ፍርድ ቤቱ በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ የፌዴራል ፖሊስ የፍርድ ቤት መጥሪያ ለምስክሮች በየአድራሻቸው እንዲያደርስ ጥብቅ ትዕዛዝ ሰጠ

ሕዳር 102014 - የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አንደኛ የፀረ ሽብርና ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮች ወንጀል ችሎት በእነ እስክንድር ነጋ መዝገብ የቀጠረው ቀሪ ሦስት  የዐቃቤ ሕግ ምስክሮች ለማድመጥ ነው። በኮሮና በሽታ ታመው፣ በኋላም አገግመው ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ የተባሉት አራተኛ የዐቃቤ ሕግ ምስክር በዚህ ችሎት ይቀርባሉ ተብሎ ቢጠበቅም ሳይቀርቡ ቀርተዋል። ዐቃቤ ሕግም ምስክሩን በስልክ ለማግኘት ቢሞክሩም ግን ማግኘት እንዳልቻሉ ለችሎቱ አሳውቀዋል።

ቀሪ 8ኛ እና 9ኛ ምስክሮች በተደጋጋሚ ያለመገኘታቸውን በሚመለከት ፍርድ ቤቱ መጥሪያ እንዲደርሳቸው በሕዳር 7፣ 2014 ትዕዛዝ ሰጥቷል። ይህን ተከትሎ የፌዴራል ፖሊስ የሆኑት ረ/ሳጅን ቢኒያም አፈወርቅ መጥሪያ የደረሳቸው ዘግይቶ በሕዳር 9 ከሰዓት በኋላ መሆኑን እና ወደ ምስክሮቹ በተደጋጋሚ ስልክ ቢደውሉላቸውም መገኘት አለመቻላቸውን በደብዳቤ ለችሎቱ ገልጸዋል። ይህን ተከትሎ ዐቃቤ ሕግ ተለዋጭ ቀጠሮ ይሰጠን ሲሉ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

ተከላካይ ጠበቆች የዐቃቤ ሕግ የቀጠሮ ይሰጠን ጥያቄ በጥብቅ በመቃወም፤ በተደጋጋሚ የተከሳሾችን መብት የሚጠብቁ ትዕዛዞችን በዐቃቤ ሕግ ሆን ተብሎ እንዲጓተት እየተደረገ ነው፤ ይህን ማድረግ ደሞ ሥነ ስርዓት ሕጉም አይፈቅድለትም በማለት ችሎቱ በተደጋጋሚ ለዐቃቤ ሕግ ዕድል ቢሰጠውም ዐቃቤ ሕግ ግን ሊጠቀምበት አልቻለም። እንደውም  በተቃራኒው የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ በግዴለሽነት ያለመፈፀም ነገር ነው የሚታየው ብለዋል።

በተጨማሪም ዐቃቤ ሕግ ለምስክሮች ከስልክ ከመደወል የዘለለ እነሱን ለማግኘት ያደረገው ምንም ዓይነት ጥረት የለም፤ ተቋሙ ካለው አቅም አንፃር ጥረት ማድረጉን የሚያሳይ ምንም ነገር የለም፤ ፍትሕ ከማጋተት ተለይቶ መታየት የለበትም ስለዚህ በተሰሙ ምስክሮች ፍትሕ እንዲሰጣቸው ችሎቱን ጠይቀዋል።

ሌላኛው ጠበቃ በማከል በዚህ የእስር ግዜ "አቶ እስክንድር ሁለት ግዜ ተደብድበዋል፣ አቶ ስንታየሁ የኩላሊት በሽቸኛ ሆነው መድኃኒት ይዘው ነው የሚንቀሳቀሱት፣ / ቀለብ ሕፃን ልጃቸው ከእናታቸው በመራቃቸው ጭንቀት ደርሶባቸዋል፣ / አስካል ከታማሚ እናታቸው ጋር በሳምንት አንድ ግዜ 10 ደቂቃ በስልክ እንዲያገኛቸው የተፈቀደው ገና ሰሞኑን ነው። ይሔ ሁሉ መስዋዕትነት እየከፈሉ ያሉት ፍትህ እናገኛለን በሚል ተስፋ ነው" ብለዋል። ዐቃቤ ሕግ ምስክሮቹ ስልክ አጥፍተዋል ላገኛቸው አልቻልኩም እያለ ስለሆነ ከዚህ በኃላ ዕድል ሊሰጣቸው አይገባም ፣ የተፋጠነ ፍትህ ከፍርድ ቤቱ እንጠብቃለን ሲሉ ለአቃቤ ሕግ አቤቱታ ምላሽ ሰተዋል።

በመዝገቡ ተከሳሽ የሆኑት ስንታየሁ ቸኮል፣ ቀለብ ሥዩም፣ አስካል ደምሌ እና ጌትነት እንየው ለዐቃቤ ሕግ ተጨማሪ ቀጠሮ ሊሰጠው አይገባም፤ ፍርድ ቤቱ ፍትሕ ሊሰጠን ይገባል። ፍትሕ ጠምቶናል ሲሉ ተደምጠዋል። የግራ ቀኙን ክርክር ያደመጠው ፍርድ ቤት ለፌደራል ፖሊስ ተወካይ ረ/ሳጅን ቢኒያም አፈወርቅ ለምስክሮች በየአድራሻቸው ሔደው መጥሪያ እንዲያደርሱ ትዕዛዝ ሰቷል።

Add a review

The comment language code.

Restricted HTML

  • Allowed HTML tags: <a href hreflang> <em> <strong> <cite> <blockquote cite> <code> <ul type> <ol start type> <li> <dl> <dt> <dd> <h2 id> <h3 id> <h4 id> <h5 id> <h6 id>
  • Lines and paragraphs break automatically.
  • Web page addresses and email addresses turn into links automatically.