመጠ በኋላ ለውሳኔ ቀጣይ ቀጠሮ ለሚያዝያ 26 2013 ሰጥቷል።

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.